Saturday, 10 October 2015 15:51

የአንጋፋው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ የቀብር ስነስርአት ተፈፀመ

Written by  አበባየሁ ገበያው (ከአሜሪካ)
Rate this item
(3 votes)

  አንጋፋው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ በስደት በሚኖርበት አሜሪካን ሃገር በርካታ ወዳጆቹ፣ የሙያ አጋሮቹና ቤተሰቦቹ በተገኙበት ከትላንት በስቲያ የቀብር ስነስርዓቱ ተፈጽሟል፡፡
ጋዜጠኛ፣ ፀሐፊ፣ የታሪክ እና የፖለቲካ ተንታኝ የሆነው አንጋፋው ሙሉጌታ ሉሌ በ1933 ዓ.ም በጐጃም ክፍለሀገር ቢቸና ይልማና ዴንሳ በሚባል ስፍራ የተወለደ ሲሆን የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ናዝሬት ባይብል አካዳሚ በመግባት ከተማረ በኋላ በሠለጠነበት የትምህርት መስክ እዚያው አካዳሚ ውስጥ በመምህርነት አገልግሏል፡፡በወቅቱም የታሪክ ባለሙያውና ፖለቲከኛውን ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ዶ/ር ላጲሶ ጋዴቦ፣ ፖለቲከኛው አቶ ሌንጮ ለታን ጨምሮ በሃገሪቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበሩ በርካታ ግለሰቦችን ማስተማሩን ከህይወት ታሪኩ መረዳት ተችሏል፡፡  በንጉሱ እና በደርግ ዘመን በተለያዩ የሬድዮ ጣቢያዎችና አዲስ ዘመንን ጨምሮ በተለያዩ የፕሬስ ውጤቶች ላይ በከፍተኛ ሃላፊነት ጭምር ሲሠራ የቆየው ሙሉጌታ ሉሌ፣ በደርግ ውድቀት ማግስት ከስራው እንዲለቅ በመደረጉ፣ በ1984 ከሌሎች አጋሮቹ ጋር በመሆን “ጦቢያ” መጽሔትን አቋቁሞ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በግል ጋዜጠኝነት ስራው ከ16 በላይ ክስ ቀርቦበት እንደነበር የተገለፀው ሙሉጌታ ሉሌ፣ በደህንነቶች ከፍተኛ ክትትል ስር በመግባቱ በወዳጆቹ ጉትጐታ ወደ አሜሪካ መሰደዱ በህይወት ታሪኩ ላይ ተጠቁሟል፡፡ በአሜሪካ ቆይታው እስከ ህይወቱ ፍፃሜ ድረስ ከንባብና ከጋዜጠኝነት ህይወቱ ተላቆ እንደማያውቅ ተገልጿል፡፡ ከህይወት ታሪኩ መረዳት ተችሏል፡፡

Read 1233 times