Saturday, 26 September 2015 09:25

“የመንገድ አለመስራት ኢንቨስተሮችን እያሸሸብን ነው”- የሣውላ ከተማ አስተዳደር

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  በደቡብ ክልል ጋሞጐፋ ዞን፣ የደምባ ጐፋ ወረዳ ዋና ከተማ የሆነችው የሣውላ ከተማ ነዋሪዎችና ለአካባቢው አርሶ አደሮች፤ የዘመናት የመንገድ ጥያቄያችን ባለመፈታቱ
ተቸግረናል ሲሉ አማረሩ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ፤ የመንገድ ችግር ኢንቨስተሮችን እያሸሸብኝ ነው ብሏል፡፡
ከአዲስ አበባ በ516 ኪ. ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የሣውላ ከተማና በአካባቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮች፤ የተትረፈረፈ የኮረሪማ፣ የበቆሎ፣ የለውዝ፣ የሰሊጥ፣ የጤፍና የተለያዩ ሰብሎች ምርት ባለቤት ቢሆኑም በመንገድ ችግር ምክንያት ምርታቸውን ለማዕከላዊ ገበያ በአግባቡ አቅርበው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
የአካባቢው የአየር ፀባይ ለግብርና ስራና ለተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ምቹ ነው የሚለው የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ፤ የመንገዱ አለመገንባት ኢንቨስተሮችን እያሸሸ የከተማዋን እድገት አቀጭጮብኛል ብሏል፡፡በወላይታ ሶዶ አድርጐ ሣውላን ከአዲስ አበባ በሚያገናኘው መንገድ ከሣውላ እስከ ወላይታ
ሶዶ ያለው 200 ኪ.ሜትር ያህል የጠጠር መንገድ ወደ አስፓልት ደረጃ እንዲያድግ
ህብረተሰቡና የወረዳው ፅ/ቤት ጥያቄ ማቅረብ ከጀመሩ ከ10 አመት በላይ እንደሆናቸው የገለፁት ነዋሪዎቹ ችግራችን የሚታልን አካል አላገኘንም ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡን የሣውላ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቱርቃቶ ቱርቶ፤ ከተማዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግስት በተሠጣት ልዩ ትኩረት የተለያዩ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እየተገነቡ ቢሆንም የመንገዱ አለመሠራት ኢንቨስተሮችን
እያሸሸብን ነው ብለዋል፡፡ ቦታ በነፃ የተሰጣቸው ኢንቨስተሮች እንዳሉ የጠቀሱት ስራ አስኪያጁ፤ በመንገዱ አለመሰራት የተነሳ በቦታው ላይ ኢንቨስት ለማድረግ መቸገራቸውን ጠቅሰው፤ ለዓመታት የዘለቀው ችግሩ
እልባት እንዲያገኝ ጠይቀዋል፡፡    

Read 1309 times