Friday, 11 September 2015 09:29

“ጨለማው እንደ ቀን…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ከዘመን ዘመን በሰላም አሸጋገራችሁማ!
ሌሊቱ እንደ ጎሕ ቀደደ፣ ጨለማው እንደ ቀን ጠራ
እንደ ውቅያኖስ ዕፅዋት፣ እንደ ጠፈር ኮከብ ደራ
ምድር ሥጋጃ ለበሰ፣ የጌጥ አልባሳት ተቀባ
ሰማይ በዕልልታ አስተጋባ
እዮሀ መስከረም ጠባ፡፡
አዲሱን ዓመት እንደ ፀጋዬ ስንኞች ያሳምርልንማ!
እሷዬዋ ምን አለች መሰላችሁ… “የአዲስ ዓመት ዕቅዴ ጥሩ፣ ጥሩ ምግብ ለመመገብ ነው፡፡ ስለዚህ የምይዛቸው ቦይፍሬንዶች አሪፍ፣ አሪፍ ምግብ ቤት እየወሰዱ የሚጋብዙኝ ብቻ ናቸው፡፡”
ጥቆማ…እንትናዎች እንትናዬዎቻችሁ “ለምን እንትን ሬስቱራንት አትጋብዘኝም!” እያሉ የቦሌና የኤድና ሞል ሰፈር ሬስቱራንቶችን ስሞች መጥራት ካበዙ…አለ አይደል… “አመጋገብን በተመለከተ የአዲስ ዓመት ዕቅድሽ ምንድነው?” ብላችሁ ጠይቋቸውማ! ቂ…ቂ….ቂ…
እሱዬው ቢያቅድ ምን ይል ይመስለኛል መሰላችሁ… “የዘንድሮ ዕቅዴ ብላክ ፎረስት ኬክ ሳዝላት እኔ ከቦምቦሊኖ ሌላ አልበላም የምትል፣ ካፑቺኖ ሳዝላት ‘ከሻይ በሎሚ ሌላ አልጠጣም’ የምትል፣ የሆነ የታወቀ ክትፎ ቤት እንሂድ ስላት ‘በእኔ በኩል ቀበሌ ሄደን አንድ በያይነቱ ለሁለት መብላት ነው የምፈልገው’ የምትል…” ምናምን የሚል ይመስለኛል፡፡ (“የዚች አይነቷን ሴት ገና ወደፊት በሚጻፍ ረጅም ልብወለድ ጠብቃት!” የሚሉ እንትናዎች እንደሚኖሩ ልብ ይባልማ!)
ደግሞላችሁ…እኛ ‘አርትኦት’ ቢጤ ሥሩበት ብንባል አንድ የምንጨምረው አለን ‘… የዛሬ ሳምንት እነሆ በረከት አንባባልም?’ ስላት፣ ‘የዛሬ ሳምንት ድረስ ምን አስኬደህ፣ ዛሬ የማንን ጎፈሬ ታበጥራለህ?’  የምትል፡፡
ነጋ፣ የአዲስ ዘመን ችቦ፣ ምድር ሕይወት አፈለቀች
የምሥራች አዝርእቷን፣ አዲስ ቡቃያ ወለደች
የአደይ አበባን ለገሰች
ለአዲስ ዘመን አዲስ ብርሃን፣ አዲስ መስከረም ገበየች፡፡
አዲሱን ዓመት እንደ ፀጋዬ ስንኞች ያሳምርልንማ!
እናላችሁ…የሚያሳስቡን ነገሮች በበዙበት በዚህ ወቅት መልካም መልካሙን መመኘት ይሻላል፡፡ ዘንድሮ በብዙ ነገሮች ላይ ማቀድ “ላም አለኝ በሰማይ…” ሊሆን ቢቃረብም ቢሆኑና፣ ባይሆኑ የምንፈልጋቸው ነገሮች መአት ናቸው፡፡ ‘የሰማይ ስባሪ’ የሚያካክሉትን ጉዳዮች ለጊዜው ትተን ስለማህበራዊ ግንኙነቶቻችን ስናስብ ቢሻሻሉልን የምንፈልጋቸው ነገሮች አሉ፡፡
ታዲያላችሁ…ብዙ ጊዜ ሦስትም ሆነ አሥራ ሦስት ሆነን ስናወራ አንድ የምናነሳው ነገር የእርስ በእርስ ግንኙነት መበላሸቱ ነው፡፡ “ሰዉ ሁሉ አውሬ ሆኗል!” እንባባላለን፡፡ የምር እኮ…ትናንት አምስት ትከሻ ያለው ይመስል ‘አቅፈነው የማንጠግበው’ን ሰው ዘንድሮ ስንጨብጥ እንኳን እየተጠራጠርን ነው፡፡ የምር እኮ…አለ አይደል…“ምን አድርጎህ ነው እከሌን ፊት የነሳኸው?” ብንባል ብዙዎቻችን መልሳችን “ልጄ፣ ዘንድሮ ማን ይታመናል?” ነው እንጂ…
“አገሩ ሄዶ አስተብትቦብኝ መጣ…”  
“በመከራ ያገኘኋትን እንትናዬን እያባበለብኝ ነው…”  
“በሦስት ጉንጩ ነው የሚበላው ብሎ አወራብኝ…”
“ከእነእንትና ጋር ውስኪ ሲጠጣ ነው የሚያድረው ብሎ አስጠቆረኝ…”
ምናምን የምንለው ነገር የለንም፡፡
እናማ…መጪው ዓመት በምኑም፣ በምናምኑም እርስ በእርሳችን የምንጠራጠረውን ነገር ይቀንስልንማ፡፡ (በነገራችን ላይ… አለ አይደል…‘ሳንጠረጠር የምንመነጥር’ም በዝተናል፡፡)
የአዲስ ዘመን ችቦ
በመስከረም ሰብል አብቦ
ክዋክብቱን ፈነጠቀ
ርችቱን አንጸባረቀ ተኳለ አዲስ ደመቀ
አዲሱን ዓመት እንደ ፀጋዬ ስንኞች ያሳምርልንማ!

ትዳሮች በሦስተኛ ወገኖች ጣልቃ ገብነት የማይፈርሱበት ዘመን ይሁንልንማ፡፡ ጥናት ምናምን ባይኖርም ብዙ ትዳሮች በአማቶች የተነሳ እየፈረሱ ነው የሚባል ነገር አለ፡፡ ልጄ…ወላጆች የልጃቸውን ትዳር ‘ጎጆ እንደመውጣት’ ሳይሆን እንደ ‘ኢንቬስትመንት’ ማየት ሲጀምሩ ዘመን እንዴት መላ ቅጡ እንደጠፋ ታውቃላችሁ፡፡
“ጓደኞችሽ መኪና ሲለዋውጡ አንቺ ከዚህ ለአውቶብስ እንኳን ከሚያርበት ጋር ምን ያቆራምድሻል!” የሚሉ አማቶችን ልብ የሚያስገዛ ዘመን ይሁንልንማ፡፡
ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው አማቱን አሟቸው ሆስፒታል ይዟቸው ይሄዳል፡፡ እናላችሁ…ዶክተሩ ምርመራ ካደረገ በኋላ…
“አዝናለሁ፣ ግን አማትህ የልብ ድካም ገጥሟቸዋል…” ይለዋል፡፡ ሰውየውም…
“ዶክተር፣ እንደሱማ ሊሆን አይችልም፡፡ ተሳስተሀል፡፡”
“ተሳስተሀል ስትለኝ ምን ማለትህ ነው?”
“ዶክተር፣ ካልጠፋ ሰው የእኔ አማት እንዴት ልብ ድካም ሊገጥማት ይችላል… መጀመሪያ መቼ ልብ አላትና!” ብሎት አረፈ አሉ፡፡ ‘ጣልቃ ገብ’ አማት ናቸው ማለት ነው፡፡
ይቺንም ስሙኝ…እሷና እሱ በሆነ ጉዳይ ተጋጭተዋል፡፡ እና አንድ እሁድ ወደ ገጠር አካባቢ እየሄዱ ነበር፡፡ ሁለቱም ለንቦጫቸውን ጥለዋል፡፡ ታዲያላችሁ… በሆነ የአንድ አርሶ አደር በረት በኩል ሲያልፉ አህዮች፣ አሳሞች ምናምን ያያሉ፡፡ ይሄን ጊዜ ሚስትየው በበፊት ብሽሽቃቸው ተናዳ ስለነበር ወደ እንስሶቹ እያመለከተች ምን ትለዋለች…
“እነኛ ዘመዶችህ ናቸው?” ትለዋለች፡፡
እሱም ምን ቢላት ጥሩ ነው… “አዎ፣ በሚስቴ በኩል…” ብሏት እርፍ፡፡
አዲሱን ዓመት ቃላችንን የምንጠብቅበት ያድርግልንማ!
ይቺን ስሙኝማ…አንድ ፖለቲከኛ ለሆነ ስብሰባ ይረፍድበታል፡፡ መኪናውን እያከነፈ ሄዶ ስብሰባው ስፍራ ሲደርስ የመኪና ማቆሚያ ክፍት ቦታ ያጣል፡፡ ይሄን ጊዜ ወደ ሰማይ እያየ ምን ይላል… “አምላኬ እባክህ ክፍት ቦታ አግኝልኝ፡፡ መኪና ማቆሚያ ቦታ ካስገኘህልኝ ከእንግዲህ ቤተክርስትያን ለመሳለም፣ መጠጥ ለማቆም፣ ለእኔና ለቤተሰቤ ብቻ ሳይሆን ለህዝብ ለመሥራት ቃል እገባለሁ…” ብሎ እንደጨረሰ ክፍት ቦታ ያያል፡፡ ቀና ብሎ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ፈጣሪ ሆይ ቦታውን ያገኘሁት እኔ ስለሆንኩ ያልኩትን ሁሉ እርሳው…” ብሎት አረፈ፡፡
አዲሱን ዓመት ሰውንም፣ ፈጣሪንም የማንክድበት ያድርግልንማ!
የአደይ ችቦ እየፋመ፣ እየጋመ
እዮሀ እያስገመገመ፣ እየተመመ
የመስቀል ደመራ
በራ
አዲሱን ዓመት እንደ ፀጋዬ ስንኞች ያሳምርልንማ!
የእውነትም አዲስ ዓመት…ከልባችን “ጨለማው እንደ ቀን…”
መልካም አዲስ ዓመት፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2670 times