Saturday, 03 October 2015 09:43

የሠይፉ ፋንታሁን መልስ ነገ በመቄዶኒያ ይከናወናል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የታዋቂው የቴሌቪዥን ሾው አቅራቢ ሠይፉ ፋንታሁን እና የባለቤቱ ወ/ሮ ቬሮኒካ ኑረዲን የሠርግ መልስ ስነስርአት በነገው ዕለት በመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ይከናወናል፡፡ ሙሽሮቹ የመልስ ስነስርአቱን ከ550 በላይ አረጋውያንና የአዕምሮ  ህሙማን ጋር ከቀኑ 7 ሰአት ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ያከብሩታል ተብሏል፡፡ ባለፈው ጳጉሜ 1 ሰርጉን በሸራተን አዲስ በደማቅ ስነስርአት የፈፀመው ሰይፉ፤ለሠርጉ ሊያውለው አቅዶት የነበረውን 300ሺህ ብር ለመቄዶኒያና ለሙዳይ በጐ አድራጐት ድርጅት መለገሱ ይታወቃል፡፡ በመልሱ ላይ የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ታዋቂ ግለሰቦችና ከ5ሺህ በላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ማዕከሉ ጠቁሟል፡፡  በሥነሥርዓቱ ላይ የመቄዶንያ አረጋውያን፤ ሙሽሮችን የሚመርቁ ሲሆን  ሙሽሮቹም ከነሚዜዎቻቸውና ቤተሰቦቻቸው በማዕከሉ የሚገኙ አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማንን እንዲሁም አልጋ ላይ የዋሉ ህሙማንን ይጐበኛሉ ተብሏል፡፡ ለአረጋውያን ስጦታ የመስጠትና ጋቢ የማልበስ ፕሮግራም እንደሚኖር ያመለከተው ማዕከሉ፤ አረጋውያንም የእንኳን ደስ አላችሁ ግጥሞችና መነባንቦችን ያቀርባሉ ብሏል፡፡   
በማዕከሉ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ሰዎች የሠርግ፣ የቀለበት፣ የልደት፣ የምረቃ ስነስርአት እንዲሁም የሙት አመት መታሰቢያዎች የማከናወን ልምድ እንዳላቸው ታውቋል፡፡ መቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል መንግስት በነፃ ባበረከተለት 30ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ሰጪ ማዕከል ለመገንባትና የተገልጋዮችን ቁጥር ወደ 3ሺህ ለማሳደግ እየሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ማዕከሉን ለመገንባትም 300 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ መነገሩ ይታወሳል፡፡ 

Read 1842 times