Saturday, 26 September 2015 08:50

መጪው በጋ የዝናብ ወቅት ይሆናል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

ወንዞችም ይሞላሉ ተብሏል
   በመጪዎቹ የበጋ ወራት ወቅቱን ያልጠበቀ ከፍተኛ ዝናብ አዲስ አበባና አካባቢዋን ጨምሮ በአብዛኛው የሃገሪቱ ክፍሎች የሚጠበቅ ሲሆን ጐርፍም ሊከሰት ይችላል ተብሏል፡፡
የብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ትናንት ባቀረበው የትንበያ ሪፖርት፤ በኤሊኖ ክስተት ምክንያት ካለፉት አመታት በተለየ የክረምቱ ዝናብ ዝቅተኛ እንደነበር ጠቅሶ የዝናቡ ስርጭት በመጪዎቹ የበጋ ወራት ያይላል ብሏል፡፡
ከጥቅምት ጀምሮ የሚጠበቀው ዝናብ፤ በደቡብና በደቡብ ምስራቅ የሃገሪቱ ክፍሎች ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የተባለ ሲሆን በተለይ በቦረና ጉጂ፣ ባሌ፣ ሶማሌና በደቡብ የኢትዮጵያ ክልሎች ዝናብ መዝነቡ ለአርብቶ አደሩ የግጦሽ ሣርና የመጠጥ ውሃ ከማስገኘቱ አንፃር ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡
በድርቁ ክፉኛ ተጐድቶ የነበረው የአፋር ክልልም በበጋው በቂ ዝናብ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአንፃሩ በበጋው ወቅት ደረቅ መሆን ይጠበቅባቸው በነበሩ የሀገሪቱ ሰሜን፣ ሰሜን ምስራቅ፣ መካከለኛው እና ምስራቅ አካባቢዎች ላይ የሚዘንበው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፤ የደረሱ ሰብሎች ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል ተብሏል፡፡ ለአርሶ አደሩም በየጊዜው መረጃ በመስጠት ምርቱን በጊዜ እንዲሰበስብ ማድረግ ይገባል ተብሏል፡፡
በአጠቃላይ ቀጣዩ የበጋ ወቅት ከዚህ በፊት ከተለመደው ውጪ ዝናባማና እርጥበታማ ሆኖ እንደሚዘልቅ የጠቆመው ኤጀንሲው፤ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ከወትሮው በተለየ ጐርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ ዝናብም ያጋጥማል ብሏል፡፡
ጐርፍ ያስከትላል ተብሎ በሚጠበቀው ከባድ ዝናብ መነሻነትም በዋቢሸበሌ፣ ገናሌና ኦሞ ወንዞች ላይ ከወትሮው በተለየ ሙላት ያስከትላል ተብሏል፡፡ በበጋው ወቅት ደረቅ መሆን ሲገባቸው ዝናብ የሚዘንብባቸው አካባቢዎች፣ ከሚፈጠረው ደመናና ዝናብ የተነሣ፣ ከከፍተኛ ቅዝቃዜና ውርጭ ስጋት ነፃ ሊሆኑ እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡
የበጋውን ወቅት ወደ ክረምትነት ይቀይረዋል የተባለው የአየር ፀባይ መዛባት (የኢሊኖ ክስተት) ወደ አመቱ አጋማሽ አካባቢ ቀስ በቀስ እየቀነሰ ወደ መደበኛው የአየር ፀባይ ይለወጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም የሜቲዎሮሎጂ ትንበያ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡  

Read 3919 times