Friday, 11 September 2015 09:49

ማይክል ጆርዳን በካሳ የሚያገኘውን 8.9 ሚ. ዶላር ለበጎ አድራጎት ሊለግስ ነው አሜሪካዊቷ ሚሊየነር በበኩሏ ለወፎቿ 100 ሚ ዶላር አውርሳለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አሜሪካዊው ታዋቂ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ማይክል ጆርዳን፤ያለ ፈቃዴ ዝናዬን ተጠቅሞ ሃብት አፍርቷል ባለው አንድ ኩባንያ ላይ ለመሰረተው ክስ በካሳ መልክ እንዲከፈለው በፍርድ ቤት የተወሰነለትን 8.9 ሚሊዮን ዶላር ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሊለግስ እንደሆነ ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
የ52 አመቱ ጆርዳን፤ሴፍዌይ የተባለው የአሜሪካ የምግብ አምራችና አከፋፋይ ኩባንያ፣ ሳያስፈቅደኝ ምስሌን ለምርቶቹ ማስታወቂያ ተጠቅሟል፣ ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ካሳ ሊከፍለኝ ይገባል በሚል የመሰረተውን ክስ ሲመረምር የቆየው ፍርድ ቤት፤ 8.9 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈለው ወስኗል፡፡
ቺካጎ ውስጥ የተሰየመው ችሎት፤ውሳኔውን ማሳለፉን ተከትሎ ጆርዳን ለጋዜጠኞች እንደተናገረው፤ጉዳዩ ክብርን የማስጠበቅ እንጂ በካሳ ገንዘብ የማግኘት አለመሆኑን ጠቅሶ፣ ኩባንያው የሚሰጠውን 8.9 ሚሊዮን ዶላር የካሳ ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ለበጎ አድራጎት ተግባር እንደሚያውለው አስታውቋል፡፡ ነዋሪነቷ በኒውዮርክ ኢስት ሀምፕተን የሆነው አሜሪካዊቷ ሚሊየነር ሌስሊ አን ማንዴል በበኩሏ፤4 ሚሊዮን ዶላር በሚያወጣው እጅግ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቷ ውስጥ ለምታረባቸው 32 ወፎች፣ 100 ሚሊየን ዶላር ማውረሷን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ሚሊየነሯ በፈረመችበት ህጋዊ የውርስ ሰነድ ላይ፣ ወፎቼ ጎጇቸው በሳምንት ሁለት ጊዜ እየተጸዳላቸውና ከሱፐርማርኬት ደረጃቸውን የጠበቁ ጣፋጭ ኬኮች፣ ካሮትና ፈንድሻ እንዲሁም የተጣራ ውሃ እየተገዛላቸው በአግባቡ እየተመገቡ እንዲኖሩ እፈልጋለሁ ብላለች፡፡
እ.ኤ.አ በ2007 ሊዎና ሄልምስሌ የተባለች በሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማረች አሜሪካዊት ሚሊየነር ለአንድ ውሻዋ 12 ሚሊየን ዶላር ማውረሷንም ዘገባው ጨምሮ አስታውሷል፡፡

Read 1813 times