Saturday, 04 February 2012 12:44

የነፃነት ዕዳ

Written by  ሶፎንያስ
Rate this item
(1 Vote)

የእውን ህልም ናት፤ ያላገኘ የሚያልማት፡፡ ነፃነት ልዩ ወርቅ ናት፣ ያላገኘ የሚመኛት፡፡ ነጻነት ብርቅና ድንቅ ናት፤ ሰው ሁሉ የሚራኮትላት፡፡ ነጻነት ለመቀዳጀት እንደ ግለሰብም፣ እንደ ሀገርም ስንት ዋጋ ይከፈላል፡፡ ዋጋ የሚከፈለው ዋጋ ያለው ነገር ስለሆነ ነው፡፡ ዋጋ የሌለው ነገር ዋጋ አያስከፍልም፡፡ ይቅርታ… ሊያስከፍል ይችላል፡፡ የሚያስከፍለው ግን ዋጋ የሌለው ነገር ዋጋ ስላለው ሳይሆን፣ ዋጋ ከፋዩ ዋጋ ቢስ ስለሆነ ነው፡፡ ነጻነት ግን ዋጋ አለው፤ ዋጋው ትልቅ ስለሆነም፣ ትልቁን ህይወት እስከማስከፈል ይደርሳል፡፡ ለምሳሌ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ ለመውጣት ባደረጉት ተጋድሎ የብዙ ሰው ህይወትን በመስዋዕትነት ገብረዋል፡፡ እነዛ የሞቱ ሰዎች ለነጻነት ሲባል የተከፈሉ የነጻነት ዋጋዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በአድዋ ጣልያን ላይ ድልን የተቀዳጁት በነጻ አይደለም፡፡ የህይወት ዋጋ ከፍለዋል፡፡ በአምስት ዓመቱ የጣልያን ወረራ ጊዜም አርበኞች በየጫካው የተዋጉት የህይወትና የአካል መስዋዕትነት እየከፈሉ ነው፡፡

ደቡብ አፍሪካውያን ከአፓርታይድ አገዛዝ ነጻ የወጡት ዋጋ ከፍለው ነው፡፡ ለዛሬዋ ደቡብ አፍሪካ ደቡብ አፍሪካ መሆን በስም የማይጠቀሱ ሰዎች ጭምር መስዋዕት ሆነዋል፡፡ ነጻነት ምንም ፀጋ ቢሆን ደግሞም ዕዳ ነው፡፡ ለግለሰብም፣ ለሀገርም ነጻነት የተከፈለው ተከፍሎ ነጻ መሆኑ ከተገኘ በኋላ አርፎ መቀመጥ አይቻልም፡፡ አብሮት የሚመጣ ኃላፊነት አለ፡፡ አብሮት የሚመጣ ዕዳ አለ፡፡ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ሲሳን ኃላፊነቱ ዕዳ ይሆናል፡፡ ይኼ እንደሀገርም እንደ ግለሰብም የሚከሰት ነገር ነው፡፡ አያያዙን ካላወቁበት ሲያዩት ያማረ ሲይዙት ያደናግራል፡፡ ለዚህ ነው በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ነጻ ከወጡ በኋላ ነጻነትን ሳያጣጥሙ የቀሩት፡፡ መሪዎቻቸው መምራትን አልቻሉበትማ! ከመምራት ይልቅ ሲገዙ እንደነበሩት ቅኝ ገዢዎች እነሱም በተራቸው መግዛት አማራቸው፡፡ ልዩነቱ እነዛ ባዕድ እነዚህ ግን ባለተመሳሳይ ቀለም መሆናቸው ነው፡፡ የነጻነት አባት የተባሉትና በነጻ አውጪነት የተፋለሙት መሪዎች ስልጣን ላይ ጉብ ሲሉ ህዝባቸውን ነጻነት ነፈጉት፡፡ ቀጥቅጠው ገዙት፡፡ ያገኙትን ነጻነት ለሀገራቸው መልካም ነገር ለመስራት በማዋል ፈንታ የራሳቸውን ህይወት በመስራት ተጠመዱ፡፡ ከህዝብ  ሰላምና ዕድገት የራስ ሆድና ኪስ ቀደመ፡፡ ሆድም ቦረጨ፣ ኪስም አበጠ፡፡ ሀገራት ግን ኮሰመኑ፡፡ ፀጋ የሆነው ነጻነትም ዕዳ ሆነ፡፡ ችግሩ ብዙዎቹ የአፍሪካ መሪዎች ነጻነቱን በአግባቡ አለመጠቀማቸው ላይ ነው፡፡ የነጻነትን ትርጉም አዛቡት፡፡ ነጻነት በከፊል ኃላፊነት መሆኑን ዘነጉት፡፡ ሥልጣን ግለሰቦች ሀገርን የሚያገለግሉበት ስርዓት መሆኑ ቀርቶ፣ ሀገር ግለሰብን የምታገለግልበት ስርዓት ሆነ፡፡ ነጻነት በግለሰብ ደረጃም የኃላፊነት ጐኑ ከተረሳ ችግር ነው፡፡ ልጆች ከወላጆቻቸው ቁጥጥር ሲወጡ ነጻነት ከብዶ የሚያጐብጣቸው ለዚህ ነው፡፡ ነገሮችን እየመረጡ ማድረግና እየመረጡ መተው ይከብዳቸዋል፡፡ ሁሉን ካላደረግኩት የሚል አባዜ ይጠናወታቸዋል፡፡ ገበያ ወጥቶ የማያውቅ ሰው የቱን ጥሎ የቱን ማንሳት እንዳለበት፣ የቱን ትቶ የቱን መግዛት እንዳለበት ከምርጫ ብዛት ግራ ተጋብቶ እንደሚወናበድ ይወናበዳሉ፡፡ ህይወት ዓይነ አዋጅ ትሆንባቸዋለች፡፡ ለዚህ ምስክርነት የዩኒቨርሲቲ ህይወት መልካም ምሳሌ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከቤተሰብ ተለይተው መኖር የሚጀምሩበት፤ ራሳቸውን በራሳቸው መሸከም እንዲችሉ የሚጠበቅበት ስፍራ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በወላጅ ቁጥጥርና ክትትል ይወጡና ይገቡ የነበሩ ሰዎች አሁን በራሳቸው ቁጥጥር ስር የሚወድቁበት ነው፡፡ ራሳቸውን በአግባቡ መቆጣጠር ካልቻሉ፣ ብዙ ነገሮች ሊቆጣጠሩዋቸው ይችላሉ፡፡ እንደ ወላጅ የሚቆጡና የሚመክሩ ሳይሆኑ እንደገዢ የሚገዙና ባሪያ የሚያደርጉ ነገሮች ይቆጣጠሯቸዋል፡፡ ስንፍና  አለ፡፡ ሴሰኝነት አለ፡፡ ሱሰኝነት አለ፡፡ ጫት፣ ሲጋራ፣ መጠጥ፣ ሴት፣ ወንድ …ወዘተ…

ከጨለማ ወደ ብርሃን ሲወጣ ዓይን እንደሚጭብረበርና እንደምንደናበር፣ ከባርነት ወይም ከጥገኝነት ወደ ነጻነት ሲወጣ መጨናበስና መደነጋገር ሊፈጠር ይችላል፡፡ በዛ መደነጋገር ውስጥ የሚጠፉም ይኖራሉ፡፡

የመሰናዶ ትምህርት ቤት (Preparatory School) እያለን የማውቃት አንዲት ልጅ ነበረች፡፡ የአንድ ክፍል ተማሪዎች ነበርን፡፡ ልጅትዋ ሳውቃት በጣም ጨዋ፣ በጣም ዓይንአፋር ነበረች፡፡ ከዓይናፋርነትዋ የተነሳ ሰላምታ እንኳን የምትለዋወጠው ከጥቂቶች ጋር ነበር፡፡

ይህች ልጅ ዩኒቨርሲቲ ገባች፡፡ እኔም ገባሁ፡፡ የደረሰን አንድ ሀገር ነበርና ታሪክ ላይ በቃሁ፡፡ ልጅትዋ ነጻነት ከበዳት፡፡ ከማይሆኑ ልጆች ጋር መዋል ጀመረች፡፡ ትምህርቷን ተወች፡፡ ስራዋ ከጭፈራ ቤት ጭፈራ ቤት ማፈራረቅ ሆነ፡፡ ውሎና አዳሯ ያለ ወንድ የማይታሰብ እየሆነባት ሄደ፡፡ እና በመጀመሪያው ሴሚስተር ከዩኒቨርሲቲው ሙሉ ለሙሉ ተባረረች፡፡ ስለዚህች ልጅ ሳስብ የማስበው ነጻነት እንደሚያጐብጥ ነው፡፡ ነጻነት በአግባቡ ላልተጠቀመበት፣ ኃላፊነቱን ለመወጣት ላልተጋበት ዕዳ ብቻ ሳይሆን መጥፊያም ይሆናል፡፡ ዩኒቨርሲቲ ሳለሁ አንድ ወዳጅ ነበረኝ፡፡ ይሄ ወዳጄ ከመልካም ቤተሰብ የመጣ መልካም ተማሪ ነበር፡፡ በመጀመሪያው ዓመት ጥሩ ውጤት ካላቸው ተማሪዎች (ከሰቃዮች) አንዱ ነበር፡፡ በኋላ ግን ነጻነት እየከበደው፣ ነጻነት የሚጠይቀውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እየተሳነው መጣ፡፡ መቃም ጀመረ፡፡ ቀጠለና ማጨስ ጀመረ፡፡ ሰለሰና መጠጣት አከለበት፡፡

“ምነው?” ስለው

“ዓለምን አሁን ገና በእጄ ጨበጥኳት” አለ፡፡

አዝኜ ተውኩት፡፡ ይኼ ወዳጄ የሱስ ሰለባ ሆኖ ቀረ፡፡ ለኔ ሲገባኝ ይህን ያመጣው ነጻነትን በአግባቡ መጠቀም አለመቻል ነው፡፡ ከቁጥጥር እስር ወደ ነጻነት ብርሃን ስንወጣ ብዥ ይልብንና እንደነባበራለን፡፡ ስንደነባበር ደግሞ የምናደርገውንም አናውቅም፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ነጻነትን የተለማመድን እየመሰለን “ራሳችንን እናጠፋለን፡፡” ለምሳሌ በፊት ወላጆቹ ዘንድ በምግብና ውሃ ብቻ የሚኖር፣ ከእነሱ ተለይቶ ለብቻው ሲሆን ጫትና ሲጋራ ካልሞከረ ነጻነቱን የተለማመደ የማይመስለው አለ፡፡ ይሄ ሞኝነት ወይም ነጻነትን አለመረዳት እንጂ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም፡፡

ነጻነት ዕዳ ነው፡፡ በአግባቡ ማሰብን ይጠይቃል፡፡ ነፃነትን ከመቀዳጀታችን በፊት የሚያስብልም፣ የሚያስብብንም የተቆጣጠረን ወይም የሚገዛን አካል ነው፡፡ በሌላው ሀሳብ ነው የምንተዳደደረው፡፡ ለማሰብ ጉልበት አናፈስም፡፡ ራሳችንን ለመምራት በምናደርገው ትጋት የምናንጠባጥበው ላብ የለም፡፡ የሚመራን ሌላው ነው፡፡ እኛ ተከታይ ነን፡፡

ነጻነትን ስንቀዳጅ ግን ማሰብ የእኛ ስራ ይሆናል፡፡ የማመዛዘን የውዴታ ግዴታ ውስጥ እንገባለን፡፡ የሚያስብልን የለም፡፡ የሚመራን የለም፡፡ የሚራመድልን፣ የሚናገርልን አካል የለም፡፡ ኃላፊነቱ በእኛ ጫንቃ ላይ ይወድቃል፡፡ ይህን መወጣት ያልቻሉ ተደናቅፈው ይወድቃሉ፡፡

የነጻነት አንዱ ገፅታው ኃላፊነት ነው፡፡ ይኼ ገጽታ ሲጠፋ ነጻነቱም ይጠፋል፡፡ ወይም የነጻነቱ ባለቤት ራሱ ይጠፋል፡፡ ይኼ ምንም ሚስጥር ወይም ውስብስብ ነገር የለውም፡፡ በአፍሪካ መሪዎችና በተማሪዎቹ ምሳሌ ያየነው እውነት ነው፡፡ ፍንትው ያለ እውነት! እውነትነቱም የአመት ሳይሆን የዕለት ተዕለት!!

 

 

Read 2648 times Last modified on Saturday, 04 February 2012 12:54