Saturday, 03 October 2015 10:49

“ሶስት ማዕዘን” ፊልም በሶስት ዘርፍ አሸናፊ ሆነ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

 “ሶስት ማዕዘን” ፊልም በደቡብ አፍሪካ በተዘጋጀ “African Movie Academy Award” (AMAA) በሶስት ዘርፍ አሸናፊ ሆኖ መሸለሙን የሴባስቶፖል ኢንተርቴይንመንት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ቴዎድሮስ ተሾመ ገለፀ፡፡
በልቦለድ ፊልሞች በስምንት ዘርፍ ታጭቶ የነበረው ፊልሙ፤ በሁለቱ ዘርፎች ማለትም፡- በ”ምርጥ ረዳት አክተር” እና በ”ምርጥ ሳውንድ ትራክ” ያሸነፈ ሲሆን በሽልማት ስነ - ስርዓቱ ላይ ምርጥ ረዳት ዳይሬክተሩ ሳምሶን ታደሰ (ቤቢ) እና የማጀቢያ ሙዚቃውን የሰራው ድምፃዊ ጌትስ ማሞ በደቡብ አፍሪካ የሽልማት ስነስርዓት ላይ ተገኝተው ሽልማቱን እንደተቀበሉ ተጠቁሟል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ፊልሙ “Special Jury Prize for Best Film” በሚለው ዘርፍም በ11ዱም ዳኞች ስምምነት አሸናፊ በመሆን ሦስተኛውን ሽልማት ለማግኘት እንደቻለ የፊልሙ ዳይሬክተር አርቲስት ቴዎድሮስ፤ ላፍቶ ሞል በሚገኘው ሴባስቶፖል ሲኒማ ውስጥ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግሯል፡፡
 ፊልሙ ከዚህ ቀደም በፓን አፍሪካን ፊልም ፌስቲቫል እንዲሁም ከ3 ወራት በፊት በሩዋንዳ “ቤስት ኦዲየንስ ፊልም አዋርድ” ላይ አሸናፊ እንደነበር ይታወቃል፡፡
በቀጣይም በስዊዘርላንድ በሚካሄድ አንድ የፊልም አዋርድ ላይ “ሦስት ማዕዘን” እጩ ሆኖ መጋበዙም ተገልጿል፡፡ ፊልሙም እንደገና ለህዝብ እይታ እንደሚቀርብ የገለፀው ቴዎድሮስ፤ የ”ሦስት ማዕዘን” ሁለተኛ ክፍልም በቅርቡ እንደሚመረቅም ጠቁሟል፡፡
ሴባስቶፖል ኢንተርቴይመንት በቅርቡ “ዊንታና” የተሰኘና ሌላም አዲስ ፊልም ለእይታ እንደሚያቀርብ ታውቋል፡፡

Read 2597 times