Saturday, 03 October 2015 09:50

የኢሳያስ እናት የ“ባላገሩ ምርጥ”ን ዳኝነት ተችተዋል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(13 votes)

“60 በመቶ ለተመልካች የተሰጠው ዳኝነት ልጄን ጐድቶታል” የኢሳያስ እናት
• “በባላገሩ ውድድር እዚህ ደረጃ መድረሴ ትልቅ እድል ነው” - ቢኒያም እሸቱ
• “በዳኞች ውጤት ኢሳያስና ዳዊት እኩል ነጥብ ላይ ነበሩ” - አረጋኸኝ ወራሽ
• “የአብርሃም ወልዴ መታመም በግሌ ጐድቶኛል - ባልከው ዓለሙ

የባላገሩ አይዶል አዘጋጅ አብርሃም ወልዴ ለመጨረሻ ውድድር የሚቀርቡትን የባላገሩ ምርጥ የድምፅ ተወዳዳሪዎች ሲመክር፤ “ጉንፋን እንኳን እንዳይዛችሁ መጠንቀቅ አለባችሁ” ብሎ ነበር፡፡ ለተወዳዳሪዎቹ ተጨንቆ እንዲጠነቀቁ ሲመክራቸው የከረመው አብርሐም ወልዴ ግን በማጠናቀቂያው ዝግጅት ላይ ራሱ ታሞ መምጣቱ የብዙዎቹን አንጀት በልቷል፡፡
ባለፈው የመስቀል በዓል በሚሊኒየም አዳራሽ የተካሄደው የመጨረሻ የባላገሩ ምርጦች ውድድር ከፍተኛ ፉክክር በታየበት ሁኔታ በድምቀት ተጠናቋል፡፡ በዳኝነቱና በውጤት አሰጣጡ ላይ ከዚህ ቀደም እንደነበሩ ውድድሮች ከፍተኛ ውዝግብ ባይነሳም የተወሰኑ ተቃውሞና ትችቶች መፍጠሩ አልቀረም፡፡
በድምፅ ውድድር ሁለተኛ የወጣው ኢሳያስ ታምራትን ለማነጋገር ሰሞኑን ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ ወደሚገኘው ቤቱ ብንሄድም በአካል ልናገኛቸው አልቻልንም፡፡ በስልክ ስናነጋግረውም በውጤቱ ዙሪያ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆነ ገልፆልናል፡፡
የኢሳያስ እናት ወ/ሮ አልማዝ ተሰማ ግን በልጃቸው ውጤት ዙሪያ ያልጠበቅነውን የሰላ አስተያየት ሰነዘሩ፡-
“ልጄ በተሰጣቸው ዜማም ሆነ በግሉ በዘፈነው ምንም እንከን አይወጣለትም፤ አንደኛ መሆን ሲገባው ሁለተኛ መሆኑ እኔንም ሆነ የአካባቢዬን ሰዎች ሀዘን ላይ ጥሎናል” ያሉት ወ/ሮ አልማዝ፤ “ውድድሩ ብቃት ባላቸው ዳኞች እየተመራ 60 በመቶ ለተመልካች መሰጠቱ ልጄን በእጅጉ ጐድቶታል” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡ እስካሁን በተካሄዱት ውድድሮች ዳኞቹ “የሴት፣ የወንድ፣ የሽማግሌና የወጣት ዘፈን ለመዝፈን የተመቸ ድምጽ ሰጥቶሃል” እያሉ ኢሳያስን ሲያሞካሹት እንደነበር ያስታወሱት  እናቱ፤ ልጃቸው በቲፎዞ ብዛት እንጂ በችሎታው እንዳልተበለጠ እርግጠኛ መሆናቸውን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
“ከዱባይ ድረስ እየተመላለሰ ሲወዳደር የነበረው ለብር ወይም ለሽልማት ብሎ ሳይሆን ብቃቱንና ችሎታውን ለማሳየት ነው” ያሉት ወ/ሮ አልማዝ፤ “ልጄ የግድ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ለመለየት ሲባል መስዋዕት ሆኗል፤ ውጤቱም አይገባውም” ብለዋል፡፡ “በዚህም” ልጅ አዋቂው የኢሳያስ አድናቂ በእንባ ተራጭቷል፤ እኔም ቅስሜ ተሰብሯል” በማለት ስሜታቸውን ገልፀዋል፡፡
ሌላው የባላገሩ ምርጦች ተወዳዳሪ ባልከው ዓለሙ፤ እስከ ምርጥ ስድስት የተካሄደው ዳኝነት፣ ግልጽነት የተሞላበትና ትክክለኛ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ የመጨረሻው ውጤት አሰጣጥ ግን የተድበሰበሰና ግልጽነት የጐደለው በመሆኑ በውጤቱ ቅር መሰኘቱን  ተናግሯል፡፡
“ባላገሩ ትልቅ እውቅናና እድል ስለሰጠኝ በሂደቱም፣ በአዘጋጁ አብርሃም ወልዴም በጣም ደስተኛ ነኝ” ያለው ባልከው፤ የውድድሩ ዕለት አብርሃም የገጠመው የጤና ዕክል በዳኝነቱ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል ባይ ነው፡፡
“እስከ ምርጥ ስድስት ድረስ ዳኞቹ እየሰበሰቡ ስለ ውጤት አሰጣጡና ስለ ዳኝነት ሂደቱ ይነግሩን ነበር፤ የመጨረሻው ላይ ግን ውድድሩን እንዴት እንደዳኙት፣ ውጤት አሰጣጡ ምን እንደሚመስል ምንም የሚታወቅ ነገር የለም” ብሏል - ባልከው፡፡ “ይሄ ደግሞ በአብርሃም ህመም ሳቢያ የተፈጠረ ችግር ነው” ያለው ተወዳዳሪው፤ “ሌላው ቀርቶ ከውጤት በኋላ ዳኞች ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት ሲገባቸው አልሰጡም” ሲልም አስተያየቱን ሰንዝሯል፡፡ በውድድሩ ምን ውጤት ጠብቆ እንደነበር ተጠይቆም፤ “በተመልካች ምርጫ ውጤት እስኪነገር ድረስ ወደ ሰባት ሺህ የሚጠጋ ድጋፍ ነበረኝ፤ ይህም የሶስተኝነት ደረጃ እንደማገኝ አመልካች ነበር፤ ነገር ግን የዳኝነቱን ሂደት ግልጽ ሳያደርጉ፣ ዳኞቹ ያለ ተፅዕኖ የፈለጉትን አድርገዋል” ሲል ቅሬታውን ገልጿል፡፡ እንዲያም ሆኖ ባላገሩ አይዶል የፈጠረለትን ትልቅ ዕድል አመስግኗል፡፡ “እዚህ እንድደርስ በስልጠና ብዙ ነገር ያሳወቀኝ ባላገሩ አይዶልንና አዘጋጁን አብርሃም ወልዴን ከልብ አመሰግናለሁ፤ ለባላገሩም ሆነ ለአዘጋጁ ትልቅ አክብሮት አለኝ” ብሏል፤ በቅርቡ ከአንድ ድርጅት ጋር ለመስራት ውል እየፈፀምኩ ነው፤ ይህ ሁሉ እድል የተገኘው በባላገሩ ስለሆነ በድጋሚ አመሰግናለሁ በማለት አስተያየቱን ቋጭቷል፡፡
ምርጥ ስድስት ውስጥ ከገቡት ድምፃዊያን አንዱ የሆነው ወጣት ቢኒያም እሸቱ ደግሞ በሁሉም ነገር ደስተኛ ነኝ ይላል፡፡ መጀመሪያም በቤተሰብና በጓደኛ ግፊት ሳይፈልግ ወደ ውድድሩ መግባቱን የጠቆመው ተወዳዳሪው፤ ተጀምሮ እስኪያልቅ በነበረው የውድድር ሂደት ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ለቢኒያም ደረጃና ሽልማት ዋናው ጉዳይ አይደለም፡፡ “በእስከዛሬው የውድድር ሂደት ላይ ዳኞቹ በሰጡኝ አስተያየት እየተመራሁ፣ ድክመቶቼን እያስተካከልኩ፣ እዚህ መድረሴና በራሴ ላይ ለውጥ ማምጣቴ ለእኔ ትልቅ እድል ነው” ብሏል፡፡
“ባላገሩ አይዶል ወደ ህይወቴ ከመጡ መልካም አጋጣሚዎች አንዱና ትልቁ ነው” የሚለው ተወዳዳሪው፤ “ደረጃና ሽልማት አስቤ ባለመግባቴ በዳኝነቱም ሆነ በውጤቱ ቅሬታ የለኝም፤ ባላገሩ አይዶል በፈጠረልኝ እውቅና የራሴን ስራ ሰርቼ ወደ ህዝቡ ለመቅረብ እጥራለሁ” ሲል ዕቅዱን ተናግሯል፡፡ “ባላገሩ አይዶል ወደ ህዝቡ ለመግባት ለስድስታችንም ሁኔታዎችን አቅልሎልናል፤ ይህን እድል መጠቀምና አለመጠቀም የእኛ ፋንታ ነው” ብሏል - ቢኒያም፡፡
የባላገሩ አይዶል የድምፅ ዳኛ አንጋፋው ድምፃዊ አረጋኸኝ ወራሽ ስለባላገሩ አይዶል ሲናገር፤ “ባላገሩ አይዶል በዚህች አገር የሙዚቃ ታሪክ ላይ የተለየና ጉልህ አሻራ ማሳረፍ የቻለ ትልቅ ፕሮግራም ነበር” በማለት አድናቆቱን ገልጿል፡፡ ባላገሩ በሁሉ ነገሩ የተለየ መሆኑን ሲገልፅም፡- ለምርጥ 25 ተወዳዳሪዎች በኩሪፍቱ የክህሎትና የዲስፒሊን ስልጠና መስጠቱ፣ በቁንጮ የሰራው አኒሜሽን፣ በከለር ካርዶች ውጤት እንዲሰጥ ማድረጉ፣ ከአልባሳት ጀምሮ ተወዳዳሪዎች ለሙያው ክብር እንዲኖራቸውና በራስ መተማመናቸው እንዲጐለብት መደረጉን ጠቃቅሷል፡፡
“በዚህ ሂደት ውስጥ ችሎታ ያላቸው 25 ምርጥ ባለሙያዎች ወደ ሙዚቃው ኢንዱስትሪ መቀላቀል ችለዋል” ያለው አረጋኸኝ፤ “ትውልዱ እድለኛ ነው፤ በእኛ ዘመን ድምፃዊያን ያላገኙት ሰፊ ዕድል ተፈጥሮለታል” ብሏል፡፡ “በውድድር ተሳታፊ ሆነው፣ ስልጠና ተመቻችቶላቸው፣ እውቅና አግኝተው፣ በመጨረሻም ተሸልመው ከመሄድ በላይ እድለኝነት የለም”፡፡ በባላገሩ አይዶል ያሳለፈውን የዳኝነት ጊዜ በተመለከተ ተጠይቆም፤ “እነዚህን የመሰሉ በስነ - ምግባር የታነፁ፣ ልዩ ችሎታና ብቃት ያላቸው፣ የሚያኮሩ ባለሙያዎች ባፈራው ባላገሩ አይዶል ላይ በዳኝነት እስከዚህ በመድረሴ ደስታም ኩራትም ይሰማኛል” ሲል መልሷል፡፡
በመጨረሻው የውድድር እለት በዳኞች ምዘና 1ኛ የወጣው ማን ነበር? በሚል ለቀረለበለት ጥያቄ፤ “በእኛ የዳኝነት ሂደት የሁለቱም (ዳዊት ፅጌና ኢሳያስ ታምራት) ነጥብ እኩል ነበር፤ ነገር ግን በተመልካች ድምጽና በታዛቢዎች ዳኝነት በጣም ጥቃቅን በሆነ ልዩነት አንደኛና ሁለተኛ ሆነዋል እንጂ… ሁለቱን እንዴት ማበላለጥ ይቻላል”፡፡
ሙዚቃ ሙያ ነው፤ መዳኘት ያለበት በባለሙያዎች እንጂ እንዴት በተመልካች ይሆናል፤ የተመልካች ድምፅ የግድ ነው ከተባለም እንዴት አብላጫውን ነጥብ (60%) ይይዛል? የሚል አስተያየት ከተለያዩ ወገኖች ይሰነዘራል፡፡ አረጋኸኝ በሰጠው የአንተ አስተያየት፤ “እኛ ስድስቱንም አንደኛ ማድረግ እንፈልግ ነበር፤ ነገር ግን ውድድር ስለሆነ እኛ በዳኝነት ብዙዎቹን እስከዚህ ድረስ አምጥተናል፤ ተመልካቹ በአሁን ሰዓት በሙዚቃ እውቀቱ የመጠቀ ስለሆነ በድምፁ መዳኘቱ ችግር ያለው አይመስለኝም” ብሏል፡፡
የባላገሩ አይዶል አዘጋጅና ዳይሬክተር አብርሃም ወልዴን ለማነጋገር ሞክረን ከህመሙ ጋር በተያያዘ ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡ ከእኛ ቀደም ብሎ ለ”ታዲያስ አዲስ” በሰጠው አስተያየት፤ “ማሸነፍ ያለበት አሸንፏል፤ የኦዲየንሱም ድምፅ ወሳኝ ነበር፤ አንድ ሰው ሮል ሞዴል የሚሆነው በብዙ አስተያየቶችና ውጤቶች ጥርቅም ነው” ብሏል፡፡ የዳዊትንና የኢሳያስን የመጨረሻ ትንቅንቅ በተመለከተ ለቀረበለት ጥያቄም፤ “ኢሳያስ በጣም ብቃቱን አሳይቷል፤ ነገር ግን ሪስክም ወስዷል፤ ብቻ በእለቱ ማሸነፍ የነበረበት አሸንፏል፡፡ የዳዊት አንደኛ መውጣት ግን የሌሎቹን ብቃት ጥያቄ ውስጥ የሚከት አይደለም” ያለው አብርሃም፣ “እኔ የሚያሳስበኝ አሁን አንደኛ ሁለተኛ መሆናቸው ሳይሆን ወደፊታቸው ምን ይሆናል፤ ነገ ምን ላይ ደርሰው አያቸዋለሁ” የሚለው ነው ብሏል፡፡
በገጠመው የጤና እክል የፕሮግራሙ ፍፃሜ እሱ ባሰበውና ባቀደው መልኩ አለመካሄዱ ቁጭት እንደፈጠረበት የጠቆመው አብርሃም፤ ህዝቡ ያደረገውን አስተዋፅኦና ያሳየውን ፍቅር በቃላት ለመግለፅ እንደሚቸግረው ለ”ታዲያስ አዲስ” ተናግሯል፡፡ለ3 ዓመት የዘለቀው ባላገሩ አይዶል ተጠናቋል፡፡ ነገር ግን ባላገሩ አይዶል አይቀጥልም እየተባለ ነው፡፡ ፕሮግራሙ ከተቀዳጀው ስኬትና ካበረከተው አስተዋጽኦ አንፃር  ቀጣይነቱ ጥያቄ ውስጥ መግባት ነበረበት ወይ? በሚል ለድምፃዊ አረጋኸኝ ወራሽ ላቀረብንለት ጥያቄ፤ “በእውነቱ ይሄን አዘጋጁን መጠየቅ ይቀላል፤ ነገር ግን እንደ ተመልካች ሆኜ ስናገር፣ ሁሉ ነገሩ ጥሩና ለየት ያለ በመሆኑ ቢቀጥል ደስ ይለኛል” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ባላገሩ አይዶል ይቀጥላል አይቀጥልም? ሌሎች ተጨማሪ 25 ወጣት ድምፃውያንን ያፈራል አያፈራም? ጊዜ መልሱን ይነግረናል፡፡

Read 10313 times