Saturday, 05 September 2015 08:33

ከሁለት የወለደ አይደሰት፤ሳይወልድ የሞተአስተዛዛኝ የለው

Written by 
Rate this item
(14 votes)

አንድ አንበሳ እያረጀ መጣ፡፡ ከሰፈር ወጥቶ ወደ ሌላ ጫካ መሄድ አቃተው፡፡ ልጆቹም ሆኑ ሚስቱ ብዙ ትኩረት የሚሰጡት ዓይነት አልሆኑም፡፡ ሲያረጁ አይበጁ እንዲሉ ሆኗል፡፡
ከዕለት ዕለት እየዛለ፣ እንደ ልብ መራመድም እያቃተው ሄደ፡፡
አንድ ቀን ልጆቹን ጠርቶ፤
“ልጆቼ! እኔ እናንተን ለማሳደግ በየጫካው ተንከራትቻለሁ፡፡ አድኜ መግቤያችኋለሁ! አደንም አስተምሬያችኋለሁ! መከበሪያችሁም ሆኛለሁ! ዛሬ ግን ሁላችሁም በእኔ ላይ ፊታችሁን አዞራችሁብኝ!”
“ኧረ ፊታችንን አላዞርንብህም አባባ! አንተ አርጅተህ ቤት ስትውል፤ ተሯሩጠን አድነን፣ ቤታችን ሞቅ እንዳለ እንዲቀጥል እየጣርን ነው፡፡ እንግዲህ አንተም ውጪ ውጪ ማለትህን ትተህ፣ ሰብሰብ ብለህ ተቀመጥ፡፡ መሞቻህ ከደረሰም እኛ ተንከባክበን እንቀብርሃለን!” አሉት ልጆቹ፤ እየተፈራረቁ፡፡
“አይ ልጆቼ! እንኳን ሞት እርጅና አለ አይደለም ወይ?!”
“ለምን እንዲህ አልክ አባባ?” አለ አንደኛው ልጅ፡፡
“እርጅና በቁም መረሳት ነው ልጄ”
“እንዴት አባባ?” አለ ሌላኛው ልጅ፡፡
“ይሄው እናንተ የምታደርጉት ማስረጃ ነው! ጀማው ህብረተ-እንስሳን ተመልከቱ - ዞር ብሎ የሚያየኝ ጠፋ! ንጉሳቸው እንደነበርኩ የሚያስታውስ፣ ውለታዬን ከቁም ነገር የሚቆጥር አንድ እንስሳ ጠፋ! ግን ልጆቼ፤ ሁሌ ልጅ ሆኖ አይኖርም - ሁላችሁም አንድ በአንድ ተራችሁን እያረጃችሁ ትሄዳላችሁ፤ ትረሳላችሁ፣ ትጣላላችሁ!”  አለ፡፡
“አሁን ምን እናድርግልህ አባባ?”
“አሁንማ እርስ በርሳችሁ ሳትከፋፈሉ፣ ሳትሻሙ፣ ሳትጣሉ፤ ተመካከሩ፡፡ እኔንም ሆነ በእኔ ዕድሜ ያሉትን ሁሉ አትናቁ፣ አትኮንኑ! የወደፊቱን ብታስቡ ከብዙ መዘዝ ትወጣላችሁ! አለበለዚያ ያለጊዜ ማርጀትም ይመጣል! ያ ደግሞ ከእርጅና የከፋ እርግማን፣ ከመርገምት ሁሉ የከፋ መርገምት ነው! የጋራ ጫካችንን እንዴት እናቆየው ብላችሁ ጨክናችሁና በቅንነት ካልተነጋገራችሁ ጫካውም ጫካ አይሆን፣ ቤታችሁም ቤት አይሆንም!”
“ታዲያ ምን ታወርሰናለህ?”
“እስካሁን የነገርኳችሁን ምክርና የእኔን የልጅነት ልብ!! ለማንኛውም ያለፈውን አትኮንኑ፣ እርስ በርስ አትካሰሱ! ከሁሉም በላይ ግን ዳኛ አያሳጣችሁ!” ብሎ አሸለበ፡፡
*           *         *
እርስ በርስ አለመተሳሰብ፣ አለመነጋገር፣ ነገር በሆድ መያዝ ክፉ ልማድ ነው፡፡ አባትህን መዘንጋት ደግ አይደለም፡፡ በውርስ መልክ መናቆርን መረከብ መርገምት ነው፡፡ “አያረጅ የለም አይለዋወጥ” የሚለውን ሁሌም ልብ ማለት ነው፡፡ በአንፃሩ አዲሱ መምጣቱ አይቀሬ ነው” (The New is Invincible) የሚለውንም ማጤን ነው! ሁሉ ነገር ተለዋዋጭ ነው፡፡ አሮጌው ያልፋል፤ አዲሱ ይተካል፡፡ ከአሮጌው አዲሱ ልብ ውስጥ የሚቀር ነገር አለ፡፡
የሩሲያን፣ የቻይናንና የኩባን መሪዎች አስመልክቶ ስብሀት ገ/እግዚአብሔር “ሽፍቶችና መሪዎች” በሚለው ጽሑፉ፤ “ባጠቃላይ እንዲያው በጭፍን ያህል ስንናገር፣ በአንድ ልብ፣ በአንድ ወኔ፣ ለአንድ ዓላማ ሲዋጉ የነበሩት ሽፍቶች፣ መሪዎች በሆኑ በማግሥቱ፤ ዓላማቸውም ልባቸውም መለያየት ይጀምራል፡፡ ልዩነቶቻቸው እየበዙ እየከረሩ ሲሄዱ፣ ጠላትነት እየተንፏቀቀ መኻላቸው ይገባል፡፡ በራሺያ ስታሊን ትሮስኪን ያባርረዋል፡፡ ከዚያም ሜክሲኮ ድረስ ልኮ ያስገድለዋል፡፡ ሽፍቶች የነበሩት የትሮትስኪ ወገኖች፣ ሽፍቶች በነበሩት የስታሊን ወገኖች ይጨፈጨፋሉ፡፡ በቻይና ሽፍታ የነበረው ሊዩ-ሻዎ-ቺ ሽፍቶቹ ወደ መሪዎቹ ሲለወጡ የመከላከያ ሚኒስትር ሆኖ ቆየ - ያውም አሪፍ! ማኢና ሊዮ የኋላ ኋላ ተቃቃሩ … አንድ ቀን ሊዮ - ሻዎ - ቺ ከአገር ለመጥፋት በአውሮፕላን ሲበር፣ የሊቀመንበር ማኦ ወገኖች ነቅተውበት ኖሮ ተኩሰው አውሮፕላኑን አጋይተው ይገሉታል፡፡
ወደ ኩባ ስንመጣ ግን ቼ እና ካስትሮ እንደተባበሩ እንደተዋደዱ ተለያዩ፡፡ ትምህርታችንን ከገለጠልን ጋሽ ስብሃት ትልቅ ትምህርት ጥሎልን አልፏል፡፡ ሥልጣን እንዳያለያየንና ዓላማችንን እንዳንረሳ! ያም ሆኖ ለስልጣን ያበቃናቸው ሰዎች፤ ስልጣናቸው ላይ እንዳይተኙ መጠንቀቅ ያባት ነው፡፡ አስረጅ ይሆነን ዘንድ የደጃች ማሩ ወግ እነሆ፡-
“ደጃች ማሩ አሽከሮቻቸውን ሰብስበው አንዱን ፊታውራሪ፣ አንዱን ግራዝማች፣ ወዘተ ብለው ሾሙ አሉ፡፡ ሆኖም ምንም ሥራ የለም፡፡ ስለዚህ አሽከሮች ጋቢ ለብሰው በየጠዋቱ ፀሐይ ይሞቃሉ፡፡
መንገደኛ አይቷቸው፤ “ምን እየሰራችሁ ነው?” ይላቸዋል፡፡
ተሿሚዎቹም፤ “ዝም ብለህ እለፍ! የደጃች ማሩ እሥረኞች ነን!” አሉት፡፡ ከዚህ ይሰውረን!!
ቅርንጫፍ ባበዛን ቁጥር የሚመች ሁኔታ አይኖርም፡፡ ለሰዓቱ ይኮናል? ስንቱን ማርካት ይቻላል?  ተመቸኝ ብሎ የማይፏልሉበት፣ አልተመቸኝም ብሎ እሪዬ - ወዬ የሚሉበት ሁኔታ እንዳይፈጠር ትልቅ ዐይን ያስፈልጋል! በአንፃሩ ዕውነተኛ ተተኪ፣ ዕውነተኛ ወራሽ አለማግኘት መረገም ነው፡፡ “ከሁለት የወለደ አይደሰት፤ ሳይወልድ የሞተ አስተዛዛኝ የለው!” የሚለው ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ሃቅ ነው!!

Read 4960 times