Friday, 11 September 2015 09:50

የአሜሪካ ፖሊስ “አፕል” መረጃ አልሰጥም በማለቱ ይከሰስ እያለ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     ፖሊስ በአይፎን ተጠቃሚ የወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ ጀምሯል
             ማይክሮሶፍትም የወንጀል ተጠርጣሪን ኢሜል ባለመስጠቱ ተከሷል
   የአሜሪካ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ከአደንዛዥ ዕጽ እና ከጦር መሳሪያ ጋር በተያያዘ ለምናደርገው ምርመራ የሚጠቅሙ የጽሁፍ መልዕክቶችን አሳልፎ ሊሰጠን አልፈቀደም ያሉት ታዋቂው የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል፤ፍርድ ቤት ቀርቦ ቅጣት የሚጣልበትን ሁኔታ እንዲያመቻችላቸው መንግስትን መጠየቃቸውን ኒውዮርክ ታይምስ ዘገበ፡፡
የኤፍቢአይ እና የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣናት፤ አፕል በሚያመርተው አይፎን አማካይነት ከሰዎች ወደ ሰዎች የተዘዋወሩ አጭር የጽሁፍ መልክቶችን ለወንጀል ምርመራ አሳልፎ አልሰጥም ብሎ በእምቢተኝነት በመጽናቱ ህጋዊ እርምጃ ይወሰድበት ሲሉ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጥያቄ ማቅረባቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ወንጀል መርማሪዎች የአፕል ምርት የሆነውን አይፎን በሚጠቀሙ የአደንዛዥ ዕጽ እና የጦር መሳሪያ ወንጀል ድርጊቶች ተጠርጣሪዎች ዙሪያ ለሚያደርጉት ምርመራ የአጭር የጽሁፍ መልዕክቶቹ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው መናገራቸውም ተጠቁሟል፡፡
አፕል ከዚህ ቀደም ከፖሊስ ለቀረበለት ጥያቄ፣ የአጭር የጽሁፍ መልዕክቶቹ የተላለፉበት አይሜሴጅ የተሰኘ የመልዕክት መላላኪያ ሲስተሙ ነባር መረጃዎችን የሚያጠራቅምበት ቋት የሌለው በመሆኑ የተጠየቀውን መረጃ ስለማያገኝ አሳልፎ መስጠት እንደማይችል ማስታወቁን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ከአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ጋር በተያያዘ በተጠረጠረ አንድ ግለሰብ ዙሪያ ለሚደረግ የወንጀል ምርመራ ጠቃሚ የሆኑ የኢሜይል መልዕክቶችን አሳልፎ ሊሰጠው ባለመፍቀዱ ከማይክሮሶፍት ኩባንያ ጋር የፍርድ ቤት ክርክር እያደረገ እንደሚገኝም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1405 times