Friday, 11 September 2015 09:52

የናይጀሪያው መሪ በባንክ ያለኝ 100 ሺህ ፓውንድ ብቻ ነው አሉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  የስልጣን ዘመናቸውን 100ኛ ቀን ባለፈው ሳምንት ያከበሩት አዲሱ የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ፤ በባንክ ሂሳብ ደብተራቸው ውስጥ ያለው ገንዘብ 100 ሺህ ፓውንድ ብቻ መሆኑን በይፋ መግለጻቸውን ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡
ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ከዚህ ገንዘብ ውጭ ያላቸው ንብረት በጭቃ የተሰሩትን ሁለት ቤቶቻቸውን ጨምሮ አምስት የመኖሪያ ቤቶችና 270 ከብቶች ያሉበት የእርሻ ቦታ ብቻ መሆኑን እንደገለጹ የጠቆመው ዘገባው፤ሰውዬው ያላቸው ሃብት ከተራው የናይጀሪያ ህዝብ እጅግ የበዛ ቢሆንም፣ በመካከለኛና በከፍተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ዜጎች ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ገልጧል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ የግል ሃብታቸውን ይፋ ማድረጋቸው ከዚህ ቀደም አገሪቱን ሲመሩ ከነበሩና የህዝቡን ሃብት ወደ ካዘናቸው በማስገባት ከሚታሙ እጅግ ባለጸጋ ፕሬዚዳንቶች የተለዩ መሆናቸውን ለማሳወቅ ነው ተብሏል፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው፤ከቡሃሪ ሃብት 9 እጥፍ የሚበልጥ የ900 ሺህ ፓውንድ ባለቤት መሆናቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ቡሃሪ ስልጣን በያዙ ማግስት ከመንግስት ካዘና 100 ቢሊዮን ዶላር መንትፈው የግል ሃብታቸው አድርገዋል በሚል የሚታሙትን ሙሰኛ የአገሪቱ ባለስልጣናት ለፍርድ ለማቅረብ እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በ1980ዎቹ የአገሪቱ ወታደራዊ መሪ የነበሩት ቡሃሪ፤በስልጣን ዘመናቸው ከሙስና የጸዱ መልካም ሰው እንደነበሩ የጠቆመው ዘገባው፣ናይጀሪያን ለአምስት አመታት ያህል አንቀጥቅጠው የገዙት አምባገነኑ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳኒ አባቻ በአንጻሩ 3 ቢሊዬን ፓውንድ ሃብት እንደነበራቸውና አብዛኛውን ገንዘባቸውን በስዊዝ ባንክ እንዳስቀመጡት አስታውሷል፡፡

Read 1323 times