Monday, 31 August 2015 09:18

የሰሜን ኮርያው “ኤር ኮርዮ” የዓለማችን ደካማው አየር መንገድ ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  - ለ4 ተከታታይ አመታት በደካማነት የሚስተካከለው አልተገኘም
                - ላለፉት 20 አመታት አዲስ አውሮፕላን ገዝቶ አያውቅም
                - አብዛኞቹ አውሮፕላኖቹ በ1960ዎቹ የተመረቱ ናቸው
                - ተሳፋሪዎች እቃቸውን በእቅፋቸው ይዘው ይጓዛሉ
    ላለፉት ሶስት አመታት በዓለማችን ከሚገኙ አየር መንገዶች ደካማው ሆኖ የተመረጠው የሰሜን ኮርያው የአየር መንገድ ኩባንያ ኤር ኮርዮ ዘንድሮም የደካማነት ክብረወሰኑን ማስጠበቁን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ተቀማጭነቱ በእንግሊዝ የሆነውና የዓለማችንን አየር መንገዶች በተለያዩ መስፈርቶች በመገምገም በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው ስካይትራክስ የተባለ አለማቀፍ የአቪየሽን አማካሪ ኩባንያ፣ዘንድሮም ደረጃ ከሰጣቸው 600 የተለያዩ አገራት አየር መንገዶች መካከል የሰሜን ኮርያውን ኤር ኮርዮ በመጨረሻ ደረጃ ላይ አስቀምጦታል፡፡
በስድስት አገራት ወደሚገኙ 14 መዳረሻዎች በረራ የሚያደርገው ኤር ኮርዮ፣ ከዚህ በፊትም አብዛኞቹ አውሮፕላኖቹ በ1960ዎቹ የተመረቱና ያረጁ ናቸው በሚል መቀጣቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ አየር መንገዱ ላለፉት 20 አመታት አዲስ አውሮፕላን ገዝቶ እንደማያውቅ ገልጧል፡፡
አብራሪዎቹ ዲጂታል ድጋፍ ሳያገኙ ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ እንደሚያበሩ፣ ተሳፋሪዎች እቃቸውን በእቅፋቸው ይዘው እንደሚጓዙ፣ ለመዝናኛ ተብለው የሚከፈቱ ሙዚቃዎችና ቪዲዮዎችም የአገሪቱን መሪ የሚያንቆለጳጵሱ ብቻ እንደሆኑ ኩባንያው ገምግሟል፡፡
ስካይትራክስ አየር መንገዶችን በአውሮፕላኖች ብቃት፣ በደንበኞች አገልግሎት ጥራትና በሌሎች የአቪየሽን መስክ ጥራት መመዘኛ መስፈርቶች እየለካ በየአመቱ ደረጃ እንደሚሰጥ ይታወቃል፡፡

Read 1285 times