Monday, 31 August 2015 09:01

በአልኮል አመጣሹ የጉበት ስብ በሽታ የተጠቁ ሰዎች 5 ዓመት በህይወት የመቆየት እድላቸው 50 በመቶ ብቻ ነው

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ቴትራሳይክሊን፣ የደም ብዛትና የካንሰር ህመም መድሃኒቶች የጉበት ስብ በሽታን ሊያስከትሉ ይችላሉ

  ጉበት መርዛማ ንጥረ ነገሮች በደም አማካኝነት ወደተለያዩ የሰውነታችን ክፍሎች ውስጥ ዘልቀው ገብተው ጤናችን አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ብርቱ ተጋድሎ የሚያደርግ የሰውነታችን ክፍል ነው፡፡ በምንመገባቸው ምግቦችና መጠጦች እንዲሁም ለተለያዩ በሽታዎች ማከሚያነት በምንወስዳቸው መድሃኒቶች ውስጥ የሚገኙና ለሰውነታችን አላስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ሁሉ በጉበት አማካኝነት እየተመረጡ እንዲወገዱ ይደረጋል፡፡ ቀይ የደም ሴሎቻችን የአገልግሎት ዘመናቸውን ሲያጠናቅቁ የሚወገዱትም በዚሁ በጉበታችን አማካኝነት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጉበታችን ፋቲ አሲድ፣ ፕሮቲን፣ ጉሉኮስንና በሽታን ለመከላከል የሚያስችሉ ንጥረ ነገሮችን እያመረተ ለሰውነታችን ክፍሎች እንደዳረሱ ያደርጋል፡፡ የዚህ የሰውነታችን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ሰጪ የሆነው የሰውነታችን ክፍል በህመም መጠቃት በሰውነታችን ሥርዓተ ዑደት ላይ ከፍተኛ ተፅእኖን ያሳድራል፡፡
ጉበትን በእጅጉ በመጉዳት ከሚታወቁ ነገሮች መካከል አልኮል ዋንኛው ነው፡፡ በአልኮል ሳቢያ የሚከሰተው የጉበት ስብ በሽታ በርካቶችን ለሞት እየዳረገ እንደሚገኝ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ሃኪም የሆኑት ዶ/ር አብርሀም ባየልኝ እንደሚናገሩት አልኮል አመጣሽ በሆነው የጉበት ስብ በሽታ የተጠቁ ሰዎች አምስት አመት በህይወት የመቆየታቸው እድል 50በመቶ % ብቻ ነው፡፡ በሽታው የጉበትን የመሥራት አቅም በፍጥነት የሚያዳክምና ከአገልግሎት ውጪ የሚያደርግ በመሆኑ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ለህልፈት የመዳረጋቸው እድል ከፍተኛ ነው፡፡ በሽታው ምንም አይነት ምልክቶችን ሳያሳይ ሊቆይ እንደሚችል የሚገልፁት ሃኪሙ፤ ከ75% በላይ የሚሆኑት የጉበት ስብ ህሙማን በበሽታው የመያዛቸውን ምልክት የሚያሳዩት ጉበታቸው የመጨረሻ ደጃ ላይ ሲደርስና ውሃ መያዝ ሲያቅተው ነው ይላሉ፡፡ የበሽታው ስርጭት በአገራችን እየጨመረ መምጣቱን የጠቆሙት ዶ/ር አብርሃም፤ በተለይ እድሜያቸው ከአርባ ዓመት በላይ የሆኑና አልኮል አዘውታሪ ሰዎች በበሽታው የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ እንደሆነና ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያለባቸው ህፃናትም ለበሽታው ሊጋለጡ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
የጉበት ጤና በማቃወስ ከሚታወቁት ነገሮች መካከል አንዱና ዋንኛው በሆነው ስብ የተጠቃ ጉበት ለጉበት ስብ በሽታ የሚጋለጥ ሲሆን ይህም በሁለት ምክንያቶች የሚከሰትና ጉበትን ወደ ቃጫነት በመለወጥ ከጥቅም ውጪ የሚያደርግ በሽታ ነው፡፡ የጉበት ስብ በሽታ ከሚከሰትባቸው ሁለት ምክንያቶች መካከል አንደኛው የአልኮል መጠጥ ሲሆን ሌላው ከአልኮል ውጪ በሆኑ ሌሎች ምክንያቶች ማለትም ለተለያዩ በሽታዎች ማከሚያነት የምንወስዳቸው መድሃኒቶች እንዲሁም የስኳር በሽታ፣ ውፍረት፣ ጉሉኮስ የማከማቸት ችግርና ኮፐርና ዚንክ የተባሉ ማእድናትን በሰውነት ውስጥ ማከማቸት… ለጉበት ስብ በሽታ መነሻ ምክንያት ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡ የአልኮል መጠጦች በጉበት ስብ በሽታ ለመጠቃት 40በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ሃኪሙ ገልፀዋል፡፡
የአልኮል መጠጦች ለጉበት ስብ በሽታ መነሻ የሚሆኑባቸውን መንገዶች ሃኪሙ ሲያብራሩ “የአልኮል መጠጦችን በምንጠጣበት ጊዜ በአልኮሉ ውስጥ የሚገኙና ለሰውነታችን ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች ጥቅም ላይ ከዋሉ በኋላ ቅሪቱ ንጥረ ነገር በጉበታችን ውስጥ ያልፋል፡፡ በዚህ ጊዜም የጉበታችን ሴሎች ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ጉበታችን በአግባቡ ሥራውን እንዳያከናውን ያደርገዋል፡፡ ጉበታችን ስራውን በአግባቡ ማከናወን ሲሳነው ወደ ሰውነታችን የገቡትና በጉበታችን አማካኝነት መጣራት የሚገባቸው ንጥረ ነገሮች በሰውነታችን ውስጥ ዝም ብለው ይከማቻሉ፡፡ በዚህ ጊዜም ጉበታችን ከመጠን በላይ በሆኑ ስቦች እንዲጨናነቅ ያደርጋል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ የጉበታችንን ሴሎች ወደ ቃጫነት በመቀየር ጉበታችን ፋትን ማመንጨትና መጠቀም እንዳይችል እንዲሁም ውሃ መያዝም እንዲያቅተው ያደርገዋል፡፡ ጉበት ሲታመም ፈሳሽ የመቋጠር አቅሙን ያጣል፡፡ ይህም ፈሳሽ በሆዳችን ውስጥ እንዲጠራቀም በማድረግ ሆዳችንን ያሳብጠዋል፡፡ መጣራት ሲኖርባቸው ሳይጣሩ ቀርተው በሰውነታችን ውስጥ የተጠራቀሙት መርዛማ ንጥረ ነገሮችም በደም አማካኝነት ወደ ጭንቅላታችን ውስጥ ገብተው ሩሃችን ያስቱናል፡፡ በተጨማሪም ፕሮቲን ጉሉኮስ፣ ፋትና በሽታን የሚከላከሉ ንጥረ ነገሮች በሰውነታችን ውስጥ መመረታቸው፣ መከማቸታቸውና በጥቅም ላይ መዋላቸው ያቆማል ብለዋል፡፡
ከአልኮል ውጭ የጉበት ስብ በሽታን ከሚያስከትሉ ነገሮች መካከል የሚጠቀሰው ለተለያዩ ህመሞች የምንወስዳቸው የተለያዩ ይዘቶች ያሏቸው መድሃኒቶች ናቸው፡፡ በተለይ ቴትራሳይክሊን፣ የደም ብዛት መድሃኒቶች፣ ለካንሰር ህሙማን የሚታዘዙ መድሃኒቶችና ሆርሞኖች በዋናነት እንደሚጠቀሱም ዶክተር አብርሃም ገልፀዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከአቅም በላይ ካልሆነ በስተቀር መድሃኒቶች ተደራርበው እንዳይወሰዱ ለማድረግ የሚመከረው በመድሃኒቶች ሳቢያ የሚከሰቱ የጐንዮሽ ጉዳቶችን ለመቀነስ በማሰብ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የጉበት ስብ በሽታ ምንም አይነት ምልክቶችን ሳያሳይ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደሚችል የሚናገሩት ዶክተሩ፤ በአብዛኛው የችግሩ መኖር የሚታወቀው ጉበቱ ከጥቅም ውጪ ከሆነና ለመዳን እጅግ አስቸጋሪ ከሚሆንበት ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
አንዳንድ የጉበት ስብ በሽታ ህሙማን የእግር ማበጥ፣ የአይን ቢጫ መሆን፣ በቀኝ ጐን በኩል የህመም ስሜቶች መኖር ሊያጋጥማቸው እንደሚችልም ገልፀዋል፡፡ በሽታው ስር ያልሰደደ ከሆነና ጉበቱ ሙሉ በመሉ ከጥቅም ውጪ ከመሆኑ በፊት ከተደረሰበት በተለያዩ ቫይታሚኖችና መድሃኒቶች በሽታውን አክሞ ማዳን እንደሚቻል ጠቁመው ከጥቅም ውጪ ለሆነ ጉበት የሚሰጥ ህክምና በአገራችን ደረጃ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡
አልኮልን አዘውትሮ አለመጠጣት፣ መድሃኒቶችን አብዝቶ አለመጠቀም፣ በአመጋገብ ላይ ጥንቃቄ ማድረግና የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የጉበት ስብ በሽታን ለመከላከል እንደሚረዱ ዶክተር አብርሃም ገልፀዋል፡፡

Read 18318 times