Saturday, 04 February 2012 12:44

“የወደፊቱ ስልጠና - ጥራትና ብቃት”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

ESOG፤ 20ኛ አመታዊ ጉባኤ፡ ጥር 18-19/2004

(Jan 27-28 /20012)

ኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር መሑሀ  20ኛውን አመታዊ ጉባኤ በትግራይ ክልላዊ መስተዳድር በመቀሌ ከተማ በሚገኘው የሰማእታት መታሰቢያ አዳራሽ አካሂዶአል፡፡የኢሶግን 20ኛውን አመታዊ ጉባኤ በንግግር የከፈቱት የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ አባይ ወልዱ ናቸው፡፡ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ይገኛሉ ተብለው የተጠበቁት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ተዎድሮስ አድሀኖም በስራ ምክንያት ሊገኙ ባለመቻላቸው በመክፈቻው ላይ እንዲነገርላቸው የላኩት መልእክት በክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ሓላፊ ወ/ሮ ያለም ጸጋዬ አማካኝነት ለጉባኤው ቀርቦአል፡፡ ወ/ሮ ያለም ጸጋዬ በክልሉ ጤና ቢሮ ስም ጉባኤውን ሚመለከት የሚከተለውን ንግግር አድርገዋል፡፡

“የኢሶግ 20ኛው ኮንፍረንስ በትግራይ በመካሄዱ በጣም ደስታ ተሰምቶናል፡፡ ይህ ኮንፍረንስ በአጠቃላይ በእናቶች ጤና ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚካሄድ ሲሆን ልዩ የሚያደርገው የትግራይ ክልልም የእናቶችን ጤና በመጠበቅ ረገድ በስፋት የሚንቀሳቀስበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡ የኮንፍረንሱ አላማ በወደፊቱ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች እና ተመሳሳይ ስራ ለሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች የሚሰጠው ስልጠና ጥራት እና ብቃትን የማስጨበጥ አሰራር ላይ በመሆኑ እና ከእናቶች ጤና ጋር በተያያዘ ብዙ ሳይንሳዊ ጥናቶችም ስለሚቀርቡ ክልላችንም ከዚህ ብዙ ጥቅም እንደሚያገኝ አንጠራጠርም፡፡ ምክንያቱም በትግራይ ክልል ብቻም ሳይሆን እንደሀገር የእናቶች ጤና ምን ይመስላል? እስከአሁን ድረስስ ምን ተሰራ? ወደፊ ትስ ምን ማሻሻል ይገባናል የሚለውን ለመነጋገር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ የትግራይ ክልልም ከዚህ መነሻ ሀሳብ በመነሳት የምእተ አመቱን ግብ ለማሳካት የጀመረውን አሰራር አጠናክሮ የሚቀጥልበትን እድል ይፈጥራል ብለን እናምናለን፡፡

የትግራይ የእናቶች ጤናን ሁኔታ ስንመለከተው ቀደም ባለው ጊዜ በተለያየ ምክንያት ብዙ ጦርቶች የተካሄዱባት እንደመሆኑዋ ብዙ የጤና ተቋም ያልነበራት ናት፡፡ እንዲሁም ትግራይ ተፈጥሮአዊው አቀማመጡዋ ተራራማ በመሆኑ የእናቶች ጤናን በተመለከተ ብዙ ችግር ስታስተናግድ የቆየች ናት፡፡ በዚህም ሳቢያ ከፍተኛ የሆነ የእናቶች ሞት ያለባት ነበረች፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በትግራይ ክልላዊ መንግስትና ጤና ቢሮ እንዲሁም በፊደራል መንግስት ትብብር ወደ 13 ሆስፒታል፣ ወደ 211 ጤና ጣቢያና ወደ 600 ጤና ኬላዎች የሰው ሓይልና የህክምና መሳሪያ ተሟልቶላቸው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ የጤና ኤክስንሽን ባለሙያዎችም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ደግሞ የእናቶች የጤና የልማት ሰራዊት በሚባል ቡድን እናቶች ተደራጅተው እርጉዝ እናቶች በሕክምና ተቋም እንዲወልዱ እና እናቶች ተሰብስበው ስለጤናቸው እሚወያዩበትን መድረክ ስለፈጠረ የእናቶች ጤና በአሁኑ ወቅት ተሸሽሎአል ማለት ይቻላል፡፡ በሚቀጥለው ጊዜም የምእተ አመቱን ግብ ለማሳካት የተሻለ መስራት እንደሚጠበቅብን እናምናለን፡፡” ብለዋል የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ያለም ጸጋዬ፡፡

በመቀሌ ከተማ በተካሄደው 20ኛው አመታዊ የኢሶግ ጉባኤ ላይ የማህበሩ አባላት እንዲሁም ተባባሪ አባላት እና ከኢሶግ ጋር የሚሰሩ ድርጅቶች ተወካዮች በተጨማሪም ከተለያዩ ሐገራት ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው በመቀሌ ስለመካሄዱና የአመቱን የትኩረት አቅጣጫ በሚመለከት የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ይርጉ ገ/ሕይወት ለአምዱ ሪፖርተር ቀጣዩን ተናግረዋል፡፡

.. የኢሶግ አመታዊ ስብሰባ የተለያዩ ሳይንሳዊ የሆኑ የምርምር ውጤቶች የሚቀርቡበት ፣ወቅታዊ እና የማህበሩን የውስጥ ጉዳዮች በሚመለከት ውይይት የሚካሄድበት ነው፡፡ ኢሶግ ላለፉት 18 አመታት ያህል ከአዲስ አበባ ሳይወጣ ጉባኤዎችን ያካሄደ ሲሆን በዚህ ሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ግን በተለያዩ ክልሎች ጉባኤውን አካሂዶአል፡፡ ኢሶግ 19 ኛውን ጉባኤ ባለፈው አመት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መስተዳድር በአዋሳ ከተማ ያካሄደ ሲሆን 20ኛውን ጉባኤውን ዘንድሮ በትግራይ ክልላዊ መስተዳድር መቀሌ አድርጎአል፡፡ ጉባኤውን በየክልል መስተዳድሩ ማካሄድ አባላቱ በቀጥታ በጉባኤው በሚነሱ ሀሳቦች ላይ ትኩረታቸውን አድርገው እንዲሳተፉ የሚረዳ ከመሆኑም በላይ ከክልሉ አሰራር ጋር ለልምድ ልውውጥ እንዲሁም አካባቢውን ለማያውቁት እንደጉብኝትም የሚቆጠር ነው፡፡

ለአንድ ሀገር ትልቁ ሀብት ህዝቡ ሲሆን የሰለጠነ የሰው ሀብት ሲኖር ደግሞ ለእድገትም ይረዳል ፡፡ የዘንድሮው 20ኛው የኢሶግ ጉባኤ መሪ ትኩረት ያደረገው የጽንስና ማህጸን ሕክምናን የሚሰጡ ባለሙያዎች የወደፊት ስልጠና ምን መምሰል አለበት የሚል ነው፡፡ የእናቶችንና የተወለዱ አራስ ልጆችን ሞት ለመቀነስ እንዲሁም የእናቶችን ጤና ለመጠበቅ ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ሐይል በየደረጃው በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እና ጤና ተቋማት ማዳረስ አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም ሁለት ነገሮች አስፈላጊዎች ናቸው ፡፡

የጤና አገልግቱን ሽፋኑን ከፍ ማድረግ  ...ሽፋኑን ከፍ ማድረግ አስፈላጊ ከሆነ አሁን በተያዘው አቅጣጫ መካከለኛ የሆኑ የጤና ሙያተኞችን በብዛትና በብቃት በተፋጠነ ሁኔታ በማሰከልጠን አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል...

የጽንስና ማጸንን ሕክምና በተመለከተ መካከለኛ ደረጃ ላይ ባሉ የጤና ባለሙያዎች  ሁሉም አይነት አገልግሎት ተሰጥቶ የሚያበቃ ስላልሆነ ከፍተኛ የሆኑ የጤና ሙያተኞችን ማሰልጠን...ተገቢ ነው፡፡

የዘንድሮው የኢሶግ አመታዊ የትኩረት አቅጣጫ ከላይ እንደተገለጸው የእናቶችንና የህጻናቱን ጤንነት ከማስጠበቅ አንጻር በህክምና አሰጣጥ ረገድ ደረጃውን የጠበቀ የስልጠና ስራ መስራት ተገቢ ስለሚሆን የወደፊቱን የእናቶችን እና አዲስ የተወለዱ ጨቅላዎችን ጤንነት  ከግምት ያስገባ ነው እንደ ዶ/ር ይርጉ ገ/ሕይወት የኢሶግ ፕሬዝዳንት ማብራሪያ፡፡

20ኛው የኢሶግ አመታዊ ጉባኤ ከስነተዋልዶ ጤና አጠባበቅ አኩዋያ የተለያዩ ሳይንሳዊ የምርምር ስራዎች የቀረቡበት ሲሆን በተለይም ከአመታዊ የትኩረት አቅጣጫ ጋር በተያያዘ ዶ/ር ተግባር ይግዛው ከ  JHPIEGO ያቀረቡትን እንደሚከተለው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የስልጠና ጥራትን በማሻሻል ደረጃ ያለውን እንቅስቃሴ ስናየው በባለሙያውም ደረጃ ቢሆን ቁርጠኝነቱ ትንሽ ደከም ያለ ነው፡፡ አገሪቱ ምንም እንኩዋን እድገትዋ ዝቅተኛ ቢሆን እና የስልጠና ጥራቱ እና ትምህርት አሰጣጡ ችግር አለው ቢባልም ብዙ ጥሩ የሚባሉ ስልጠናና የትምህርት አሰጣጥን ያሻሻልንባቸው መንገዶች አሉ፡፡

በባለሙያውም፣ በትምህርት ተቋማትም ፣በመንግስትም ፣በህብረተሰቡም የሚሰማው ከትምህርት ተቋማት የሚወጡት የጤና ባለሙያዎች ያላቸው የብቃት ደረጃ የሚፈለገውን ያህል አይደለም የሚል ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ስራ ላይ ላሉ ባለሙያዎች የሚሰጠው ስልጠና ጥራቱን የጠበቀ እንዳልሆነ የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ስለዚህ በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠውን የህምና ትምህርት እንዲሁም ስራ ላይ ላሉት የህክምና ባለሙያዎች የሚሰጠው ስልጠና ብቃትን ማረጋገጥ የሚያስችል አቅም ያለው ሊሆን ይገባል፡፡ የጤና ባለሙያው የታማሚዎችን ችግር ሊፈታ የሚችለው ስራውን ለመስራት የሚያስችል አመለካከትና ብቃት ሲኖረው እንዲሁም በችሎታው ሲተማመን ነው፡፡ ስለዚህ ከአለም አቀፉ አሰራር የምንወስደው ልምድ በስፋት ቢሰራበት የሚፈለገውን የስልጠና ብቃትና ጥራት ማምጣት ስለሚቻል የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ፣አዋ ላጅ ነርሶች እንዲሁም በተመሳሳይ ስራ ላይ ያሉትን ባለሙያዎች ክህሎት ማዳበር ያስችላል፡፡

ትምህርት ወይንም ስልጠና በሚፈለገው አቅጣጫ እንዲሄድ የሚመሩ Standards እንዲኖሩ ማድረግ፣

የስርአተ ትምህርቱ ቀረጻ ትምህርቶችን ወይንም ብዙ ርእሶችን በመሸፈን ለማስተማር ብቻ ከሚጥር በትክክል ችሎታን በሚያስጨብጥ ደረጃ ቢቀረጽ ፣

ትምህርት የሚሰጥበት መንገድ አሳታፊ ቢሆንና የተማሪ ምዘናውን ጠንካራራ ማድረግም አስፈላጊ ነው፡፡

የስልጠናው ወይንም የትምህርቱን ጥራራት ማስጠበቂያ ዘዴው ምን እንደሚመስል መመልከት ፣ የሚማረው ወይንም የሚሰለጥነው ባለሙያ በእርግጥ ጥራራት አለውን ? በሚል መመርመርና ጥራራትን ለማሻሻል የሚረዳ አሰራራር መዘርጋት ይገባል... ዶ/ር ተግባር ይግዛው ከ JHPIEGO እንደገለጹት፡፡

 

 

Read 2593 times Last modified on Saturday, 04 February 2012 12:47