Saturday, 04 February 2012 12:41

“ሀኒሙን” እና “ደርቢ” ፊልሞች ይመረቃሉ

Written by  መልካሙ ተክሌ (melkamutekele@gmail.com)
Rate this item
(0 votes)

በኢሳግ ፊልም ፕሮዳክሸን የተሰራው “ሀኒሙን” እና በኦክቴት ፒክቸርስ የተሰራው “ደርቢ” የአማርኛ ፊልሞች ነገ ይመረቃሉ፡፡“ሃኒሙን” በኢሳያስ ግዛው ተፅፎ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ሽመልስ አበራ፣ ተስፋ ብርሃኔ፣ ፍፁም ፀጋዬ፣ ችሮታው ከልካይ፣ ካሌብ ዋለልኝ እና ሌሎች ተውነውበታል፡፡ የ110 ደቂቃ ፊልሙ ለዝግጅት ስድስት ወር ፈጅቷል፡፡ ይሄ ልብ አንጠልጣይ የፍቅር ፊልም  ከነገው የአዲስ አበባ ምርቃት በተጨማሪ የፊታችን ሰኞ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በልዩ ዝግጅት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ይመረቃል፡፡ይህ በዚህ እንዳለ በአንዱአለም ጌታቸው ተፅፎ የተዘጋጀው “ደርቢ” የተሰኘው የ90 ደቂቃ ፊልም ነገ በአዲስ አበባ በሚገኙ ሲኒማ ቤቶች ይመረቃል፡፡ መኮንን ላዕከ፣ ዘሪሁን አስማማው፣ ሰገን ይፍጠር፣ ሜሮን ጌታቸውና ሌሎች የተወኑበት ፊልም ባለፈው ሐምሌ 15 ቀን 2003 ዓ.ም ተመርቆ ለአንድ ቀን ብቻ የታየ ሲሆን በፕሮዲዩሰሮች መካከል በተፈጠረ አለመግባባትና በነበረው የድምፅ ችግር አዲስ ቀረፃ በማስፈለጉ እንደ አዲስ መቀረፁን አዘጋጆቹ ለአዲስ አድማስ ገልፀው አለመግባባቱ መፈታቱንም ተናግረዋል፡፡ ነገ ከቀኑ 8 ሰዓት በሲኒማ አምባሳደር እንዲሁም በሌሎች የግልና የመንግስት ሲኒማ ቤቶች በ8፣10 እና 12 ሰዓት ይመረቃል፡፡

 

 

Read 1796 times Last modified on Saturday, 04 February 2012 12:44