Saturday, 03 October 2015 10:25

በሐዋሣ ሂልተን ኢንተርናሽናል ሆቴል ሊገነባ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ከ5 ዓመት በኋላ ግንባታው ተጠናቆ ሥራ ይጀምራል
                       
     ሂልተን ኢንተርናሽናል ከአዲስ አበባ ውጪ የመጀመሪያውን ሂልተን አለማቀፍ ሪዞርት እና ስፓ ግንባታ በዚህ አመት የሚጀምር ሲሆን የስራ አስተዳደር ስምምነትም ከሰንሻይን ቢዝነስ ጋር ሰሞኑን ተፈራርሟል፡፡
በስምምነት ፊርማ ስነስርአቱ ወቅት እንደተገለፀው፤ የሪዞርትና ስፓ ግንባታው በሐዋሳ ከተማ በሐይቁ ዳርቻ በያዝነው አመት በ840 ሚሊዮን ብር ገደማ ይጀመራል፡፡ ከ5 አመት በኋላ በ2013 ዓ.ም ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡
እስከ አሞራ ገደል ብሔራዊ ፓርክ ድረስ በሚገኘው የሃይቁ ዳርቻ ላይ ይገነባል የተባለው ይህ አለማቀፍ ሪዞርትና ስፓ 169 ክፍሎችና ቪላዎች የሚኖሩት ሲሆን፣ በተጨማሪም የውጪ መዋኛ እና የስፓ ማዕከሎቹ የሪዞርቱ ልዩ መለያ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
ሂልተን አለማቀፍ እና ሰንሻይን ቢዝነስ ሰሞኑን በሂልተን አዲስ አበባ የስምምነት ፊርማ በተፈራረሙበት ወቅት እንደተገለፀው የዋና ገንዳ ዙሪያ ባር እና ግሪል ያለው ልዩ ሬስቶራንትን ጨምሮ የአራት የተለያዩ አገራት የምግብ ምርጫዎች ያላቸው ሬስቶራንቶች ይኖሩታል ተብሏል፡፡
ሆቴሉ ከስድስት የስብሰባ አዳራሾች በተጨማሪ ከ1ሺህ ካ.ሜትር በላይ የሆነ አዳራሽ እንደሚኖረውም ተገልጿል፡፡
በስምምነት ፊርማው ወቅት የሂልተን አለማቀፍ የአውሮፓ እና የአፍሪካ የልማት ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት ፓትሪክ ፊትዝጊቦን፤ “ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበ ባለሙ ክልል ውስጥ ሆቴሉ መከፈቱ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ለሚጓዙ ጐብኚዎች መልካም አጋጣሚ ይሆናል” ብለዋል፡፡
የሰንሻይን ቢዝነስ ባለቤት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ በበኩላቸው፤ “ከሂልተን አለማቀፍ ጋር በመሆን የመጀመሪያውን አለማቀፍ ስም ያለው ሆቴል ወደ ታዋቂዋ የቱሪስት መዳረሻ ሃዋሣ በማምጣታችን ደስተኛ ነን” ብለዋል፡፡
በ55 ሚሊዮን ዶላር ስራው ከ3 አመት በኋላ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው የሃዋሣ አውሮፕላን ማረፊያ እና የአዲስ አበባ ሞጆ ሃዋሣ የፍጥነት መንገድ መሠረተ ልማቶች ወደ ሃዋሣ የሚደረገውን የቱሪስት ፍሰት ከፍ እንደሚያደርጉት ይጠበቃል፡፡
የ96 ዓመት እድሜ ያስቆጠረው ሂልተን፤ የሆቴሎችና ሪዞርቶች አገልግሎት በ82 አገራት በሚገኙ 550 ሆቴሎች እየሰጠ ሲሆን ወደ አፍሪካ ከገባም ግማሽ ክ/ዘመን (50 አመት) ሆኖታል፣ በቅርቡም የወርቅ ኢዮቤልዮ በዓሉን ያከብራል ተብሏል፡፡
እስካሁን በአፍሪካ የተለያዩ ሀገራት 70 አለማቀፍ የሂልተን ሆቴሎች በግንባታና በአገልግሎት ላይ ሲሆኑ በአጠቃላይ 22ሺህ የመኝታ ክፍሎችም እንዳሉት ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 1565 times