Monday, 31 August 2015 09:11

የዓለማየሁ ገላጋይ ትንቢታዊ ድምጾች

Written by 
Rate this item
(7 votes)

የመጽሐፍ ቅኝት - በአብነት ስሜ)

ካለፈው የቀጠለ
ተራኪው እና ደራሲው
የልቦለዱ ተራኪ እኔ ሞኝ ነኝ፤ እኔ ፈሪ ነኝ ይላል። ነገር ግን፣ ሞኝነቱ ውስጡ አስተዋይነትን፣ ፍርሀቱ ውስጥ ደግሞ ድፍረትን ማየት ይቻላል። ተራኪው ከክርስቶስ ይልቅ ለደቀመዝሙሩ ለጴጥሮስ ይቀርባል። ጴጥሮስ እንደ ህፃን የዋህ፣ ጉጉ፣ ችኩል፣ ፈጣንና ፍርሀት አልባ ነው። ብዙ ይጠይቃል። ይጋፈጣል። ለክርስቶስ በጣም ቅርቡ ነበር። ውሀ ላይ እንደ ክርስቶስ መራመድ ከጀመረ በኋላ መሀል ላይ ራሱን ይጠረጥራል። እናም ይፈራል። መስጠም ሲጀምር ወደ ክርስቶስ ይጮሀል።  ከመስጠምም ይድናል። ጌታውን ሊይዙ ከመጡት ውስጥ ያንዱን ጆሮ በሰይፍ ቀንጥሷል። በዚህም ግን ተገስፆአል። ክርስቶስ በተያዘ ጊዜ ከደቀመዛሙርቱ ውስጥ ለረዥም ጊዜ በድፍረት የተከተለው ጴጥሮስ ነው። በተጠየቀ ጊዜ ግን ስለፈራ፣ “ይህንን ሰው አላውቀውም” ብሎ ሦስቴ ካደ። ድፍረቱ ሳይታይለት በክህደቱ ብዙ ተወቀሰ፤ ተገሠፀ፤ ተሣቀቀ።  ሌሎች ኢየሱስን ጥለውት የሔዱ ደቀመዛሙርት ግን እንደ እርሱ አልተወገዙም። ሐዋርያው ጴጥሮስ የዋህ ቢመስልም ብልህ ነበር፤ ጀግና ቢመስልም ፈሪ ነበር።
የወሪሳ ልቦለድ ተራኪም ለኢየሱስ ሳይሆን ለጴጥሮስ ነው የሚቀርበው።  በተራኪው ውስጥ የምናየው ደራሲውም የተላበሰው ሰብእና ኢየሱሳዊ ሳይሆን ጴጥሮሳዊ ነው።  የዋህና ፍርሀት አልባ ሕፃን ባይሆን ኖሮ እንዲህ ዓይነቱን ህልም አይጽፍልንም ነበር። ይህንን ዘግናኝ ነውራችንን የህፃን የዋህነት የሌለው ደራሲ ካልሆነ ማንም አይነግረንም።
ክርስቺያን አንደርሰን የተባለው ኖርዌጂያዊ እንደዚህ እንደ ዓለማየሁ ገላጋይ ጴጥሮሳዊ ህፃንነትና የዋህነትን የተላበሰ ደራሲ ነበር። “የንጉሱ ልብስ” በተሰኘ ልቦለዱ እንደራሱ ያለ አንድ ህፃን ፈጥሮልን አልፏል። ታሪኩን አብረን እናስታውስ። ንጉሡ ማጌጥ ይወድዳል። ለየት ያሉ አልባሳትን ያደንቃል። ይህን የተረዱ ሁለት አታላዮች ከንጉሡ ዘንድ ይቀርቡና ልዩ የሆነ ትንግርታዊ መጎናፀፊያ ለንጉሡ ለማዘጋጀት እንደአቀዱ ይናገራሉ። ልብሱን ለየት የሚያደርገው በክፉና በተንኮለኛ ሰው ዓይን አለመታየቱ ነው።  አንዱ  የንጉሡ ሚኒስትር ልብሱ ከሚደወርበት ሔዶ እንዲያይ ተላከ። ባዶ የሽመና ዕቃ ብቻ አየ። ልብስ የሚባል የለም። “አይ ክፉና ተንኮለኛ ከምባልስ” በሚል መንፈስ ያላየውን እንደ አየ አድርጎ ተናገረ። ሌሎች ሹማምንትም  እንዲሁ አደረጉ። ልብሱ ተጠናቀቀ ተባለና ወደ ንጉሡ ተወሠደ። ንጉሡም በግብዝነት ያላየውን እንደ አየ፣ የሌለውን እንደ አለ አድርጎ “ልብሱን ለበሰና” በሰልፍ ወጥቶ ወደሚጠብቀው ህዝብ በሰረገላ ሆኖ መታየት ጀመረ። ተመልካቹ ሁሉ “ክፉና ተንኮለኛ” ላለመባል  ሲል “ግሩም ድንቅ” እያለ የንጉሡን አዲስ መጎናጸፊያ አደነቀ። ንጉሡ ግን ራቁቱን ነበር። ታዲያ ከሰልፈኛው ህዝብ መካከል አንድ ህፃን ልጅ እንዲህ አለ፤ “እናንተ ንጉሡ ራቁቱን ነው።” ከዚህ ቃል በኋላ የታወረው ህዝብ አየ። ንጉሡም ከቀን እንቅልፉ ነቃ።
ሐዋርያው ጴጥሮስ በአንደርሰን ተረት ውስጥ እንዳለው ህፃን ነው። የአንደርሰን የራሱም ተፈጥሮ በተረት እንደተፈጠረው ህፃን ነው። ህፃኑ ራሱ አንደርሰን ነው። ዓለማየሁ ገላጋይም ጴጥሮሳዊ ነው። ነገረሥራው ሁሉ እንደ ደራሲው አንደርሰን ነው። የወሪሳ ተራኪና የአንደርሰን ተረት ውስጥ ያለው ህፃንም አንድ ናቸው። ገበናችንን ይገልጡታል፤ጉዳችንን ያሣዩናል።
ወሪሳዊ ተውሳክ
ወሪሳ ስርቆትና ዝርፊያ የነገሡበት የጉድ ሠፈር ነው። በዚያ ሰፈር “ቢዝነስ” መስራት ማለት መስረቅ፣ ማጭበርበር፣ መዝረፍና መግደል ነው።  ይኸ በሀገር ደረጃ የተዋቡና የሚያደናግሩ ቃላት እየተጠቀምን “ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት” የምንለው ነገር በወሪሳ ሰፈር ውስጥ ራቁቱን የሚመላለስ ጀግና ነው። በወሪሳ ውስጥ ሰርቶ የሚበላው ሞኙ ተራኪ ብቻ ነው። በዚያ ምድር ሰርቶ የሚበላ “ፋራ” ነው። የሚበላው፣ የሚሰረቀው ግን ማን ነው? የሚበላው ወደ ሥራ የሚሠማራው ሞኝ ወይም ፋራ ነው።  ስለዚህ ወሪሳ ፓራሳይት ወይም ተውሳክ ነው። ተውሳክ በሽታ ነው። የራሱን ምግብ አያመርትም። በተክል ወይም በሰው ላይ ሰፍሮ ሰለባውን እስኪሞት ድረስ ይበላዋል። ሌባ፣ ዘራፊ፣ ጉቦኛ፣ ሙሰኛ፣ ወይም ኪራይ ሰብሳቢ የህብረተሰብ ተውሳክ ነው።
በሀገር ደረጃ ሲታይ ኢትዮጵያም ትልቋ ወሪሳ ነች። ሳንሰራ የምንበላ ሌቦችና ለማኞች እየሞላናት ነው። ሰርቶ የሚበላው ሁሉ እንደ ወሪሳው ተራኪ ፋራ ነው። በዚሁ ከቀጠልን የሚቀሩን ፋራዎች ቁጥር እየተመናመነ ይሔድና ምንም ይሆናል። ያኔ እንግዲህ በአሪፍ የሚበላው ፋራ ይጠፋል። ከዚያ ትልቁ አሪፍ ትንሹን አሪፍ መብላት ይጀምራል። የወሪሳ ነዋሪዎች ሁሉም “ብልጥ” ናቸው። ስለዚህ አይሠሩም። ይሠርቃሉ። የኢትዮጵያ ሰዎችም እንደ ወሪሳ ሰፈር ሰዎች ብልጠታቸው እየጨመረ “ፋራነት” የተባለውን ሠርቶ መብላትን እያስወገዱ ነው።
በ1980ዎቹ አጋማሽ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ የሰማሁት አንድ ነገር ሁሌም ከአእምሮዬ አይጠፋም። ሴትየዋ በስድስት ኪሎ ካምፓስ አቅራቢያ ጠላ ቤት አላቸው አሉ። ልማደኛ ተማሪዎች እዚያ ያመሻሉ። ኮማሪትዋ የልጆቹን የትምህርት መስክ እየደጋገሙ በመጠየቅ ብዙ አውቀዋል። ታዲያ አንድ ቀን፣ “እኔ ምለው” አሉ። “እኔ ምለው፣ አንዳችሁም እንኳ ጉምሩክ የሚባል ትምህርት አትማሩም?”
የትምህርት ባህላችንም ከሞላ ጎደል ይኸው ነው። ድሮም ሆነ አሁን ያው ነው። ከጥቂት “ፋራዎች” በስተቀር የትምህርት ሥርዓቱ ያፈራልን የወሪሳ መዓት ነው። እንደ አማርኛ አስተማሪው ተራኪ ፋራ የሚሆኑ ጥቂት ናቸው። ሌላው “ግራጁዌት” ሁሉ ወሪሳዊ ነው። አሁን ደግሞ ሁሉም “ነቄ” ሆኗል። ሠርቶ የሚበላ ፋራ እንደ ዳይኖሰር ጠፍቶ ሊያበቃ የቀረው አንድ ሐሙስ ነው። ዛሬ ረቡዕ ነው። ነገ ማለዳ ላይ “አሪፍ” ነን ያሉ ሁሉ “ፋራ” እንደሆኑ ይረዱታል። አጉል አሪፍነታችንን በቶሎ ካላቆምን መጨረሻችን አያምርም። ተረቱ የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል ይላል። ፉክክር የብልጥ ነው፤ብልጠት እናበዛለን።
ገዢዎቻችን
በሀገራችን አንድ የሚገርመኝ ነገር አለ። ሁሉም ፖለቲከኛ ነው። ሁሉም ለፍላፊ ነው።  ሁሉም ሥልጣን ይፈልጋል። ሁሉም መግዛት ይፈልጋል። ሰርቶ የሚበላ ገበሬ ብቻ ነው። ሌላው ገበሬ የሚያመርተውን ይበላል። ከዚያም አልፎ የገበሬው የበላይ ይሆናል።
ስንትና ስንት ህዝብ እያለበት አገር የንጉሥ ነች ይባላል። ንጉሥ ዘራፊ ነው። ዘራፍ ማለት ዘራፊ ከሚለው ቃል የወጣ ነው። ዘራፊ ጀግና ነው። የሚሰርቅና የሚዘርፍ ጀግና ነው ይባላል። ንጉሡ ዘራፊ ነው። ሀገር ሙሉ የኔ ነው ብሏል። የንጉሡ አንጋሾች ዘራፊዎች ናቸው። ሳይሠሩ ነው የሚበሉት። የንጉሡ ወታደሮችም ዘራፊዎች ናቸው። ሳይሠሩ ነው የሚበሉት።
መንግስቱ ለማ የአባታቸውን ትውስታዎች “ትዝታ ዘ አለቃ ለማ” በሚል መጽሐፍ አሳትመውታል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ አስደማሚ ትረካዎች አሉ። አለቃ ለማ አባታቸውን ወደ ትምህርት ላከኝ ብለው የሙጥኝ ይላሉ። ይኸ የዛሬ 150 ዓመት ገደማ ነው። ለማ ካልተማሩና ካህን ካልሆኑ አራሽ ገበሬ ሊሆኑ ነው። በወቅቱ፣ ገበሬ በወታደር ይዋረዳል። ንብረቱን ይቀማል። ሚስቱን ይነጠቃል። በዚያ ሳቢያ እርሻውን እየተወ “የጌታ የሚያድር” ይበዛ ነበር። እንግዲህ አገሩ ሁሉ ገበሬ ነው። የሚያመርት እሱ ነው። እሱ ግን ይዘረፋል፤ ይዋረዳል። ከዚህ ውርደት የሚተርፍ ፍጡር ቢኖር ካህን ብቻ ነው።  ስለዚህ አለቃ ለማ፣ አልቅሰውና ጮኸው ወደ ዘመኑ ትምህርት ተላኩ።
ካህንና ወታደር የገዥዎች እጅ ናቸው። ካህን ህዝቡን በመስበክ መንፈሱን ያኮላሸዋል። ወታደር ደግሞ ህዝቡን በጦር እየወጋ አካሉን ያደቅቀዋል። በመንፈስና  በአካል የተኮላሸ ህዝብ ብቻ ነው ሊገዛ የሚችል። በወቅቱ ይገዝዛ የነበረው ገበሬው ነው። ከባህላዊው ወደ ዘመናዊው ትምህርት ስንሸጋገርም የሰው ዓላማ ተምሮ ለመሥራት አልነበረም። ይህ መንፈስ አሁንም አለ። የተማረ ሁሉ ስሙ ይለያይ እንጂ ያው ካህንና ወታደር ነው የሚሆነው። የገዥ እጅ ነው። ገዥው የውጭም የሀገር ውስጥም ሊሆን ይችላል። ቁጭ ብዬ ልብላ ብሎ የሚማር ሁሉ ጤነኛ አይደለም። ተውሳክ ነው። ትምህርትን እንደ ጽድቅ ነው የምናየው።  ከጭለማ ወደ ብርሃን የምንወጣበት መንገድ ነው እየተባለ ብዙ ተሰብኳል። እውነታው ግን እሱ አይደለም። ትምህርት የሰለጠኑ ባሮች የማፍሪያ መሣሪያ የሆነበት ጊዜ ብዙ ነው። ትምህርት የዕድገት መሠረት ነው እያልን ስንዘምር አንድ መቶ ዓመት ደፍነናል። እውነታው ግን እድገት የትምህርት መሠረት መሆኑ ነው። አድጎ የተማረ እንጂ ተምሮ የበለፀገ ሀገር የለም።
እነዚህ ሁሉ ውዥንብሮች ወሪሳዎችን እያበዙና “ፋራዎችን” እየቀነሱ ነው። ወደ እውነታው ብንመለስ ይሻላል። እንደ ግብዙ ንጉሥ የዘመኑ ሥልጣኔ ያስገኘውን ድንቅ መጎናጸፊያ ለብሰናል ብለን ራሳችንን ባናታልል ይበጀናል። በብዙ ቦታ እርቃናችንን ነን። ብልጠት አብዝተን የወሪሳ አገር እየሆንን ነው።
ሺ-ትርገጥ እና ጭፍን
ሺ-ትርገጥ የአምበርብር ልጅ ነች። አባትና ልጅ በቀመሩት ታላቅ ሤራ ሺ-ትርገጥ የተራኪው ህጋዊ ሚስት ትሆናለች። ባህሪዋ ጥልቅና ድብልቅልቅ ነው። በአካላዊ መጠን አባትዋ ደቃቃ ነው። እሷ ግን በእናትዋ ወጥታ ግዙፍ ወይም መንዲስ ነች። ግዙፍነትዋ ልዩ ነው። ለእኔ ከጉማሬ እናትና ከዳይኖሰር አባት የተወለደች ሆና ትታየኛለች። ተራኪው በአነስተኛ የሥጋ ተራራ ይመስላታል። አንዳንዴም ከደብረ ዳሞ ተራራ ጋር ያመሳስላታል። ተራኪው በገመድ እየተጎተተ ይወጣል። የገመዱ ጎታች የአማቱ፣ የሺ-ትርገጥ አባት አምበርብር ነው። ይህ ገለፃ የተራኪው ነፍስ በማን እጅ እንደሆነች ይነግረናል።
እዚህ ላይ ፃድቁን ያመላልስ ነበር የተባለው ዘንዶም በማን እንደሚመሰል መገመት ይቻላል። ሺ-ትርገጥ ተራኪውን የምታጠምደው በአልጫና በቀይ የበግ ወጥ ነው። ተራኪው በሆዱ ተጠምዷል። ደሞዙ ከወር ወር አይደርስም። ይርበዋል። በተለይ አንድ ቀን አሜሪካ በ77ቱ ረሀብ ለኢትዮጵያ እንደደረሰችላት ዓይነት ነው ሺ-ትርገጥ አገልግል ተሸክማ በረሀብ ዝሎ በ7 ሰዓት ላይ ከቤቱ አልጋ ላይ ለተንጋለለው ተራኪ የምትደርስለት። ሺ-ትርገጥ ተራኪውን ጭፍን ከተባለች ወዳጁ፣ አሜሪካ ደግሞ ኢትዮጵያን ከሶቪየት ኅብረት ወይም ከሶሻሊስቱ ጎራ ትነጥላታለች።
ሺ-ትርገጥ ተራኪውን ከማግባትዋ በፊት አንድ አገር ልጆች ወልዳለች። በቁጥር ግን አራት ናቸው። ቤት ሞልተው ይንጫጫሉ። የቤቱ ግድግዳ “ፖሊስና እርምጃው” በተሰኘ ጋዜጣ ከዳር እስከ ዳር ለብሷል። ልጆቹ በአያታቸው እየተመሩ እነዚህን ጋዜጦች ያነባሉ። ተራኪው ባልወለዳቸው ልጆች ይከበባል። በህልም አፈታት እነዚህ ልጆች ማን ናቸው?
የተራኪው የፀሐይ ኮከብ ሐመል እሳት ወይም ኤሪስ ነው። ኮከቡ ከኢትዮጵያ የምድር ኮከብ ጋር ይገጥማል። እሱ የኢትዮጵያ ጭንብላዊ ተምሳሌት ነው። ባልወለዳቸው ልጆች የአሳዳጊነት እዳ ገብቷል። የርሱ ገቢ ለነዚህ ሁሉ ልጆች ማሳደጊያ አልበቃም ማለት ይጀምራል። ልጆቹ የዐባይ ወንዝ ጥገኛ የሆኑት ሀገሮች ህዝቦች ናቸው። ግዙፍዋ ሺ-ትርገጥ የአሜሪካ ተምሳሌት ነች። ከዚህ በላይ ለብልህ አይነግሩም፤ ለአንበሳ አይመትሩም ነው ተረቱ። አሁን ደቃቃው የተራኪው አማት፣ የሺ-ትርገጥ አባት የየቷ ሀገር ተምሳሌት እንደሆኑ መገመት የማይችል አንባቢ አይኖርም።
ከሺ-ትርገጥ በተጓዳኝ ሌላ ገፀባህሪ አለች። ጭፍን በመባል ትታወቃለች። ለልቦለዱ ተራኪ ብዙ ተረት ትነግረዋለች። በጭፍን አንደበት የአማርኛ ተረትና ምሳሌዎች ኩላሊታቸው ፈርጦ ጨጓራቸው ይዘረገፋል። ፍቅር እስከ መቃብር የተባለው ልቦለድ በጭፍን “ቨርዥን” ሲተረክ ከፍ ያለ የእሳት እቶን ወይም “ካምፋየር” ውስጥ የገባ ጀሪካን ይሆናል። ሀዲስ ዓለማየሁ ሊብራ ናቸው።
ተራኪው ከጭፍን ጋር አፍላጦናዊ ወደ አልሆነ “ሮማንቲክ” ፍቅር ውስጥ ይገባል። ልቡ አብዝቶ ወደርሷ ይሳባል። ከጭፍን ጋር ያለው ፍቅር በሺ-ትርገጥ የጋብቻ ሤራ ይጨናገፋል። ተራኪው ውሎና አዳሩን የአማቹ ሰፈር ከሆነው ከእሪበከንቱ ሲያደርግ ከአክስቱ የወረሰው የወሪሳ ቤት ወና ይሆናል። ኋላ ላይ ቤቱ በጭፍን እየተጎበኘ እንደሆነ እናውቃለን። ጭፍን የምሥራቁ ዓለም ሀገራት ተምሳሌት ነች። ከቻይና፣ ከጃፓን፣ ከህንድ፣ እና ከኮሪያ አንዱን መምረጥ ይቻላል። የቻይና ኮከብ ሊብራ ነው።
በወናው ቤት ውስጥ ተዳብሎ መኖር የሚጀምር ሌላም አስር ዓመት ያልሞላው የእሪበከንቱ ልጅ አለ። ይህ ልጅ ድመት በሸምቀቆ አድርጎ በሰንደቅ መስቀያ ሲሰቅል የኢትዮጵያን የህዝብ መዝሙር ይዘምራል። ይህ ልጅ ማንን ይወክላል? ማለፊያ የሆነ ህልም ፈቺ ያስብበት። የወና ቤቱ፣ የጭፍንና የሰይጣን ግልገል የሆነው ልጅ ህልማዊ ትንታኔ ብዙ ትንቢታዊ ድምፆች አሉበት። የድመት ገዳዩ ልጅ ዓላማ አንበርብርን ለመግደል ነው። ይኸ ነገር በአጠቃላይ የፀረአይሁድን በተለይ ግን የኢራንና የእስራኤልን ባላንጣዊ ጠላትነት ይወክላል። ልጁ በተለይ የሚወክለው ኦሳማ ቢን ላደንን ነው። እርሱ የሺትርገጥን ልጅ ለመግደል ሙከራ አድርጎ ሸሽቷል፤ በመጨረሻም በወሪሳ ሰፈር በተራኪው ቤት ተሸሽጓል።
የስምንት ዓመቱ የመጣባቸው ልጅ የሺ-ትርገጥን የመጨረሻ ልጅ በገመድ ሸምቅቆ ለመግደል ሙከራ አደረገ። ከዚያ በኋላ ከእሪበከንቱ የወንዝ ጉራንጉር ውስጥ ሸፈተ። በመቀጠል ወሪሳ ከሚገኘው ከተራኪው ቤት ውስጥ ተሸሸገ። አንበርብር እያሳደዱት ነው። የአሜሪካን የ “ናይን ኢለቨን” (9/11) ሽብር ያደራጀ ነው የሚባለው ኦሳማ ቢን ላደን በመጨረሻ ተሸሽጐ የተገኘው የአሜሪካ ተባባሪ ከተባለች አገር ጉያ ውስጥ ነው።
ሺ-ትርገጥ ከተራኪው አርግዣለሁ የምትለው ልጅ የመጣባቸውን የመሰለ ሆኖ እንዲወለድ ትመኛለች። ከዚያም ያለፈ ጥረት ታደርጋለች። ሐሳቧ የመጣባቸውን ልጅ ከበራፍ ተቀምጣ እሱ ሲያልፍና ሲያገድም ማየት ነው። እርጉዝ ሴት ደጋግማ ያየችውን ሰው የመሰለ ትወልዳለች ከሚል እምነት ተነስታ ይመስላል። የሷ ታሪክ ከምን እንደደረሰ ሳናውቅ ነው የ“ወሪሳ” ትረካ የሚያበቃው።
አሜሪካ የኦሳማ ቢን ላደን ነገር ሲያንገበግባት ቆየ። በርሱ ዳፋ ኢራቅ ተደበደበች። ወረራው ወደሌላም አገር ተዛመተ። ይህ እንግዲህ በጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ዘመን ነው። አሜሪካ በቀጣይ ያገኘችው መሪ ባራክ ሁሴን ኦባማ ሆነ። ይህ ሰው ቢያንስ በስሙ ከኦሳማ ቢን ላደን ጋር አንዳች መመሳሰል  አለው። አሜሪካ እንደ ሺ-ትርገጥ የልጇን ገዳይ የመሰለ መውለድ ተመኝታ ነበርን የሚያስብል ግርምታ ይጭራል።
ኮከብን በተመለከተ ጥቂት ቃላትን እንጨምር። የሺ-ትርገጥ ኮከብ ካንሰር ወይም ሸርጣን ውሀ ነው። የጭፍን ኮከብ ሊብራ ነው። ከውጭ ስትታይ ወንዳወንድ የምትመስል ነች። በቅርበት ግን ሞንሟና የሆነች ሴት ነች። ደራሲው ዓለማየሁ ገላጋይ፣ የልቦለዱ ተራኪ ገፀባህሪ፣ ክርስቺያን አንደርሰን፣ በአንደርሰን ተረት ውስጥ ያለው ህፃንና ችኩል የሆነው ሐዋርያው ጴጥሮስ ሁሉም ኤሪስ ናቸው።
አምበርብር የቶረስ፣ የስኮርፒዮ፣ የካፕሪኮርንና የአኳሪየስ ኮከቦች በጎጂ መልኩ ተሰባጥረው የሚታዩባቸው ገፀባህሪ ናቸው። ከዚህ ውስጥ የጨረቃ ኮከባቸው ካፕሪኮርን ነው። ይኸ ኮከብ የአይሁድ ወላጆች ኮከብ ነው ይባላል፤ በጨረቃና  በወላጅነት ውስጥ።
የግዙፎቹ የሺ-ትርገጥ ኮከብና የአሜሪካ ኮከብ ካንሰር ነው። የአሜሪካ ሙሉ ኮከብ ስብጥሩ በጥሩ ሁኔታ የተቀመረና የታሰበበት ቢሆንም አንድ ወሳኝ ጉድለት አለበት። አሜሪካ ውስጥ ያሉ እስቴቶች ኮከብም ይታወቃል። የትኞቹም ግዛቶች ግን የኤሪስ ኮከብ የላቸውም። በዚህ ሳቢያ አሜሪካ በጦርነቱ ዘርፍ የኤሪስን ጀግንነት አልታደለችም። በየወቅቱ በገጠመቻቸው ጦርነቶች እንደ ኤሪሶቹ እንግሊዞችና  ጀርመኖች የሚያኮራ ጀግንነት አሳይታ አታውቅም። ሀገሪቱ ውስጥ ኤሪስ ግዛቶች ስለሌሉ አሜሪካ የኤሪስ ኮከብ ላላቸው ሰዎች ብዙም አትመችም ይባላል። ይህ ግን ትንሽ የተጋነነ ነው። ለብዙ ኤሪሶች ገነት የሆነችባቸው ጊዜያቶች ብዙ ናቸው። እንዲያም ሆኖ ግን ለኤሪስ ግለሰቦች አስጨናቂ የምትሆንበት ጊዜ አለ። ከውሀ ኮከብዋ ጋር ያለው ሰፊ እንክብካቤዋ እሳቶቹን ኤሪሶች ቀዝቀዝ ያደርጋቸዋል። ችግሩ ከዚህ ብቻ የሚመነጭ ነው።
ካንሰርዋ ሺ-ትርገጥ በራስዋ ጥሩ እናትና ወላጅ ነች። ኤሪሱ ተራኪ ግን ይፈራታል። አፍና የምትገድለው ይመስለዋል። እሳት ውሀን የሚፈራውን ያህል ሲያያት ይርበደበዳል፤ ፍርሀቱ ውስጥ ግን ማሾፍም አለበት። የኤሪሱ ተራኪ ኮከብ የገጠመው ከሊብራዋ ጭፍን ጋር ነው። ኤሪስና ሊብራ ዋልታዊ ኮከቦች ናቸው። በተለይ በተቃራኒ ፆታዎች መካከል ሲሆን ሁለቱ ኮከቦች አብዝተው ይሳሳባሉ። ነገሩ ሁለት ማግኔቶች በተቃራኒ ጎናቸው ሲጠጋጉ እንደሚሳሳቡትና እንደሚሳሳሙት ዓይነት ነው። ሊብራዋ ጭፍን የኤሪሱ ተራኪ ተቆርቋሪ ነች። ከአደጋ ልትከላከለውም ትተጋለች። አልሆንለት ይላል እንጂ እርሱም ከእቅፏ ባይወጣ ይመርጥ ነበር።
የወሪሳ ሰፈር የአኳሪየሳዊት ኢትዮጵያ ተምሳሌት ነች። ሊነጋ ሲል በጣም ይጨላልማል እንደሚባለው ክፉ ዛር ለቋት ሊሔድ ሲቃረብ የእብደቷ መጠን ከፍተኛውን ደረጃ ይደርሳል።  የዚህ ውክልናም ወሪሳ ነች። ወሪሳ ወደ ሞት እንጂ ወደ ህይወት የምትሄድ አትመስልም። ነገር ግን የተስፋ ጭላንጭል አለ። ፀሐይ ትወጣለች። የኢትዮጵያ ኮከብም በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ይወጣል። ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያ ደጅ እያደረች ኮከብ አትቆጥርም። የእንጀራ እናትዋንም በወላጅ እናትዋ ትተካለች። ወሪሳንም እሪበከንቱንም አትሆንም። ምሥራቅም ምዕራብም አትልም፤ ራስዋን ትችላለች፤ ራስዋን ትሆናለች።
በወሪሳ አስራሁለቱም ኮከቦች መጥፎና ደካማ ጎናቸውን አፍርጠውና ገልጠው የዛር ድቤአቸውን ይደልቁባታል። የወሪሳ መንደር ሰዎች በኤሪሳዊ ድፍረትና ጭካኔ ይተራረዳሉ፤በቶረሳዊ ስግብግብነት ይቀማማሉ፤ በጄሚናዊ መንታ ምላስ ታሪካቸውን ይከታትፋሉ፤ በካንሰራዊ ጥፍር ይነጣጠቃሉ፤ በሊዮአዊ ማን አለብኝነት ያጓራሉ፤ በቪርጎአዊ ንዝንዝ ይጠቃጠቃሉ፤ በሊብራዊ ስንፍና ቀን ከሌት ያንኳርፋሉ፤ በስኮርፒአዊ በቀል በውድቅት ሌሊት ይገዳደላሉ፤ በሳጁታሪየሳዊ ልቅ አንደበት ይዘራጠጣሉ፤ በካፕሪኮርናዊ ቅዝቃዜ ይጠላለፋሉ፤ በአኳሪየሳዊ የቀውስ ዛር ልብሳቸውን ጥለው ያብዳሉ፤ በፓይሰሳዊ ቅዥት ውዥንብር ይፈጥራሉ። ሁሉም አብደዋል። የበረከትን ዝናብ ይናፍቃሉ። ሁሉም ታውረዋል። የበረከትን ጮራ ይሻሉ። ሁሉም እየጓጎሩ ነው። ከቅዠታቸውና ከአስፈሪ ህልማቸው ካልባነኑ አይድኑም።
አንድ ሀገር ልጅ ያላትን ሺ-ትርገጥን ያገባው ተራኪ የእንጀራ ልጆቹ ቀላቢ ይሆናል። ኋላ ላይ ሙሉ ደሞዙን ለሚስቱ ያስረክባል። ለራሱ የአውቶብስ መሳፈሪያ የሚሆነው አንድ ብር እንኳን ይከለከላል። ይኸ የዐባይ ወንዝ ተምሳሌት ነው።
ኢትዮጵያ የራሷንም ድርሻ እንኳን ስትከለከል ቆይታለች። የሺ-ትርገጥ ልጆች ከዐባይ ተፋሰስ አገሮች ውስጥ በተለይ የግብፅ አገር ህዝቦች ተምሳሌቶች ናቸው። አሁን ጥያቄው የአማርኛ አስተማሪ ነኝ የሚለው ተራኪ ሙሉ ደሞዙን እየተቀማ ለራሱ አንድ ብር እንኳን እየተከለከለ እስከመች ይቆያል ነው? ተራኪው በምግብም እየተበደለ ይራባል። አንድ ሁለቴ ጭፍን ሰርቃ ካገኘችው ስትጋብዘው እናያለን። ተራኪው ለነፃነቱ እየቃተተ ነው። ኢትዮጵያ የዐባይን፣ ተራኪው ደግሞ የደሞዙን ነፃነት ይሻሉ። ልቦለዱ በብዙ ዓለማቀፋዊ ትእምርቶች የተሞላ ነው፤ከላይ የዘረዘርኩት ጥቂቱን ብቻ ለቅምሻ ነው።  
ማጠቃለያ
የዓለማየሁ ገላጋይ ወሪሳ ለየት ያለ ድርሰት ነው። የልቦለዱ ፋይዳ ከመዝናኛ ግብአትነት አለፍ ይላል። ልቦለዱ ህልም ነው። ህልሙ ውስጥ ህመም አለበት። ህመሙ የኅብረተሰብ ህመም ነው። ህልሙ መፈታት፣ ህመሙ ደግሞ መዳን አለበት።
“ሀገሬ ኢትዮጵያ ሆይ! እስኪ ህልምሽን ንገሪን” ለምንል ዜጎችዋ፣ ጦቢያ ልክ የዛሬ 50 ዓመት ህልሟን በፍቅር እስከ መቃብር ነግራናለች፤ ዛሬ ደግሞ በወሪሳ። ያኔ በሊብራው ሐዲስ ዓለማየሁ፤ ዛሬ በኤሪሱ ዓለማየሁ ገላጋይ። ህልሟን መናገር የርሷ፣ ህልሟን መፍታት ደግሞ የኛ ድርሻ ነው። ያለፈውን ፈለግና መንገዳችንን ብቻ ሳይሆን የመፃኢውን ዒላማና ዓላማችንን ጭምር በሀገራችን ህልም ውስጥ እናነበዋለን፡፡  
ልቦለድን እንደ ህልም ስንፈታ የምናቀርበው ትርጓሜ ፈርጀ ብዙ ነው መሆን ያለበት። አንዱ ትእምርታዊ ገፀባህሪ ወይም የትረካ አንጓ ከአንድ በላይ ትርጓሜዎች ይኖሩታል። የዚህ ዓይነቱን የሥነኂስ ስልት በቅጡ ለመረዳት ብዙም ርቀን መሔድ አያስፈልገንም። እዚሁ ሀገራችን ለዘመናት የሰፈነ የአንድምታ ትርጓሜ የሚባል ባህልና ጥበብ አለን።
ይህን ሒሳዊ ብእሮግ ከአንድምታ ትርጓሜ ጠቅሼ ልቋጭ። በመጽሐፍ ቅዱስ በዘፀአት መጽሐፍ በምእራፍ ሁለት፣ በቁጥር አምስት ላይ እንዲህ የሚል ዓረፍተ ነገር አለ። “ወወረደት ወለተ ፈርዖን ከመ ትትሐፀብ በውስተ ተከዚ” [የፈርዖን ልጅ ገላዋን ትታጠብ ዘንድ ወደ ዐባይ ወንዝ ወረደች።] የሀገራችን ሊቃውንት ለዚህ ዐረፍተ ነገር ያስቀመጡት የአንድምታ ትርጓሜ ቀጥሎ ያለውን ይመስላል።
ተርሙት የምትባል የፈርዖን ልጅ ልትታጠብ ወደ ፈሳሹ ወረደች፤ ስለ ምን ቢሉ በፈሳሹ ዳር እንደ መዋት ያለ ነበር፤ ኮብሽ የሚባል ደዌ ነበረባትና ለመጠመቅ፤ አንድም ነጋዴ ወዳጅ ነበራትና ያንን ለመቀበል፤ አንድም አዞ ጉማሬ ታመልክ ነበረችና ስለዚህ፤አንድም በጎርጎራ ሳለ ያጤ መለክ ሰገድ ልጆች ውሀ ዋና ይማሩ እንደነበረ ውሀ ዋና ልትማር ነው።
የፈርዖኑ ልጅ የተርሙት ወደ ዐባይ ወንዝ መውረድ አራት አንድምታዊ ትርጓሜዎች ተሰጥተውታል፤ አንድም ለህክምና ጠበል፤ አንድም ለድብቅ ፍቅር፤ አንድም ለጉማሬ አምልኮ፤ አንድም ለውሀ ዋና ትምህርት በሚል። አንድምታዊ ትርጓሜ ጥልቅ ንባብ ነው። እንደ ቁጥር ስሌት ሁለት ሲደመር ሦስት አምስት ነው ብሎ አያቆምም፤ ከዚያ ብዙ ያልፋል።
 ይህን ድንቅ የሆነ የጥልቅ ንባብ ባህላችንን ወደ ልቦለዶቻችንም ልናመጣው ይገባናል ብዬ አስባለሁ። የወሪሳ ትንታኔ ብዙ የሚሔድ ነው፤ ላሁኑ ግን በዚሁ ይብቃኝ።
 [ድኅረ-ማስታወሻ፤ ፍካሬ ኢትዮጵያ በተባለው መጽሐፌ ውስጥ የፍቅር እስከ መቃብር የአንድምታ ትርጓሜ ይገኛል። የፈጠራ ድርሰትን እንደ ህልም የማየትን የሒስ ስልት፣ ሚካኤል ሺፈራው በምስጢረኛው ባለቅኔ መጽሐፉ ተግብሮታል። ስለእርሱ የሒስ ስልት በሌላ ጽሑፍ ለማቅረብ እቅዱ አለኝ።]

Read 7202 times