Saturday, 03 October 2015 09:53

የመንግስትና የግል ሚዲያዎች የአመለካከትና የክህሎት ችግሮች አለባቸው ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(27 votes)
  • የመንግሥት ሚዲያዎች “የመንግሥት ቃል አቀባይ” ከመሆን የዘለለ ተግባር የላቸውም
  • አድርባይነትና የመንግሥት ልሳንነት በመንግስት ሚዲያዎች ላይ ጐልቶ ይታያል
  • ፅንፈኛ የግል ሚዲያዎች መንግሥትን መለወጥ ግባቸው አድርገው የተነሱ ናቸው

   በአገሪቱ የሚገኙ የመንግሥትና የግል ሚዲያዎች የአመለካከት፣ የክህሎትና የአደረጃጀት ችግር እንዳለባቸው የተጠቆመ ሲሆን በህዝቡ ዘንድ ተአማኒነትን እያጡ እንደሆነም ተገለፀ፡፡በአገሪቱ ተፅእኖ ፈጣሪ ሚዲያ ለመገንባት ባሉ ፈተናዎችና መፍትሄዎች ላይ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ለሁለት ቀናት ባዘጋጀውና በትናንትናው እለት በጁፒተር ሆቴል በተከፈተው የሁለት ቀናት ሲምፖዚየም ላይ እንደተገለፀው፤ የአገሪቱ ሚዲያዎች ላይ የተአማኒነት ቀውስ እንደሚታይና ሚዲያው ከጠንካራነት ወደ አቅመቢስነት እያመራ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የመንግሥት ሚዲያዎች የመንግሥትን ፖሊሲ በራሱ በመንግስት ቋንቋ ከማቅረብ ውጪ ህዝቡ ጉዳዩን እንደራሱ እንዲቀበለው አድርጐ በማቅረብ ረገድ ደካማ እንደሆኑና የክህሎትና የአመለካከት ችግር በስፋት እንደሚታይባቸው ተገልጿል፡፡
በመንግሥት ሚዲያዎች በአመራርነት ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች የዘመናዊ ሚዲያ ማኔጅመንት ክህሎትና ልምድ እጥረት ያለባቸው ሲሆን ጋዜጠኞቹም የሙያ ብቃት ማነስ እንደሚታይባቸው ተገልጿል፡፡ አድርባይነትና የመንግሥት ልሳንነት፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ላይ ጐልቶ እንደሚታይ ጥናቱ አመልክቷል፡፡ የመንግሥት ሚዲያ ባለሙያዎች የህዝባዊ ወገንተኝነት ችግር እንዳለባቸው የገለፀው ጥናቱ፤ የመንግሥት ሚዲያው የመንግሥት ልሳንነቱ የበዛ፣ የህዝቡን ብሶት የመቀበል አቅሙ ደካማ የሆነና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ፈትሾ በማቅረብ ረገድ የአቅም ውስንነት እንደሚታይበት ተገልጿል፡፡
በግል ሚዲያዎች ላይ የሚታዩ ችግሮች ተብለው ከተገለፁት መካከል ለዘብተኝነትና ፅንፈኝነት ተጠቅሰዋል፡፡ ለዘብተኛ የግል ሚዲያዎች ሚዛናዊ የመሆን ሙከራ ሲኖራቸው ፅንፈኛ የግል ሚዲያዎች ደግሞ መንግሥትን መለወጥ ግባቸው አድርገው የተነሱና ለፖለቲካዊ ተልእኮ ማስፈፀሚያነት የተመሰረቱ ናቸው ብሏል - ጥናቱ፡፡
ሚዲያን እንደ መንግስት መገልበጫ አድርጐ ማሰብና ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር በግል ሚዲያዎች ላይ በስፋት እንደሚታይ ጠቁሞ ይሄም ለፕሮፌሽናል ጋዜጠኝነት ቦታ መንሳቱን ገልጿል፡፡
እነዚህን ችግሮች በማስወገድ ሚዲያው ኃላፊነት ባለው መልኩ ሙያዊ ተግባሩን እንዲወጣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅበታል ያለው ጥናቱ፤ መንግስት የመረጃ ነፃነትን ማረጋገጥ፣ የሚዲያ ተቋማትን እንደ ሁነኛ የህዝብ ድምፅ ማዳመጫ መቁጠርና በሚዲያው ለሚዘግቡና የመንግሥትን ውሳኔ ለሚፈልጉ ጉዳዮች አፋጣኝና ቁርጠኛ እርምጃ መውሰድ ይገባዋል ብሏል፡፡የሚዲያ ባለሙያዎችም አቅማቸውን በማጐልበት፣ ስራቸውን ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ሊወጡ እንደሚገባም ተገልጿል፡፡ ፖሊስና ፍርድ ቤት በጋዜጠኞች ላይ የማሰር ስልጣናቸውን እንደልባቸው እንዳይተገብሩ የሚያደርግ የተለየ የህግ ጥበቃ እንደሚያስፈልግም በጥናቱ ተገልጿል፡፡
ውይይቱ ዛሬም የሚቀጥል ሲሆን የግል ሬዲዮና የማህበረሰብ ሬዲዮ ስለሚስፋፋበት፣ የግል የቴሌቭዥን ፈቃድ አሰጣጥ፣ በብሮድካስት ሚዲያዎች ላይ ስለሚሰራጩ ማስታወቂያዎችና የህትመት ሚዲያው ስለሚጠናከርበት ሁኔታ ሰፋ ያለ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Read 3387 times