Saturday, 03 October 2015 09:45

የደብረ ከዋክብት አቡነ አረጋዊና ቅ/ገብረ ክርስቶስ አስተዳዳሪ የአዲስ አድማስን ዘገባ አስተባበሉ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

• የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ሪፖርት እንዲያቀርብ በምእመናኑና በሰንበት ት/ቤቱ ተጠይቋል
• የታገደው የቅ/ማርያም ገዳም ሰበካ ጉባኤ ሪፖርት ለማቅረብ የፓትርያርኩን አመራር ጠየቀ


በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የደብረ ከዋክብት አቡነ አረጋዊና ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ አስተዳዳሪ፣ ስለ ደብሩ የአስተዳደርና የገንዘብ አያያዝ ችግር በአዲስ አድማስ የወጣው ዘገባ፤ “በማስረጃ ተደግፎ ያልቀረበ የስም ማጥፋት አስተያየት ነው” ሲሉ አስተባበሉ፡፡
አስተዳዳሪው መልአከ ፀሐይ አባ ገብረ ሥላሴ ኃይለ ማርያም፣ “በአዲስ አበባ: ሰበካ ጉባኤያት በአስተዳደር ሓላፊዎች መታገዳቸው አሳሳቢ ሆኗል” በሚል ርእስ በተጠናቀረው ዘገባ፤ ስለ ደብሩ የተነሡት ጉዳዮች “ማንነታቸውን ባላወቅናቸው ግለሰቦች የቀረቡ ናቸው” በማለት  ዘገባውን ተቃውመዋል፡፡
በዘገባው፣ አስተዳዳሪው የሰበካ ጉባኤውን ውሳኔ አይተገብሩም የተባለው፣ “በግልጽ ተዘርዝሮ ያልቀረበና ፍጹም ሐሰት ነው፤” ያሉት አስተዳዳሪው፤ “በሰበካ ጉባኤው ተወስኖ ተግባራዊ ያልሆነ ምንም ዐይነት ውሳኔ የለም፤” ብለዋል፡፡ የሰበካ ጉባኤውን ምክትል ሊቀ መንበር ጨምሮ ሌሎችም አባላት፣ አንሠራም በማለታቸው በፈቃዳቸው ሓላፊነታቸውን የለቀቁና በደብዳቤም ቢጠሩ ለመምጣት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እንጂ አስተዳደሩ አንዳቸውንም እንዳላገደ ገልጸዋል፡፡
ደመወዝና ሥራ ማስኬጃ ከመፈረም ውጭ፣ በቃለ ዐዋዲው በተሰጣቸው ሥልጣንና ተግባር መሠረት በውሳኔ ሰጪነት የማይሳተፉት÷ የደብሩን ገቢና ወጪ አጥብቀው በመቆጣጠራቸው፤ የሒሳብ ሪፖርትም በመጠየቃቸው ሳቢያ እንደሆነ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በተካሔደ ማጣራት እንደተረጋገጠ የቀረበው ዘገባ “ሐሰት ነው” ያሉት አስተዳዳሪው፤ ስለጉዳዩ ለበላይ አካል ሪፖርት አቅርበው የሚሰጠውን ውሳኔና መመሪያ በመጠበቅ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ የአስተዳዳሪውን አልታዘዝ ባይነት በመግለጽ የክፍለ ከተማው ጽ/ቤትም ለሀገረ ስብከቱ አስተላልፎታል በሚል የቀረበውን ሪፖርትም በተመለከተ፤ “የደብሩ ጽ/ቤት የማያውቀው ነገር እንደሆነ” ገልፀዋል፡፡
የደብሩ የገቢና ወጪ ሒሳብ በዘመናዊ መልክ እንደሚሠራ በመጥቀስ የአሠራሩን ትክክለኛነት የገለፁት አስተዳዳሪው፣ የ2007 ዓ.ም. አጠቃላይ ሒሳብ ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በተላኩ ኦዲተሮች ተመርምሮ ያለምንም ጉድለት መጠናቀቁን ጠቅሰዋል፡፡ ሪፖርቱም በደብሩ መዝገብ የሚቀመጥ በመሆኑ የሰበካ ጉባኤው አባላት፣ ጠይቀው የመረዳት መብት አላቸው፤ ብለዋል፡፡ በማንኛውም ደብር ስም የሚከፈት የባንክ ሒሳብ የሚከፈተው በሀገረ ስብከቱ ቁጥጥር እንደሆነና የሚንቀሳቀሰውም በአስተዳዳሪውና በሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር እንደሆነ ያስረዱት አስተዳዳሪው፣ ሳይፈቀድ እንደተፈለገ የሚንቀሳቀስ አልያም የሚወጣና የሚገባ ገንዘብ የለም፤ በሚል ይህንኑ ያስረዳልኛል ያሉትን ማስረጃ አቅርበዋል፡፡
ለሀገረ ስብከቱ የሚገባው የሃያ በመቶ ድርሻ ፈሰስ ሳይደረግ፣ ደብሩ ለዕዳ ተዳርጓል መባሉን በተመለከተ አስተዳዳሪው በሰጡት ምላሽ፤ እርሳቸው ተመድበው ከመምጣቸው በፊት የብር 900‚000 ውዝፍ እንደነበረበትና ከተመደቡበት ካለፈው ዓመት መጋቢት 1 ቀን ጀምሮ ግን እንዲከፈል በማድረግ “ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድትመሰገን አደረግሁ እንጂ ለዕዳ ዳርገዋታል መባሉ ሐሰት ነው፤” ብለዋል፡፡
“ካህናት ፍቅርን የሚሰብኩ የሰላም አባቶች እንደሆኑና ቤተ ክርስቲያኒቱም ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ ልጆቿ ተሰባስበው በአንድነት የሚያገለግሉባት ነች፤” ያሉት አስተዳዳሪው፣ በተወላጅነት የተከፋፈለ አንድም ካህንና ሠራተኛ እንደሌለ በመጥቀስ፣ የሰበካ ጉባኤው አባላት በአስተዳደር ሠራተኞች ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ማኅበረ ካህናቱን በተወላጅነት ይከፋፍላሉ መባሉን አስተባብለዋል፡፡ ካህናትና ሠራተኞች ከደመወዝና ከሥራ እንዳልታገዱና ያጠፋ ቢኖር እንኳ በማገድ ሳይሆን በቃለ ዐዋዲው መሠረት፣ በቃል ምክርና በማስጠንቀቂያ የገንዘብ ቅጣት ሊቀጣ እንደሚችል አመልክተዋል፡፡  
ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ የበላይ አካል ሳያውቀው ቅጥርም ሆነ ዝውውር ተደርጎ አያውቅም፤ ያሉት አስተዳዳሪው፣ ያለአግባብ የሠራተኞች ቅጥርና ዝውውር እንደሚፈጽሙ በዘገባው የቀረበው፣ በማስረጃ ያልተደገፈ በመሆኑ ውድቅ ሊሆን እንደሚገባው አመልክተዋል፤ በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቋሚ ሠራተኛ እንዳስፈላጊነቱ ከአንድ አጥቢያ ወደ ሌላ እየተዘዋወሩ የመሥራት ግዴታ ያለባቸው በመሆኑም ቅሬታው ይህንኑ ደንብና መመሪያ በጥልቀት ያልተረዳ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡
አስተዳዳሪው የቤተ ክርስቲያንን መሬት ለግል ጥቅማቸው በማዋላቸው ከሓላፊነታቸው ታግደው እንደነበር የተጠቀሰውን በተመለከተ፣ መልካም ስማቸውንና ዝናቸውን ለመጉዳት ሆነ ተብሎ የተሰነዘረባቸው “ፍጹም ሐሰትና አሳዛኝ ውንጀላ ነው” ሲሉ ተከላክለዋል፡፡ አለቃው ከሓላፊነታቸው ታግደው እንደነበር በማስተባበያቸው ቢያምኑም፤ በፍርድ ወንጀለኛ ተብለው ያልተቀጡበት እንደሆነና እገዳውም ሥልጣኑ በማይመለከተውና ደረጃው በማይፈቅድለት ሓላፊ የተላለፈ እንደነበር በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መንፈሳዊ ፍ/ቤት ሚያዝያ 10 ቀን 2005 ዓ.ም. መረጋገጡን አስታውሰዋል፡፡ ይኸው ውሳኔ ለቅዱስ ሲኖዶሱ ታኅሣሥ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀርቦ ያልተከፈላቸው ደመወዛቸው ተከፍሏቸው ወደ ምድብ ሥራቸው እንዲመለሱ እንደተወሰነላቸውም በመጥቀስ ክሡ፣ “ፈጽሜ በማላውቀውና ባልተደረገ” የቀረበብኝ ነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
ከበርካታ አድባራት ሲቀርቡ በቆዩ አቤቱታዎች መነሻነት በአዲስ አድማስ በተጠናቀረው ዘገባ የተካተተው የደብረ ከዋክብት አቡነ አረጋዊና ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ውዝግብ፤ የሰበካ ጉባኤው አባላትና ምእመናን ለሀገረ ስብከቱ ባቀረቧቸው የጽሑፍ አቤቱታዎችና የኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በሀ/ስብከቱ ትእዛዝ አጣርቶ ባቀረበው ሪፖርት ላይ ተመሥርቶ የቀረበ መሆኑ ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል፣ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ከሥራ ውጭ ኾኖ ባለበት በአሁኑ ወቅት አስተዳዳሪው፣ ያለሰበካ ጉባኤው ፈቃድ በሰበካ ጉባኤው ስምና ማኅተም የጨረታ ማስታወቂያ በማውጣትና ሌሎች ደብዳቤዎችንም በመጻፍ አግባብነት የሌለው ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ ምእመናኑና የሰንበት ት/ቤቱ አባላት ይናገራሉ፡፡ ስለ ደብሩ ወቅታዊ ሁኔታ ባለፈው ሳምንት እሑድ መወያየታቸውን ጠቅሰው፣ የሰበካ ጉባኤውና የአስተዳደር ጽ/ቤቱ በነገው ዕለት የሥራ ሪፖርት እንዲያቀርቡላቸው የሚጠይቅ ከ500 በላይ ፊርማ አሰባስበው ማስገባታቸውን አስታውቀዋል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ የፓትርያርኩ መቀመጫ በሆነችው የቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም፣ ባለፈው ዓመት ግንቦት በአስተዳደር ሓላፊዎች የታገደው ሰበካ ጉባኤ፣ ለመረጠው የማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምእመናን ምልዓተ ጉባኤ፣ እንደ ቃለ ዐዋዲው ደንብ የሥራ ሪፖርቱን ማቅረብ እንዲችል ፓትርያርኩ አመራር ይሰጡለት ዘንድ ጠይቋል፤ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያም በደንቡ ድንጋጌዎች መሠረት ርምጃ እንዲወስድም ጠይቋል፡፡
በገዳሙ ያለውን ዘረፋ በማስቆም ግልጽነትንና ተጠያቂነትን የሚያሰፍኑ አሠራሮችን እንዲዘረጋ ከፓትርያርኩ በተቀበለው ትእዛዝ፣ መተዳደርያ ደንብና መመሪያዎችን አዘጋጅቶ በከፊል ወደ ሥራ ቢገባም አዎንታዊ እገዛም ሆነ አመራር አለማግኘቱን ጠቅሷል፡፡ ጉዳዩን በየጊዜው በተለያዩ መንገዶች ለፓትርያርኩ ሲያሳውቅ ቢቆይም፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለችግር የዳረጓትን ኃይሎችን ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ ጥበቃና ክብካቤ እየተደረገላቸው እንዳለ በመጥቀስ “እናቱን በገጀራ የገደለ ጎራዴ ተሸለመ” በሚል ተችቷል፡፡
 “ሙስናን እንታገላለን፤ መልካም አስተዳደር እናሰፍናለን” በሚል ፓትርያርኩ በየመድረኩ የገቧቸው ቃሎች በተግባር ካልተተረጎሙም የማዘናጊያ መፈክር ከመሆን ስለማያልፉ፣ መልካም አስተዳደርን በተግባር ወደሚያሰፍን ርምጃ እንዲገባ ጠይቋል፤ በዚህ በኩልም ተስፋ ባለመቁረጥ ከፓትርያርኩ ጎን እንደሚቆምም የታገደው ሰበካ ጉባኤ ዝግጁነቱን አረጋግጧል፡፡   

Read 2052 times