Saturday, 05 September 2015 08:38

የሜዲካል ቱሪዝም- (ህክምናና ጉብኝት)

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ አገራት በየዓመቱ ከ100 ቢ. ዶላር በላይ ገቢ ያገኛሉ
    በግራ እግሩ ጣቶች ላይ የጀመረው የህመም ስሜት እያደር እየበረታና እየጠነከረ መሄዱ ቢሰማውም እንዲህ ለከፋ ደረጀ ያደርሰኛል ብሎ ለአፍታም አስቦ አያውቅም፡፡ ከዛሬ ነገ ይሻለኛል እያለ ስሜቱን ችላ ቢለውም ህመሙ ዕለት ከዕለት እየጨመረ መሄዱ አሳሰበው፡፡ ሁኔታው ሲከፋበትም ወደ ሃኪም ዘንድ ሄደ፡፡ በሽታውን የመረመሩት ሃኪሞች የተለያዩ መድሃኒቶችን በማዘዝ፣ ህመሙን ለማስታገስና ከበሽታው ለመፈወስ ጥረት ቢያደርጉም በቀላሉ ሊሳካለቸው አልቻለም፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድና ድካም በኋላ በሽታው የአጥንት ካንሰር መሆኑንና ህክምናውም እዚህ አገር እንደማይሰጥ ነግረው፣ ወደ ውጪ አገር ሄዶ እንዲታከም ፃፉለት፡፡ ለ32 ዓመቱ ወጣት ዳዊት ተስፋዬ ነገሩ ዱብዕዳ ነበር፡፡ ድንጋጤው መለስ ሲልለት ስለ ህክምናው ሁኔታና ህክምናው ስለሚሰጥባቸው አገራት መረጃ ማሰባሰብ ጀመረ፡፡ ታይላንድ፣ ሲንጋፖር፣ ህንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ላሉ የህክምና ተቋማት በኮሚሽን የሚሰሩ ኤጀንሲዎችን አግኝቶ ለህክምናው የሚያስፈልገውን የገንዘብ መጠን ማጠያየቅ ያዘ፡፡ በመጨረሻም ለህክምናው ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልገው ተነገረው፡፡ ገንዘቡ ከአቅሙ በላይ በመሆኑም ዋጋ ያወጡልኛል ያላቸውን ንብረቶቹን በመሸጥና ወዳጅ ዘመዶቹ የእርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉለት በመጠየቅ፣ ገንዘብ የማሰባሰቡን ተግባር ተያያዘው፡፡ ከተሳካለትም በመጪው አዲስ አመት መጀመሪያ ላይ በአንፃራዊነት የተሻለ ዋጋ ወደቀረበለት ህንድ ተጉዞ ህክምናውን ለማድረግ ዕቅድ ይዟል፡፡ እንዲህ እንደ ዳዊት በተለያዩ በሽታዎች የተያዙ በርካታ ዜጐች ህክምና ለማግኘት ወደ ታይላንድ፣ ቻይና፣ ሲንጋፖር፣ ህንድ፣ ደቡብ አፍሪካና ሌሎች የአውሮፓ አገራት ይጓዛሉ፡፡ የህክምና አገልግሎትን ለማግኘት ከአገር አገር ድንበር አቋርጦ የሚደረገው ጉዞም የህክምና (ሜዲካል) ቱሪዝም ተብሎ ይጠራል፡፡ የህክምና ቱሪዝም አገራት እጅግ ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙበት የቱሪዝም ዘርፍ ሆኗል፡፡ ሜዲካል ቱሪስቶች ጉዞአቸውን የሚያደርጉባቸው ምክንያቶች ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የሚሹትን ህክምና በአገራቸው ለማግኘት ያልቻሉ ሰዎች ህክምና ፍለጋ ወደ ሌሎች አገራት የሚንቀሳቀሱ ቢሆንም ዝቅተኛ የህክምና ክፍያ ፍለጋ አሊያም ወረፋ ላለመጠበቅ ህክምናውን በፍጥነት ወደሚያገኙባቸው ሌሎች አገራት የሚንቀሳቀሱ ሜዲካል ቱሪስቶችም አሉ፡፡ በርካቶች ለህክምና ከሚመርጧቸው የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ አገራት መካከል ብዙዎቹ በደቡብ ምሥራቅ እስያ ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ ጥቂት የአውሮፓ አገራትና ደቡብ አፍሪካም በሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻነታቸው የሚጠቀሱ አገራት ናቸው፡፡ አንዳንድ አገራትም በዓለማችን የተለያዩ አገራት ውስጥ ወኪሎቻቸውን አስቀምጠው የሜዲካል ቱሪስት ፍለጋውን እያጧጧፉት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የሜዲካል ቱሪዝም ዓለም አቀፍ ገበያ
በዓመት ከ100 ቢሊየን ዶላር በላይ ነው፡፡ በዓለማችን ህክምና ፈላጊ ቱሪስቶችን የሚያስተናግዱ አገራት ቁጥር 40 እንደሚደርስ የጠቆመው መረጃው፤ ህንድ፣ ብራዚል፣ ሲንጋፖር፣ ታይላንድ፣ ቻይና፣ ሀንጋሪ፣ ኮስታሪካ፣ ማሌዥያ፣ ሜክሲኮና ደቡብ አፍሪካ ዋንኛ የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ አገራት መሆናቸውን ገልጿል፡፡ እነዚህ አገራት እጅግ ከፍተኛ ዶላር በሚዝቁባቸው በልብ ቀዶ ጥገና፣ በአካል ንቅለ ተከላ፣ ውስብስብ በሆኑ የአጥንቶችና የመገጣጠሚያ ህክምናዎች፣ በጥርስ ህክምና፣ በካንሰር ህመሞች ህክምናና በፊት ቀዶ ህክምናዎች የተራቀቁ ናቸው፡፡ ከዋና ዋናዎቹ የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ አገራት መካከል አንዳንዶቹ ህመምተኞቻቸውን በአነስተኛ ዋጋ በማስተናገድ የሜዲካል ቱሪዝም የበለጠ የሚስፋፋባቸውን መንገዶች ሲፈልጉ ይስተዋላሉ፡፡ከእነዚህ አገራት ደግሞ ህንድ ቀዳሚነቱን ትይዛለች፡፡ ከልብ ጋር ለተያያዙ ህክምናዎች፣ ለሽንጥና ለመገጣጠሚያ ችግሮች ብዙዎች የሚመርጧት ህንድ፤ ረቀቅ ያሉ መሳሪያዎችንና ጥልቅ ዕውቀትን ለሚጠይቁት የህክምና አገልግሎት የምታስከፍለው ገንዘብ በአሜሪካና በእንግሊዝ ለተመሳሳይ ህክምና ከሚጠየቀው ገንዘብ አንድ አስረኛውን ብቻ ነው፡፡ የህንድ የጤና ከተማ እየተባለች
የምትጠራውና የደቡባዊዋ ህንድ ከተማ ቼናይ፣ ከተለያዩ የዓለማችን አገራት ጤናቸውን ፍለጋ የሚጓዙ በርካቶችን ታስተናግዳለች፡፡ 45 በመቶ የሚደርሱ ዓለም አቀፍ ታካሚዎችም ከደዌአቸው ለመፈወስ ይህችኑ ከተማ የሙጢኝ ብለዋል፡፡ አገሪቱ ከሜዲካል ቱሪዝም ዘርፍ የምታገኘው ዓመታዊ ገቢ ከ3 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል፡፡ ህንድ በመላው ዓለም ከሚገኙና የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ ከሆኑት አገራት መካከል በአንፃራዊነት ተመጣጣኝ ክፍያ የሚጠየቅባት አገር ነች፡፡ እንደ ህንድ ሁሉ ታይላንድም ተመጣጣኝ በሆነ ክፍያ ህክምና የሚገኝባት የሜዲካል ቱሪዝም
መዳረሻ አገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ በተለይ ከውበት ጋር ለተያያዙ ቀዶ ጥገናዎችና ለአዕምሮ
ህክምናዎች ታይላንድ ተመራጭ አገር መሆኗን የጤና ድርጅቱ መረጃ ያመለክታል፡፡ የተለያዩ አገራት
ባለስልጣናትና ታዋቂ ግለሰቦች ህክምና ፍለጋ የሚጓዙባት ታይላንድ፤ አለምአቀፍ እውቅና ያላቸውና
ደረጃቸውን የጠበቁ ሆስፒታሎችም አሏት፡፡ ደቡብ አፍሪካም በውበት ቀዶ ጥገና ህክምናዋ የምትታወቅና በበርካታ አሜሪካውያንና አውሮፓውያን የምትጐበኝ የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ አገር ነች፡፡ የጡት ማሳነስ፣ ማስተለቅ፣ የከንፈርና የአፍንጫ ማስተካከል፣ የውፍረት መጨመርና መቀነስ ህክምናዎች በደቡብ አፍሪካ በስፋት ይሰጣሉ፡፡ አገሪቱን ለሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻነት ተመራጭ ያደረጓት የሚሰጡት የህክምና ዓይነቶች ብቻ ሳይሆኑ የህክምና ክፍያው ተመጣጣኝነትም ጭምር ነው፡፡ እነዚህ የውበት ማስተካከያ ህክምናዎች ከአውሮፓና ከአሜሪካ ዋጋቸው በግማሽ ይቀንሳል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት ያደረገውንና በአሜሪካ የሚገኘውን የደልዌር ዩንቨርሲቲ ጥናት ጠቅሶ የአለም ጤና ድርጅት መረጃ እንዳመለከተው፤ ለተለያዩ የጤና እክሎችና ለውበት የሚደረጉ ህክምናዎችን በህንድ፣ በታይላንድና በደቡብ አፍሪካ ማካሄድ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚደረገው ህክምና ከሚጠይቀው ወጪ ከግማሽ በታች ይጠይቃል፡፡
 ህሙማኑ በእነዚህ አገራት ለሚያደርጉት ህክምና የሚከፍሉት ገንዘብ፣ የሆቴልና የመዝናኛ ወጪዎቻቸውንም የሚያካትት መሆኑ ደግሞ የበለጠ ተመራጭ ያደርጋቸዋል፡፡ የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ በሆኑ አገራት ውስጥ የሚገኙት ሆስፒታሎች በአለም አቀፍ የጥራት ቁጥጥር ተቋማት እየተመዘኑ እውቅና የሚሰጣቸው ሲሆን በተለያዩ የአውሮፓና የአሜሪካ አገራት ውስጥ የሚሰጠውን የስፔሻላይዜሽን ትምህርት በተከታተሉ የህክምና ባለሙያዎች የተደራጁም ናቸው፡፡ እንደ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጣሊያንና ፈረንሳይ ያሉ አገራት ውስጥ የሚገኙ ህሙማን ምንም እንኳን ሕክምናው በአገራቸው ቢገኝም በአነስተኛ ዋጋ ለመታከምና አገር ለማየት ሜዲካል ቱሪስት መሆኑን ይመርጣሉ፡፡ በዚህ ሳቢያም የሜዲካል ቱሪዝም ዘርፍ እጅግ እየሰፋና ለየአገራቱም ከፍተኛ የገቢ ምንጭ እየሆነ መጥቷል፡፡     Read 3517 times