Saturday, 05 September 2015 08:44

አቶ ሀብታሙ አያሌው በማረሚያ ቤትይቆዩ ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

      ከተከሰሱበት የሽብር ክስ ፍ/ቤት በነፃ ያሰናበታቸውን የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አቶ ሀብታሙ አያሌውን ማረሚያ ቤቱ ለምን ከእስር እንዳልለቀቃቸው ፍ/ቤት ቀርቦ ያስረዳ ሲሆን ጉዳዩን  የተመለከተው ችሎት፤ ተከሳሽ እስከ ይግባኝ ቀጠሮ ድረስ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
ተከሳሹ ነሐሴ 27 ቀን 2007 ዓ.ም ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የፃፉትን አቤቱታ መሰረት አድርጎ ነበር ችሎቱ በትናንትናው እለት ተከሳሹና የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ቀርበው ስለ ጉዳዩ እንዲያስረዱ ያዘዘው፡፡
አቶ ሀብታሙ ለችሎቱ በፅሁፍ ባቀረቡት አቤቱታ፤ ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም ጉዳያቸውን ሲመረምር የነበረው ፍ/ቤት፣ በነፃ እንዳሰናበታቸው ጠቅሰው ማረሚያ ቤቱ ከእስር ሊለቃቸው ያልቻለበትን ምክንያት ፍ/ቤት ቀርቦ እንዲያስረዳላቸውና አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድላቸው ጠይቀው ነበር፡፡
በትናንትናው እለት ተረኛ ችሎት የቀረቡት የማረሚያ ቤቱ ተወካይ ኃላፊ፤ ተከሳሹ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ የተደረገው የጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ትዕዛዝን በማክበር ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
“ተከሳሹ አቶ ሀብታሙ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ የተደረገው፣ በነፃ በተሰናበቱ ማግስት አቃቤ ህግ ይግባኝ በመጠየቁና ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ፣ ተከሳሹ እስከ ይግባኝ ቀጠሮ ጥቅምት 21 ቀን 2008 ዓ.ም በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ በማስተላለፉ ነው” ብለዋል - የማረሚያ ቤቱ ተወካይ ኃላፊ፡፡ በተጨማሪም ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤቱ በከፍተኛው ፍ/ቤት የተደረገው ክርክር ግልባጭ እንዲቀርብ ማዘዙን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ ተከሳሹ አቶ ሀብታሙ በበኩላቸው፤ ከፍተኛው ፍ/ቤት በነፃ ካሰናበታቸው በኋላ ለምን ታስረው እንደቆዩ እንዲገለፅላቸው የአስተዳደር አካላትን በደብዳቤም ጭምር መጠየቃቸውን ጠቁመው ኃላፊዎቹን ግን “መልስ ለመስጠት አንገደድም” በሚል ምክንያቱን ሳያስረዱኝ ቀርተዋል፤  ያልተፈታሁበት ምክንያት ለኔም ሆነ ለቤተሰቤ ባለመገለፁ፣ ቤተሰቦቼ ላይ ከፍተኛ እንግልት ደርሷል” ሲሉ ቅሬታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
“ቤተሰቦቼ እኔን ለማስፈታት በመጡ ጊዜ እስከ ምሽት ድረስ ይፈታል ጠብቁ ተብለው ተንገላተዋል” ብለዋል - ተከሳሹ ለችሎቱ፡፡
የማረሚያ ቤቱ ተወካይ ኃላፊ በበኩላቸው፤ ተከሳሹ ያልተፈቱበት ምክንያት ተገልፆላቸዋል፤ ከቤተሰብ አካላት በጉዳዩ ላይ ጥያቄ ያቀረበ ግን የለም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም ያህል ጉዳዩን መርምሮ ብይን የሰጠው ፍ/ቤቱ፤ ተከሳሹ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ የተደረገበት ምክንያት ከማስረጃ ጋር የተደገፈና በቂ ማብራሪያ የቀረበበት በመሆኑ፤ በማረሚያ ቤት ቆይተው ጉዳያቸውን በጠቅላይ ፍ/ቤት ወንጀል ይግባኝ ሰሚ ችሎት እንዲከታተሉ ብይን ሰጥቷል፡፡
የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ሀብታሙ አያሌውን ጨምሮ በእነ ዘላለም ወ/አገኘሁ የክስ መዝገብ በሽብር ከተከሰሱት 10 ግለሰቦች መካከል አምስቱ በነፃ እንዲሰናበቱ ከፍተኛ ፍ/ቤት ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም ብይን መስጠቱ ይታወሳል፡፡

Read 2577 times Last modified on Saturday, 05 September 2015 14:57