Saturday, 03 October 2015 10:09

የዩኒቨርስቲው በር ተሰብሯል! ዐምዶቹም ተነቃንቀዋል!

Written by  ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ (የአ.አ ዩ የቀድሞ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(15 votes)


 የፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ ገጽታ፣ ከኹለት ትረካዎች አንጻር ሲፈተሽ
ካለፈው የቀጠለ
ከአዘጋጁ
ባለፈው ሳምንት ዶ/ር ዳኛቸው በጽሁፋቸው በአራት የተከፈሉ ርዕሰ ጉዳዮችን እንደሚዳስሱ ቢጠቁሙም በቦታ ጥበት የተነሳ ያወጣነው ሁለቱን ብቻ ነበር፡፡ ለማስታወስ ያህልም አንደኛው፡- ስለ ዩኒቨርስቲ አጠር ያለ መሠረታዊ ሐሳብ እና የአካዳሚያዊ ነጻነት መርሖዎች ሲሆን ኹለተኛው፡- የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመንግሥት መዳፍ ሥር ስለ መውደቅ በሚል ቀርቧል፡፡ ዛሬ ሦስተኛው፡- የፕሬዝዳንት ዶ/ር አድማሱ ጸጋዬን ገጸ ሰብእና (persona) በኹለት ወጎች ሥር ማብራራት እና አራተኛው፡- የርእሰ ጉዳዮቹ ማጠቃለያ ይቀርባል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
፫.
 የፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ ገጽታ፣ ከኹለት ትረካዎች አንጻር ሲፈተሽ
ፕሬዝዳንት አድማሱ ለአራት ዓመታት የዩኒቨርስቲው የበላይ አመራር ኾነው በቆዩባቸው ጊዜያት፣ እኔም እንደ አንድ የዩኒቨርስቲው ማኅበረሰብ  አባል ኾኜ በማገለግልበት ወቅት ስለ ሰውዬው ያየኹትንና የታዘብኩትን ጉዳይ በሚከተሉት ወጋዊ ትረካዎች ለማቅረብ እሞክራለኹ፡፡ ይህንንም ለመተግበር ፕሬዝዳንቱ በተለያዩ ወቅቶች በዩኒቨርስቲው ውስጥ ካደረጉት ንግግር፤ በየጊዜው የዩኒቨርስቲውን አስተዳደርና ሒደት በሚመለከት ጽፈው ወደተለያዩ የትምህርት ክፍሎች በላኳቸው ሰነዶች እናም በመጨረሻም ዩኒቨርስቲው ልማታዊ ወይም ተግባራዊ መንገድ ይዞ መጓዝ አለበት ብለው ደጋግመው ካቀረቡት ዕቅድ በመነሣት ነው፡፡
ሀ. ፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ እና የካውንት ሌቭ ቶልስቶይ ጀነራል
ከዚህ የሚከተለውን ትረካ የወሰድኩት፣ ከሌቭ ቶልስቶይ “ጦርነት እና ሰላም” ከሚለው ታላቁ ድርሳን ነው፡፡ ለአንባብያን እንዲመች ለማድረግ ሐሳቡ ላይ ትኩረት በመስጠትና በማገናዘብ እንደሚከተለው አቀርባለኹ፡፡
የታሪኩ መቼት፣ በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን “የናፖልዮኒክ ጦርነት” ተብሎ በሚጠራውና ናፖሊዮን ቦናፓርት ሩስያን ወርሮ ለመያዝ ባካሔደው ጦርነት ወቅት ነው፡፡ የፈረንሳይ ሠራዊት በዚያን ጊዜ በጦርነት ዐውድማ ማንም ተፎካካሪ ኃይል ስላልነበረው፣ የወረራ አቅጣጫውን ወደ ሩስያ ባደረገበት ወቅት ትልቅ መደናገጥንና ፍርሀትን በመላው ሀገሪቱ አሳደረ፡፡
የወራሪውን ሠራዊት ለመቋቋም በአንድ የተወሰነ ግንባር ያሉ የሩስያ  ጀነራሎች የመከላከል ዕቅድ ለመንደፍና በአጠቃላይ የጦርነት ስልት ለማዘጋጀት ስብሰባ አድርገው ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ከቶልስቶዩ ጀነራል በስተቀር ኹኔታውን በጥሞና በመከታተል የተቻላቸውን የሐሳብ አስተዋፅኦ ለማበርከት ሞክረዋል፡፡ በአንጻሩ ግን ጀነራሉ ስለ ውጊያው ስትራቴጂ የበኩሉን ድርሻ ማቅረብ ከመዘንጋቱም በላይ የጉዳዩ ክብደት ሳያሳስበው እያንቀላፋ ነበር፡፡ የጀነራሎቹ ስብሰባ አልቆ ኹሉም የድርሻቸውን የውጊያ ሚና ከተከፋፈሉ በኋላ ተለያዩ፤ ጀነራሉም የተወሰነ ድርሻውን በሓላፊነት ተረክቦ ወደ አንደኛው ግንባር ተላከ፡፡
በበነጋው ይኼው ጀነራል የዕዙን ወታደሮች ይዞ ከጦር ሜዳው ደረሰ፡፡ በሥሩ ያሉት መኮንኖች ጦሩን ቦታ ቦታ ካስያዙ በኋላ ፍልሚያ ሊጀምር ትንሽ ሲቀረው ጀነራሉ ከቦታው ተሰወረ፡፡ አብረውት የነበሩት የጦር አመራሮች በመገረም የጀነራሉ ምክትል ዕዙን ተረክቦ እንዲመራ በመስማማት በጣም ከከረረ ውጊያ በኋላ ሩስያውያኑ ድል ቀንቷቸው የወራሪውን ኃይል ለመመለስ ቻሉ፡፡
ከጦርነቱም በኋላ ባገኙት ድል በመደሰት፣ ሞቅ ያለ ግብዣ ተደርጎ በትልቅ ድግስ ላይ እንዳሉ ጀነራሉ በነጭ ፈረስ ላይ ኹኖ ከግብዣው አካባቢ ብቅ አለ፡፡ ይህን ያዩ መኮንንኖች ወደርሱ ቀርበው፣ “በጣም የምታስገርም ሰው ነህ፡፡ ከትላንት ወድያ የጦርነቱን ፕላን ስናወጣ፣ አንተ ታንቀላፋ ነበር፤ ትላንት ጧት ደግሞ እንድታዋጋ ተሰጥቶኽ ከነበረው ግንባር ተሰወርክ፡፡ እንደዚህ ዐይነት ድርጊት ወደ ጦር ፍርድ ቤት እንደሚያስወስድኽና ከፍተኛ ቅጣት እንደሚያሰጥኽ ማወቅ ይኖርብሃል፡፡” በማለት በቁጣ ተናገሩት፡፡
ጀነራሉ፣ ተናደው በቁጣ ላናገሩት መኮንኖች የሚከተለውን መልስ ሰጣቸው፡፡ “ከኹሉ አስቀድሞ ንዴታችኹ ይገባኛል፡፡ ኾኖም ግን አንድ ለናንተ የተሰወረና እኔ ደኅና አድርጌ የማውቀው ጉዳይ አለ፡፡ ይኸዉም ከእናንተ ይበልጥ እኔ ራሴንና  ማንነቴን ጠንቅቄ ስለማውቅ ነው፡፡ እኔ የጦርነቱ ፕላን ሲወጣ ሙሉ ለሙሉ ተካፋይ ብኾን ኖሮ፣ ዛሬ ድል ከእናንተ ጋር አትኾንም ነበር፡፡ ትላንትናም ቢኾን በጦር ሜዳው ግምባር ዋናው አዋጊ ብኾን ኑሮ ከድል ይልቅ ዕጣችኹ እንዲኽ አያምርም ነበር፡፡ ዐያችኹ፤ ከኔ ይልቅ ምክትሎቼ የተሻሉ አዋጊዎች ናቸው ብዬ ስላመንኩ ሓላፊነቱን ለእነሱ ትቼ ዘወር አልኩ፡፡ በእኔ ዐተያይ ሀገር መውደድ ማለት የራስን አቅም ሳይፈትሹ፣ አደርገዋለኹ በሚል ድፍረት መንቀሳቀስ ሳይኾን የራስን ችሎታና አቅም በሚገባ አጢኖ፣ የተሻለ ሰው ከተገኘ የሥራ ምድቡን ለቆ ጥሩ ውጤት እንዲገኝ ለሀገርና ለወገን ሲባል ከቦታው ዘወር ማለት ነው፡፡”
በዚህ ትረካ ያየነው፣ የቶልስቶዩ ጀነራል ችሎታ ባይኖረውም ሀገሩን የሚወድና  የሞራል ላቂያ ያለው ሰው ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ በእሱ አስተያየት፣ ሀገር መውደድ ማለት ከኹሉ አስቀድሞ ችሎታም ባይኖር የያዙትን ሹመት የሙጥኝ ብሎ አልለቅም ከማለት ለተሻለ ሰው ቦታውን መልቀቅ ማለት ነው፡፡
ወደ ፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ ስንመለስ፤ ራሳቸውን ከማወቅ አንጻርም ኾነ ለያዙት ቦታ ከእርሳቸው የተሻለ፣ እዚኹ ግቢ ውስጥ፣ በርከት ያለ ሰው መኖሩን እያወቁ እንደ ቶልስቶዩ ጀነራል ዘወር አለማለታቸውን ስንታዘብ፣ ስለ ራሳቸው የተሳሳተ ግምት  እንዳላቸውና ሀገር ወዳድነታቸውን ትልቅ ጥያቄ ውስጥ እንደሚያስገባ መገንዘብ ይኖርባቸዋል ብለን እናስባለን፡፡
ምናልባት በዚህ ድምዳሜ ላይ ፕሬዝዳንቱ፣ ሀገሪቱን በበላይነት ከሚያስተዳድሩት ውስጥ ለሥራቸው የማይመጥኑ መኖራቸው እየታወቀ፣ ምነው እኔ ብቻ ተነጥዬ ቦታህን ለሚችል ሰው ልቀቅ መባሌ፤ ብለው ይጠይቁ ይኾናል፡፡ ጥያቄያቸው የተወሰነ እውነታ አለው፡፡ ኾኖም ግን፣ በሀገራችን የቅርብ ታሪክ ውስጥ ለሀገርና  ለወገን ሲሉ ቦታቸውን የለቀቁ እንዳሉ ታሪክ ያስተምረናል፡፡ አምባሳደር ዘውዴ ረታ፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት በሚለው አስደማሚ መጽሐፋቸው ላይ ስለ ቦታ መልቀቅ የሚከተለውን ታሪክ ያጫውቱናል፡፡
ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሩዝቬልት፣ የአፍሪካን የግብርና ሚኒስትሮች በአጠቃላይ ወደ አሜሪካ መጥተው እንዲወያዩ  የስብሰባ ጥሪ አቀረቡ፡፡ በጊዜው የኢትዮጵያ የግብርና ሚኒስቴር የነበሩት አቶ መኮንን ሀብተ ወልድ ቢኾኑም ከሩዝቬልት ጋር ተገናኝቶ ስለ እርሻ ብቻ ሳይኾን እንግሊዞችን ከኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ ለማውረድ ትብብራቸውን እንዲለግሱ ለመጠየቅ ታስቦ ነበር፡፡ ለዚህ ሥራ ብቁ የሚኾኑት ከአቶ መኮንን ይልቅ አቶ ይልማ ደሬሳ መኾናቸውን አቶ መኮንን ሀብተ ወልድ ከወንድማቸው ከአቶ አክሊሉ ሀብተ ወልድ ጋር ተመካክረው፣ ሐሳቡን ለጃንሆይ አቅርበው በማስወሰን አቶ ይልማ ደሬሳ ሔደው ከሩዝቬልት ጋር በመነጋገር፣ ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ እመርታ አግኝተው ተመልሰዋል፡፡
ለ. ፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ እና የፕሌቶ ምግብ አብሳዮች “ሐኪሞች በሌሉበት ምግብ አብሳዮች የጤና አማካሪ ኾነው ብቅ ይላሉ፡፡”
(ፕሌቶ)
ፕሌቶ “ሪፐብሊክ” በሚለው መጽሐፉ፣ ከሙያቸው ውጭ ጣልቃ እየገቡ ችግር ስለሚፈጥሩ ሰዎች በሚከተለው ትረካ ለማስረዳት ሞክሯል፡፡
አልፎ አልፎ ትልቅ ግብዣ በሚካሔድበትና ተጋባዡ ቦታ ቦታውን ይዞ በሚታደመበት አዳራሽ ውስጥ ምግብ የሚያበስሉ ወጥ ቤቶች፣ እንግዶቹ ወዳሉበት ሥፍራ በመሔድ፣ ራሳቸውን እንደ ሕክምና ባለሞያ በመቁጠር የጤና አማካሪ ኾነው ይቀርባሉ፡፡ በመኾኑም ከጠረጴዛ ወደ ጠረጴዛ በመዞር “ይቺን ብትበላ ትስማማኻለች፤ ይኼኛውን ምግብ ብዙ አትድፈር፤ በተለይ ደግሞ ይህ ዐይነቱ ምግብ ለደም ብዛትና ለኩላሊት ፈውስ ነው፤” ወዘተ  የሚል ምክር ይለግሳሉ፡፡ በእንዲህ ዐይነት ከሙያቸው የራቀ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳሉ ወደ ግብዣው ቦታ እውነተኞቹ ሐኪሞች ወይም ዶክተሮች ብቅ ሲሉ ወጥ ቤቶቹ ወደ መደበኛ ሥራቸው ይመለሳሉ፡፡
የፕሌቶ ምግብ አብሳዮች ሐኪም መስለው መቅረባቸው ጥፋተኛ ቢያሰኛቸውም እውነተኞቹ ሐኪሞች ሲመጡ ቦታውን ለቀው ወደ ማዕድ ቤት መመለሳቸው በእጅጉ ያስመሰግናቸዋል፡፡ ከዚህ ትረካ ስንነሣ የፕሌቶ ምግብ አብሳዮች እንደ ቶልስቶዩ ጀነራል ለተሻለ ሰው ቦታ መልቀቃቸውን እንገነዘባለን፡፡
ከሙያና ችሎታ ዉጭ ቦታን መያዝ በተመለከተ፣ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ዕውቁ የአሜሪካን ፈላስፋ ዊሊያም ጀምስ፣ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፤ “ለእኔ የተሰጠኝን አብዛኛውን የሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት መመረቂያ ጽሑፍ ባነበብኩ ጊዜ፣ ይህች ሀገር ስንት ገበሬ እንዳጣች ሳስብ አዝናለሁ፡፡” አሉ፡፡ እኔም የፕሬዝዳንት አድማሱን ኹኔታ ሳስብ፣ሰውዬው አለቦታቸው ሳይገቡ በሙያቸው ተሰማርተው፣ የጀመሩትን የግብርና ምርምር ቢቀጥሉ ኖሮ፣ ሀገሪቱ ከረኀብ ለመውጣትና በምግብ እህል ምርት ራሷን ለመቻል ታደርገዋለች ለሚባለው ተጋድሎ የተሻለ አስተዋፅኦ ይኖራቸው ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡

ማጠቃለያ
ጹሑፋችንን የምናጠቃልለው በሚከተሉት ሁለት ጉዳዮች ዙርያ አጠር ያሉ ነጥቦችን በማንሣት ነው፡፡ እነዚህንም ነጥቦች “ዕውቀት” እና “እብሪት” በተሰኙ ሁለት አርእስት ከፍለን እናቀርባለን፡፡
ሀ. ዕውቀት
የአንድ ዩኒቨርስቲ ከፍተኛ አመራር ለመኾን የሰውዬው ወይም የሴትዬዋ የዕውቀት ደረጃ በእጅጉ ከፍ ያለ መኾን አለበት፡፡ የዛሬ ኃምሳ ዓመት ገደማ በአሜሪካን ሀገር በምሁራኑ አካባቢ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት  የሚኾን ሰው ምን ዐይነት መሥፈርት ማሟላት አለበት? አንድንስ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ብቁ የሚያሰኘው ነገር ምንድር ነው? ፕሬዝዳንትን ለመሠየም የሚያስችሉ ሰፋ ያለ ተቀባይነት ያላቸውን መመዘኛዎች ማስቀመጥ ይቻላል ወይ? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በማንሣት፣ ረዘም ላሉ ጊዜያት ከተወያዩ በኋላ አምስት ወይም ስድስት መሥፈርቶችን ለይተው አወጡ፡፡
ከተስማሙባቸው ወሳኝ ነጥቦች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱት፣ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ከኹሉም በላይ የተጠናከረ ምሁራዊ ዝንባሌና ርእይ ያለው መኾን እንዳለበት፤በኹለተኛ ደረጃ የአመራርና የአስተዳደር ችሎታ ያለው መኾን እንደሚገባው ካቀረቡ በኋላ ሌላው ነጥባቸው፣ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ባለትዳርና  ቤተሰብ ያለው ቢኾን ይመረጣል የሚል ነው፡፡
ፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ፤ የአሜሪካን ምሁራን ለፕሬዝዳንትነት አስፈላጊ ናቸው ብለው ከዘረዘሯቸው መሥፈርቶች ውስጥ፣ በእኔ አተያይ፣ ባለትዳር ቢኾን ይመረጣል ያሉትን መለኪያ ብቻ የሚያሟሉ ይመስለኛል፡፡   
ፕሬዝዳንቱ ጠንካራ ምሁራዊና የአስተዳደር ክህሎት ስለሚጎድላቸው፣ ዩኒቨርስቲው የራሱን ዕቅድ ነድፎ፣ እንደ አንድ አካዳሚያዊ ተቋም ከመተግበር ይልቅ ከመንግሥት ሥራ እየተቆጠረ የሚሰጠው ኾኗል፡፡  
ስለኾነም ፕሬዝዳንቱ ምንጊዜም የመንግሥትን ፖሊሲና ፕላን ወደ ዩኒቨርስቲ አምጥተው ማስፈጸም ስለሚፈልጉ፣ አኹን ባለበት ኹኔታ የጥናትና ምርምር ማእከል መኾኑ ቀርቶ፣ “ልማታዊ ዩኒቨርስቲ” ተብሎ እስከ መጠራት ደርሷል፡፡ እዚህ ጋ እንደ ማሳያ ለማቅረብ የምፈልገው፣ ከስድስት ወራት በፊት ጋዜጠኞችን ሰብስበው በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሲሰጡ፤ለዩኒቨርስቲው እንደ ርእይና እንደ ግብ አድርገው ካቀረቧቸው አንዱ፣ የበሬ ማድለብን ፕሮጀክት ነው፡፡ እዚህ ላይ በጣም የሚያስገርመው፣ አንድ ዩኒቨርስቲ በዋናነት የአእምሮ ማድለቢያ እንጂ የበሬ ማድለቢያ እንዳልኾነ ብዙ ሰዎች ያውቁታል፡፡ እርሳቸው ግን ይህን መሳታቸው ከግል ድክመት የመነጨ ሳይኾን ወደ እውነተኛ የሙያ ጥሪያቸው ከማዘንበል የተነሳ ነው፡፡ባለፉት አራት ዓመታት ያደረጓቸውን ንግግሮች ያዳመጠ ሰው ሊስተው የማይችለው ነገር ቢኖር፣ ፕሬዝዳንቱ ኹልጊዜም ሪፖርት አቅራቢ ኾነው መገኘታቸው ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ዩኒቨርሲቲው እንዴት ካለፉት ዓመታት ዘንድሮ የተማሪውን ቅበላ እንዳሳደገ፤ ምን ያህል ዐዲስ ሕንፃዎች እንደ ተሠሩ፤ ስንት የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች እንደገቡ፤ ስንት ዐዲስ የትምህርት ክፍሎች እንደተከፈቱ… ወዘተርፈ በቁጥር ማቅረብ ነው፡፡ እንደዚህ ዐይነት ዘገባዎች፣ በዩኒቨርስቲው የሕዝብ ግንኙነት ወይም በየትምህርት ክፍሉ ሊቀርብ ሲችል የፕሬዝዳንቱ ተቀዳሚ ሥራ ኾኖ መገኘቱ በእጅጉ አስገራሚ ነገር ነው፡፡
በመጨረሻም ፕሬዝዳንት ኾነው ባገለገሉባቸው ጥቂት ዓመታት፣ የተለያዩ ጥያቄዎች ወደ እርሳቸው በሚቀርብበት ጊዜ ቶሎ ብሎ የሚቀናቸው፣ ጉዳዩ በኮሚቴ እንዲታይ ማድረግ ነው፡፡ አንዳንድ ጉዳዮችን በኮሚቴ ማየቱ ተገቢ ቢኾንም የቀረበውን ጥያቄ ኹሉ ወደ ኮሚቴ ማስተላለፍ፣ በራስ ያለመተማመንና ሓላፊነትን ለመሸሽ የሚደረግ አዝማሚያ መስሎ ይታያል፡፡ ለማሳያ ያኽል፣ በቅርቡ የሪፖርተር ጋዜጠኛ፣ “የክብር ዶክትሬት ለመጠሪያነት ይውላል ወይ?” በሚል ለጠየቃቸው ሲመልሱ፤“በእኔ እምነት ይቻላል፤ ነገር ግን መጠራት ይቻላል ወይስ አይቻልም ለሚለው ጉዳይ የመጨረሻ ዕልባት ለመስጠት እንዲረዳ ኮሚቴ አቋቁመን እንዲወሰን እናደርጋለን፡፡” በማለት መልሰዋል፡፡
ለ. እብሪት
እብሪት ብቻውን የሚከሠት ነገር አይደለም፡፡ ዕውቀት በሌለበት ቦታ፣ ንዋይ በበዛበት መንደር እብሪት መፈልፈሏና ማበቧ አይቀርም፡፡ በተጨማሪም አንድ ሰው ያልኾነውን ነገር መኾን ሲከጅል፣በእብሪት አዙሪት ውስጥ ይወድቃል፡፡ ጥንታውያኑ የግሪክ ጸሐፍት እብሪትን ሲገልጹት፣ ከአማልክቱ ጋር ለመወዳደር መሻት ነው ይሉታል፡፡ ይህ ውድድር በመጨረሻም  ለእብሪተኛው ውድቀት ይኾነዋል፡፡ የፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ እብሪቶች፣ በተለያዩ ጊዜያት የታዩ ቢኾንም፤ በእኔ ላይ የደረሰውን እብሪታዊ ድርጊት እንደ ማሳያ ልጥቀስ፡፡ ለሰባት ተከታታይ ዓመታት በዩኒቨርስቲው ላስተማርኩበት የጠየቅኹት የሰባቲካል ፈቃድ ስለተነፈገኝ፣ ሥርዓቱንና ዕርከኑን ጠብቄ ቅሬታዬን ለፕሬዝዳንቱ አቀረብኩ፡፡ ነሐሴ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ላስገባኹት በርካታ የሰነድ ማስረጃዎች ያሉት አቤቱታ በማግስቱ፣ ነሐሴ 23 ቀን 2006 ዓ.ም.፣ “በጥልቅ መርምረን እንዳረጋገጥነው፣ የኮሌጁ ውሳኔ የሚለወጥበት ምክንያት የለም” የሚል መልስ በቆራጣ ደብዳቤ ላኩልኝ፡፡ የእብሪቱ ጫና ባይኖርና እንደ ደንቡ ቢኾን ኖሮ፣ ከትምህርት ክፍሉ ጀምሮ እስከ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ድረስ ያሉትን ሓላፊዎች እንዲኹም የሕግ አማካሪዎቻቸውን ሳያማክሩና በማስረጃነት ያቀረብኳቸውን ሰነዶች ሳይመረምሩ በሰዓታት ውስጥ ባልወሰኑ ነበር፡፡

Read 5239 times Last modified on Saturday, 03 October 2015 14:25