Saturday, 26 September 2015 09:16

የመድሃኒት ዋጋውን በ5,000% የጨመረው ኩባንያ ተቃውሞ ገጥሞታል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    13.50 ዶላር የነበረው መድሃኒት፣ 750 ዶላር ገብቷል
    
   ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ዜጎች በሚወስዱት መድሃኒት ላይ የ5,000% የዋጋ ጭማሪ ያደረገው የአሜሪካ መድሃኒት አምራች ኩባንያ፣ ከታማሚዎች፣ ከመብት ተሟጋች ቡድኖች፣ ከህክምና ማህበራት፣ ከፖለቲከኞችና ከማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎች ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠመውና ዋጋውን ለመቀነስ ማሰቡን እንደገለፀው ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ቱሪንግ ፋርማሲዩቲካልስ የተባለው የመድሃኒት አምራች ኩባንያ፤ ዳራፕሪም በመባል የሚታወቀውን የመድሃኒት ምርቱን የመሸጫ ዋጋ ከ13.50 ዶላር ወደ 750 ዶላር ማሳደጉን ማስታወቁን ተከትሎ ከታማሚዎችና ከተለያዩ አካላት ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠመው የጠቆመው ዘገባው፣ የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚም የተወሰነ የዋጋ ቅናሽ ለማድረግ ማሰባቸውን እንደተናገሩ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የዋጋ ጭማሪው ያስነሳውን ተቃውሞ ለማጣጣል የሞከሩት የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርቲን ሸክሬሊ፣ ተቃውሞውን የሚሰነዝሩት ስለ መድሃኒት አምራች ኢንዱስትሪው አካሄድ በቂ ግንዛቤ የሌላቸው ሰዎች ናቸው፤ የዋጋ ጭማሪውን አድርገን የምናገኘውን ተጨማሪ ገንዘብ ሌሎች መድሃኒቶችን ለመፍጠር ለምናደርገው ምርምር ለማዋል ነበር ያሰብነው ብለዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው ማርቲን ሸክሬሊ በትዊተር ገጻቸው ላይ የተሰነዘረባቸውን ከፍተኛ ተቃውሞ ተከትሎ፣ ቱሪንግ ፋርማሲዩቲካልስ የተባለው ኩባንያቸው በቅርቡ ከህብረተሰቡ የመግዛት አቅም ጋር የሚመጣጠን የዋጋ ቅናሽ እንደሚደርግ ቢናገሩም፣ ምን ያህል የዋጋ ቅናሽ ለማድረግ እንደታሰበ በግልጽ አላሳወቁም፡፡
ኩባንያው ዳራፕሪም የተባለውንና የቶክሶፕላዝሞሲስ የፓራሳይት ኢንፌክሽንን በማከም ረገድ ፍቱን የሆነውን መድሃኒት አምርቶ የመሸጥ ፍቃድ ያገኘው በቅርቡ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ ኤችአይቪ ኤድስን በመሳሰሉ በሽታዎች የተጠቁና በሽታን የመከላከል ተፈጥሯዊ አቅማቸው ደካማ የሆኑ ታማሚዎች መድሃኒቱን በስፋት እንደሚወስዱ ገልጧል፡፡
በተያያዘ ዜናም በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የሚሰነዘሩ ሃሳቦችን መነሻ በማድረግ ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ፣ በአሁኑ ወቅት በአገረ አሜሪካ አይንህን ለአፈር በመባልና በመጠላት ረገድ፣ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ያደረገውን ኩባንያ የሚመሩት የ32 አመቱ ማርቲን ሸክሬሊ ቱሪንግ፣ ቀዳሚውን ስፍራ ሊይዙ እንደሚችሉ ጠቁሟል፡፡

Read 1577 times