Saturday, 19 September 2015 09:00

‘የሰው ሚስት አትመኝ’ ብሎ ነገር…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ከዘመን ዘመን ስላሸጋገርከን ምስጋና ይግባህ፡፡
አንድዬ፡— አጅሬው ደግሞ መጣህ!… ዘንድሮስ ፈጠንክ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ዓመቱን ሙሉ ስጨቀጭቅህ ከምኖር ለምን አንድ ጊዜ ዝርግፍ አይወጣልኝም ብዬ ነው፡፡ መቼም የተሸከምነው ሸክም እኮ አንድዬ… የተሸከምነው ሸክም!
አንድዬ፡— እሺ፣ አሁን ደግሞ ምን አድርግ ልትለኝ ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንደዬ፣ አሁን እንኳ ለየት ያለ ነው፡፡ ምን መሰለህ… አሥርቱ ትዕዛዛትን እንደገና አይተህ ወይ አሻሸልልን፣ ወይ ሙሉ ለሙሉ ለውጥልን፡፡
አንድዬ፡— (ከት ብሎ ሳቀ)  ብላችሁ፣ ብላችሁ ደግሞ በዚህ መጣችሁ! ምኑን ነው የማሻሽልላችሁ! ቃሌ እንደማይለውጥ ጭራሹኑ ረሳችሁት!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንደዬ ብዙ ትዕዛዞችህን፣ — እንደውም ሁሉንም ልንል ማለት አልቀረንም — መፈጸሙ እየከበደን ስለመጣ ማሻሻያ ይደረግልን፡፡
አንድዬ፡— ነገርኩህ፣ ቃሌ አይለወጥም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ጊዜው ተለውጧላ! ጊዜው ተለውጧል!
አንድዬ፡— ጊዜማ ያው ነው፡ እየተለዋወጠ ያስቸገረኝ ጊዜው ሳይሆን የእናንተ ባህሪይ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ያኔ አንተ እነኛን ትዕዛዛት ለሙሴ የሰጠኸው ጊዜ የነበረው ዓለምና የአሁኑ ዓለም ተለዋውጧል እኮ!
አንድዬ፡— ታዲያ እናንተ ትዕዛዛቴን መፈጸም ካልቻላችሁ ተዉት እንጂ፡ ያውም ለእናንተ  ‘ስፈጥራቸው የሠራሁት ስህተት ነበር እንዴ!’ እያልኩ ራሴኑ እንድጠይቅ ላደረጋችሁኝ  ብዬ  ነው ዓለም የሚመራባቸውን ትዕዛዛት የምለውጥ!
ምስኪን ሀበሻ፡— እሺ አንድዬ፣ ቢያንስ ትዕዛዛቱን ለጊዜው እኛ ላይ እንዳይሠራ አግድልንና የሽግግር ጊዜ ስጠን፡
አንድዬ፡— የምን ጊዜ አልከኝ?
ምስኪን ሀበሻ፡— የሽግግር ጊዜ…
አንድዬ፡— እሱ ደግሞ ምንድነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ በቃ ስለእኛ ነገር ዓለሙን ትተኸዋል! አየህ እኛ ዘንድ ለሁሉ ነገር የሽግግር ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ አሥር ዓመት ለሞላውም፣ ሀያ ዓመት ለሞላውም የሽግግር ጊዜ ለምዶብናል፡፡ ይኸው ከስንትና ስንት ዓመት በፊት ጀመርናቸው ያልናቸው ነገሮች ላይ ሁሉ ገና ሽግግር ላይ አይደለን፡፡ አንድዬ ትንሽ ቂ…ቂ…ቂ… ብል ቅር ይልሀል!
አንድዬ፡— ቂ…ቂ..ቂ…. ደግሞ ምንድነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— ሳቅ ነዋ አንድዬ!
አንድዬ፡— ተስቆ ተሙቷል፡፡ በል ሳቅህን ለብቻህ ስትሆን ትስቃለህ፡፡ አንዳችሁ በአንዳችሁ እየሳቃችሁ አይደል ወደ እኔ ለአቤቱታ የምትግተለተሉት! አሁን ወደ ጉዳይህ…የመጨረሻ ቃሌ ትዕዛዛቱ አይለወጡም ነው፡፡ ጨረስን አይደል!
ምስኪን ሀበሻ፡— አልጨረስንም አንደዬ፣ አለጨረስንም፡፡ ገና መች ጀመርንና!
አንድዬ፡— ስነግርህ ስማ እንጂ…ነው ወይስ እልፍኜ ድረስ እያስተጋባ የሚረብሸኝ ጭቅጭቃችሁን ቁጭ ብዬ ላዳምጥ!
ምስኪን ሀበሻ፡— በጭራሽ አንድዬ፣ በጭራሽ! ግን ለምሳሌ ‘የሰው ሚስት አትመኝ’ ምናምን የሚለው ትዕዛዝ በአሁኑ ጊዜ አንተስ ስታየው ልክ ነው? አንተ መጀመሪያ የመመኘት ባህሪይን ባትፈጥርልን ኖሮ እኛስ እንመኝ ነበር!
አንድዬ፡— እና ምን ይሁን ነው የምትለው?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ምኞት ብቻ ሀጢአት መሆኑ ልክ አይደለማ! ትንሽ አኮ የምንተነፍሰው ምኞት የተባለ ነገር ስላለ ነው፡፡ እሱኑ ወስደህብን ምን እንሁን?
አንድዬ፡— ታዲያ ደግ ደጉን ነገር ተመኙ እንጂ የሰው ሚስት ምን ያስመኛችኋል?
ምስኪን ሀበሻ፡— ዘመኑ ነዋ አንድዬ… ደግሞ አንድዬ፣ አትታዘበኝ እንጂ ገና ሲያዩዋት ልብ ቷ የምታደርግ የሰው ሚስት ከመመኘት የበለጠ ምን ደስታ አለ! አንድዬ ዘመናዊነት የሚለካው አንድም የሰው ሚስት በመመኘት፡ ከተቻለ ደግሞ እነሆ በረከት…
አንድዬ፡— እነሆ ምን?
ምስኪን ሀበሻ፡— እነሆ በረከት…ምን መሰለህ አንድዬ፣ ይሄ አንሶላ መጋፈፍ የሚባል ነገር አለ አይደል… አንዳንዴ እንደ ቅኔ ልናስመስለው እነሆ በረከት እንለዋለን፡፡ ለነገሩ አንድዬ ዘንድሮ የሚገፈፍ አንሶላም አያስፈልገንም፡፡
እሱንማ እኔ መኖሬን ረስታችሁ ‘ሰው ባያይ እሱ ያየናል ብላችሁ ሳትሰጉ፣ በአደባባይ ተያይዛችሁት የለ እንዴ! … በፊት እኮ የአካል እንቅስቃሴ የምታደርጉ እየመሰለኝ መለስ ብዬም አላይም ነበር፡፡ በኋላ ላይ አይደል እንዴ ጉዳችሁን ያወቅሁት!
ምስኪን ሀበሻ፡— ይኸው አንድዬ፣ ይኸው! አኔም የምልህ እኮ ይህንኑ ነው፡፡ እነዛ የምታያቸው እኮ ገሚሶቹ የሌሎች ባሎች ሚስቶች፣ ገሚሶቹ የሌሎች ሚስቶች ባሎች ናቸው፡፡ አንድዬ እንደውም አንድዬ፣ ራሳቸው ሚስት፣ ባል የሚባሉት ቃላት የትርጉም ለውጥ ያስፈልጋቸዋል፡፡
አንድዬ፡— እውነት!
ምስኪን ሀበሻ፡— እንክት ነዋ፣ አንድዬ!… ለምሳሌ ሚስት የሚባለውን ቃል ትርጉም ‘ለግል ይዞታነት ብቻ ሳይሆን እንደ ተጫባጭ ሁኔታው አንዳንዴም ‘አውትሶርስ’ በማድረግ…
አንድዬ፡— አንደኛውን ለይቶላችኋልና! አንደኛውን የጋራ በለኝና እረፈው!
ምስኪን ሀበሻ፡— አየህልኝ አይደል አንዴዬ! ይሄኔ እንዴት እየሆኑ ነው ብለህ አለፍ፣ አለፍ እያልክ ብየታየን ኖሮ እንዲሀ አትለኝም ነበር፡፡ አንድዬ…ሚስቱን ተነጠቆ የቺን ታክል የማይሰማው  ባል የሞላበት ዘመን ነው እኮ፡፡
አንድዬ፡— ለእናንተ አሥሩን ትዕዛዛት ማሻሻል ሳይሆን ማድረግ ያለብኝ ሌሎች ለእናንተ ብቻ የሚሆኑ አንድ መቶ አሥር ትዕዛዛት መጨመር ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ምነው አንድዬ፣ ምነው፡! አሁን ያለው ሸክም ከበደን እያልንህ እንደገና መቶ አሥር ትዕዛዛት!
አንድዬ፡— አንድ የማውቅላችሁ ነገር ቢኖር ሸክም እንደምትችሉ ነው፡፡ የእናንተ ሸክም ሌላው ትከኛ ላይ ቢሆን የሰዉ ሁሉ ትከሻ ተሳባብሮ፣ ተሰባብሮ እኔንም ‘ምን ብዬ ነው ትከሻ የሚል የአካል ክፍል የፈጠርኩት!’ ብዬ ጸጸት ይገባኝ ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ደግሞ አንድዬ ያኔ ትዕዛዙን ስታወጣ በወንዶች ላይ አድልዎ ፈጽመሀል፡፡ በዚሀ ዘመን ቢሆን ኖሮ በጸረ ወንድንት ትከሰስ ነበር፡፡
አንድዬ፡— ክሰሱኛ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ኸረ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን!
አንድዬ፡— አንተው ነህ ያልከው፡፡ እሺ፣ ምን ማለት ነበረብኝ፡
ምስኪን ሀበሻ፡— የሰው ሚስት አትመኝ ከሚለው አስከትለህ የሰው በባል አትመኚ ብለህ መጨመር ነበረብሀ!
አንድዬ፡— እንደዛ ባይባልስ የታወቀ አይደለም እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አይደለም አንደዬ፣ የታወቀ አይደለም፡፡ ዘንድሮ እኮ ከሚስት ነጣቂ እኩል ባል ነጣቂ ሞልቶልሀል፡፡
አንድዬ፡— ለመነጣጠቅማ ጊዜና ቦታ አታጡም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ኸረ ጊዜም ቦታም አያስፈልገንም…
አንድዬ፡— ማለት…
ምስኪን ሀበሻ፡— ማለትማ አንድዬ…መኪናው በለው፣ ቢሮው በለው፣ የህንጻ ጣራና ምድር ቤት በለው፣ የግምብ ጥግ በለው… ብቻ ልበለህ ሁሉ ቦታ ላየ ነው ሚስትምባልም የሚነጠቀው፡፡
አንድዬ፡— ግራ አጋባኸኝ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንደዬ ክፉ አታነግረኛ! በቃ እዛው ይነጠቃል፣ እዛው እንትን ይባላል…አለቀ ደቀቀ፡፡ ነገም ሌላ ቀን ነው፡፡
አንድዬ፡— ለመራቢያ የሰጠኋችሁን የሰውነት ክፍሎች መረባረቢያ አደረጋችኋቸዋ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ በትክክል ተመልሷል፡፡ አሁን ገና የእኛ ቋንቋ እየገባህ ነው፡፡  አንድዬ፣ ግን የአሥርቱን ትዕዛዛት ነገር አስተካክልልንና ስትራቴጂ ነድፈን፣ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት ተረባርበን ለስኬት በማብቃት የምእተ ዓመቱን ግብ እናሳካለን፡፡
አንድዬ፡— ቆይ፣ ቆየኝማ እስኪ ያለከውን ድገምልኝ፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እኔም ቃል በቃል ለመድገም ያስቸግረኛል፡፡
አንድዬ፡— ባያስቸግርህ ነበር የሚገርመኝ፡፡ ሦስት ምዕራፈ የሚወጣውን ነገር በአንድ አራት ነጥብ ብቻ ነው እኮ የጨረስከው!
ምስኪን ሀበሻ፡— ዘመን ነዋ፣ አንድዬ! ከዘመኑ ጋር እሄድ ብዬ ነው፡፡
አንድዬ፡— በል አሁን ብዙ የቁም ነገር ጥያቄ ይዘው የሚጠብቁኝ ስላሉ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ መቼ ጨረስኩ! እንደውም አልጀመርኩም፡፡
አንድዬ፡— ሳምንት ተመለስ…
ምስኪን ሀበሻ፡— ይመችህ አንድዬ፣ ይመችህ!
አንድዬ፡— ሆሆይ… ቀስ ብለህ እኮ ቢራ ልጋብዝህ ልትለኝ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ብልህ አትገረም፡፡ እንደ አምላክ የሚያደርገን በዝተናል፡፡
አንድዬ፡— በል ደህና ሰንብት፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አሜን አንድዬ፣ አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4674 times