Saturday, 10 October 2015 16:36

የኬንያ ፓርላማ መብራት ለ3 ቀናት መቋረጡ አባላቱን አወዛገበ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 * “መጸዳጃ ቤት ተቆልፎብናል፤ ውሃና መብራትም ተቋርጦብናል”   - ተቃዋሚዎች
                         * ፓርላማው 97 ሺህ ዶላር የመብራት ኪራይ አልከፈለም
    የሚመለከተው የመንግስት አካል መክፈል የሚገባውን 97 ሺህ ዶላር የመብራት ኪራይ ባለመክፈሉ ሳቢያ በኬንያ ፓርላማ ለ3 ቀን መብራት መቋረጡንና ይህም የተቃዋሚ ፓርቲ ፓርላማ አባላትን ክፉኛ ማስቆጣቱን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ተቃዋሚዎቹ ለክስተቱ መንግስትን ተጠያቂ ማድረጋቸውንና የውሎ አበል እንደማይከፈላቸው በምሬት መናገራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ የገዢው ፓርቲ አባላት በበኩላቸው፣ ለመንግስት ወግነው መከራከራቸውን ገልጧል፡፡
ካለፈው ሳምንት አርብ ጀምሮ እስከ ሰኞ ድረስ የፓርላማው መብራት መቋረጡ በአባላቱ መካከል ውዝግብ መፍጠሩን የገለጸው ዘገባው፣ በወቅቱም የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አዳን ኬናን የተባሉ የፓርላማው አባል አንድ የኤሌክትሪክ ሃይል መስመር ጥገና ባለሙያ ድንገት ከተፍ ብሎ የፓርላማውን የመብራት መስመር እንደቆረጠው ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ሌላው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ ችሪስ ዋማላዋ በበኩላቸው፣ በነጋታውም መጸዳጃ ቤት ለመጠቀም ፈልገው ወደዚያው ሲያመሩ ተቆልፎ እንዳገኙትና በፓርላማው ግቢ ውስጥ የውሃም ሆነ የመብራት አቅርቦት እንዳልነበር ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡
የኬንያ መንግስት እየተባባሰ የመጣ የገንዘብ እጥረት ቀውስ ውስጥ እንደገባ የገለጸው የቢቢሲ ዘጋቢ፣የፓርላማው የፋይናንስ ኮሚቴ አባላትም በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር መሰብሰባቸውን ገልጾ፣ ይሄም ሆኖ ግን ለፋይናንስ ቀውሱ ተጠያቂው ማነው በሚለው ጉዳይ ዙሪያ ተቃዋሚዎችና የገዢው ፓርቲ አባላት ሊግባቡ አለመቻላቸውን ጠቁሟል፡፡

Read 1213 times