Saturday, 10 October 2015 16:33

የ2015 የኖቤል ተሸላሚዎች ይፋ እየተደረጉ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  - 273 ግለሰቦችና ተቋማት በዕጩነት ቀርበዋል

       የዘንድሮው የዓለም የኖቤል ሽልማት ተሸላሚዎች ዝርዝርም በያዝነው ሳምንት ይፋ መደረግ የጀመረ ሲሆን፣ ተሸላሚዎችም ከአንድ ወር በኋላ በስቶክሆልምና በኦስሎ በሚከናወኑ ስነስርዓቶች የገንዘብ ሽልማታቸውን ይቀበላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኖቤል የሽልማት ድርጅት ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፣ በዘንድሮው የኖቤል ሽልማት የተለያዩ ዘርፎች 205 ግለሰቦችና 68 ተቋማት በዕጩነት የቀረቡ ሲሆን የየዘርፉ ተሸላሚዎችም ይፋ መደረግ ጀምረዋል፡፡
በሳምንቱ ይፋ ከተደረጉት የ2015 የኖቤል ሽልማት ዘርፎች አሸናፊዎች መካከል፣ የፊዚክስ ዘርፍ ተሸላሚዎቹ ጃፓናዊቷ ታካኪ ካጂታ እና ካናዳዊው አርተር ቢ ማክዶናልድ ይጠቀሳሉ፡፡ ሁለቱ ተመራማሪዎች ለዚህ ሽልማት የበቁት፣ በኒዪትሮኖች ባህሪ ዙሪያ ባደረጉት ምርምር ባበረከቱት ቁልፍ አስተዋጽኦ ነው ተብሏል፡፡
ረቡዕ ዕለት ይፋ የተደረገው የኬሚስትሪ ዘርፍ የኖቤል ተሸላሚዎች ውጤት ደግሞ፣ ስዊድናዊው ቶማስ ሊንዳል፣ አሜሪካዊው ፖል ሞድሪች እና ቱርክ-አሜሪካዊው አዚዝ ሳንካር አሸናፊ መሆናቸውን ያሳወቀ ሲሆን፣ በዲኤንኤ ዙሪያ በጋራ ያደረጉት ምርምር ተሸላሚ እንዳደረጋቸው የሽልማት ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ባለፈው ሰኞ በስዊድኑ ካሮሊንስካ ኢንስቲቲዩት ይፋ የተደረገው የ2015 የኖቤል የህክምና ዘርፍ ሽልማት ውጤት ደግሞ፣ የዘንድሮውን የዘርፉ ሽልማት ዊሊያም ሲ ካምቤል፣ ሳቶሺ ኦሙራ እና ቱ ዮዩ የተባሉ ሶስት ሳይንቲስቶች እንደተጋሩት ገልጧል፡፡
የሽልማቱን ግማሽ ገንዘብ የሚወስዱት በዘርፉ ተሸላሚ በመሆን የመጀመሪያዋ ቻይናዊት ሳይንቲስት ቱ ዮዩ ሲሆኑ፣ የወባ በሽታን በማዳን ረገድ ወደር እንደማይገኝለት የተነገረለትን መድሃኒት በመፍጠራቸው ለሽልማት የበቁ ተመራማሪ ናቸው፡፡ ቀሪውን ግማሽ ገንዘብ ለሁለት የሚካፈሉት ደግሞ፣ በጋራ ምርምራቸው በፈጠሩት አርቴምሲኒን የተሰኘና በጥገኛ ተዋህስያን ሳቢያ የሚከሰቱ በሽታዎችን የሚያድን መድሃኒት ተሸላሚ የሆኑት ጃፓናዊው ማይክሮ ባዮሎጂስት ሳቶሺ ኦሙራ እና አሜሪካዊው ሳይንቲስት ዊሊያም ካምቤል ናቸው፡፡
በ2015 የዓለም የኖቤል ሽልማት የስነጽሁፍ ዘርፍ ደግሞ፣ ቤላሩሳዊቷ ደራሲ ቬትላና አሌክሴቪች ተሸላሚ መሆኗን የሽልማት ድርጅቱ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡
ትናንት ይፋ በተደረገው የ2015 የኖቤል የሰላም ሽልማት ውጤት መሰረትም፣ በዘርፉ ናሽናል ዲያሎግ ኳርቴት የተባለው የቱኒዝያ ተቋም በአገሪቱ ብዝሃነት ያለው ዴሞክራሲ ለመፍጠር ባደረገው አስተዋጽኦ ተሸላሚ የሆነ ሲሆን፣ የኢኮኖሚከስ ዘርፍ ተሸላሚዎች ደግሞ ከነገ በስቲያ ይፋ እንደሚደረጉ ይጠበቃል፡፡
እ.ኤ.አ ከ1901 እስከ 2014 ድረስ ለ567 ጊዚያት በተከናወኑት የዓለም የኖቤል እና የኢኮኖሚክ ሳይንስስ ሽልማቶች፣ በድምሩ 889 ግለሰቦችና ተቋማት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

Read 1780 times