Monday, 31 August 2015 08:54

በመልካም አስተዳደር ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት አልቻለም ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

     በመቀሌ እየተካሄደ የሚገኘው የኢህአዴግ 10ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ድርጅቱን የሚመሩ አዳዲስ አመራሮችን የሚመርጥ ሲሆን በጉባኤው መክፈቻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ባለፉት ዓመታት በመልካም አስተዳደር ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን ገልፀው በዚህ ጉዳይ ላይ ጉባኤው ወሳኝ አቅጣጫ ያስቀምጣል ብለዋል፡፡ ሰሞኑን አባል ድርጅቶቹ፡- ብአዴን፣ ደኢህዴን፣ ኦህዴድና ህውሓት ባደረጉት ጉባኤ የቀድሞ መሪዎቻቸውን በድጋሚ አስመርጠዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በየድርጅቶቻቸው ውስጥ ስራ አስፈፃሚ የነበሩ ነባር አመራሮች በሰሞኑ ጉባኤ ከስራ አስፈፃሚነት ወጥተዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አፈጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ፣ የውሃ መስኖ ኢነርጂ ሚኒስትሩ አለማየሁ ተገኑ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሶፊያን አህመድ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ በረከት ስምኦን፣ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም እንዲሁም ወደ ከፍተኛ የህወሓት አመራርነት ይመጣሉ ተብለው የተጠበቁት በሚኒስትር ማዕረግ የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪ ዶ/ር አርከበ እቁባይ ይገኙበታል፡፡
በኢህአዴግ ውስጥ ከጥቂት ዓመታት በፊት መተግበር በጀመረው የመተካካት መርህ፤ ከየድርጅቱ ነባር አባላት ከስራ አስፈፃሚነትና ከማዕከላዊ ምክር ቤት አባልነት መሸኘታቸው የሚታወስ ሲሆን ከህወሓት ተሰናብተው የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን፣ ዶ/ር አርከበ እቁባይ፣ አቶ ስብሃት ነጋ፣ አምባሳደር ብርሃነ ገ/ክርስቶስን ጨምሮ ሌሎች ነባር አባላት በሰሞኑ ጉባኤ እንዲመለሱ ተደርጐ የድምፅ ተሳታፊ እንዲሆኑ መወሰኑ አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል፡፡
ህወሓት ባለፈው ረቡዕ ባደረገው ስብሰባ፣ የጠ/ሚኒስትሩ የፖሊሲ አማካሪ አቶ አባይ ፀሐዬን ጨምሮ የህወሓት ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ሃጎስ፣ በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ አባዲ ዘሙ፣ የጠ/ሚ የደህንነት አማካሪ አቶ ፀጋዬ በርሄ፣ በፓርላማ የመንግሥት ተጠሪ ወ/ሮ ሮማን ገ/ሥላሴ፣ የህወሐት ፅ/ቤት ም/ኃላፊ አቶ ተወልደ በርኸና አቶ ተኽለወይኒ አሰፋ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት በክብር አሰናብቷል፡፡ ከታሰበው ቀን በላይ የፈጀው የህወሓት ድርጅታዊ ጉባኤ ከትናንት በስቲያ አቶ አባይ ወልዱን የድርጅቱ ሊቀመንበር እንዲሁም ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤልን ም/ሊቀመንበር አድርጐ በመምረጥ የተጠናቀቀ ሲሆን ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ወ/ሮ አዜብ መስፍን፣ አቶ አለም ገ/ዋህድ፣ አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ ዶ/ር አዲስአለም ባሌማ፣ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔርና አቶ በየነ መክሩ የህወሓትና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አድርጐ መርጧል፡፡ ጠንከር ያለ ክርክር ተደርጐበታል የተባለው የህወሐት ጉባኤ፤ ዶ/ር አርከበ እቁባይን ወደ ሥራ አስፈፃሚነት ያመጣል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ዶ/ር አርከበ በስራ አስፈፃሚነትም ሆነ ከ45ቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ውስጥ ሳይካተቱ ቀርተዋል፡፡ ባለፈው ጉባኤ በመተካካት ከተሸኙ በኋላ በሰሞኑ ጉባኤ ወደ ፓርቲው እንዲመለሱ ተደርገው ነበር የተባሉት አምባሳደር ስዩም መስፍን፣ አቶ ስብሃት ነጋ፣ አምባሳደር ብርሃነ ገ/ክርስቶስና ሌሎችም በማዕከላዊ ም/ቤት አለመመረጣቸው ታውቋል፡፡ ከህወሓት ሊለቁ ይችላሉ ተብለው የነበሩት የወ/ሮ አዜብ መስፍን በድጋሚ በስራ አስፈፃሚ አባልነት መመረጥም ብዙዎች ያልጠበቁት ነበር፡፡ በህወሓት ጉባኤ ጠንካራ ውይይት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል የመልካም አስተዳደር ችግር ተጠቃሽ ሲሆን፤ የትግራይ ህዝብ ለስደትና ለልመና እየተዳረገ ነው፣ በመልካም አስተዳዳር እጦት ኢንቨስተሮች ከክልሉ እየሸሹ ነው የሚሉ ቅሬታዎች ከጉባኤው ተሳታፊዎች ተሰንዝረዋል፡፡የብሄረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) በበኩሉ፤ በባህር ዳር ባደረገው ድርጅታዊ ጉባኤ ብዙም የአመራር ለውጥ ሳያደርግ ምክትል ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን የድርጅቱ ሊቀመንበር፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡ በተጨማሪም አቶ ብናልፍ አንዷለም፣ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈጉባኤ አቶ ካሣ ተክለብርሃን፣ አቶ አለምነው መኮንን፣ ዶ/ር አምባቸው መለሰ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው፣ የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ እና አቶ ተስፋዬ ጌታቸውን የድርጅቱና የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ሆነው ሲመረጡ፤ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበውን ጨምሮ አቶ ጌታቸው ጀምበሩ፣ ወ/ሮ ዝማም አሰፋና አቶ ለገሰ ቱሉ የብአዴን ስራ አስፈፃሚ አባል በመሆን ተመርጠዋል፡፡ ከ4 ዓመት በፊት በአዳማ በተካሄደው 8ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ፣ በክብር ተሰናብተው የነበሩት የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ አዲሱ ለገሠ ሰሞኑን ባህርዳር ላይ በተካሄደው የብአዴን ጉባኤም፣ ከብአዴን ማዕከላዊ ም/ቤት አባልነታቸው በክብር የተሰናበቱ ሲሆን ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን በስራ አስፈጻሚነት ሳይመረጡ ቀርቷል፡፡
ሰሞኑን በአዳማ ከተማ 8ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ያካሄደው የኦሮሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) እንዲሁ የከፍተኛ አመራር ለውጥ አላደረገም፡፡ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድር ሊቀመንበር፣ ወ/ሮ አስቴር ማሞ ምክትል እንዲሁም አቶ ዳባ ደበሌ፣ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ፣ አቶ አብዱላዚዝ መሃመድ፣ አቶ በከር ሻሌ፣ አቶ ድሪባ ኩማ፣ አቶ በዙ ዋቅቤካ እና አቶ ኡመር ሁሴን ለድርጅቱና ለኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚነት የተመረጡ ሲሆን በተጨማሪም አቶ ለማ መገርሳ፣ አቶ እሸቱ ደሴ፣ አቶ ሰለሞን ኩቹ፣ አቶ አበራ ሀይሉ፣ አቶ አብይ አበበና አቶ ተፈሪ ጥያሮ በኦህዴድ ስራ አስፈፃሚነት ተመርጠዋል፡፡ ድርጅቱ 81 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትንም መርጧል፡፡
ድርጅቱ በጉባኤው ክልሉን በርዕሰ መስተዳድርነት ያገለገሉትንና ኋላም የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባኤ የነበሩትን አቶ አባዱላ ገመዳን፣ አቶ አለማየሁ ተገኑና አቶ ሶፊያን አህመድን በስራ አስፈፃሚነት አልመረጠም፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) በበኩሉ፤ ሃዋሳ ላይ ባካሄደው ጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን የድርጅቱ ሊቀመንበር፣ የትምህርት ሚኒስትሩን አቶ ሽፈራው ሽጉጤን ምክትል አድርጎ የመረጠ ሲሆን የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬን፣ አቶ መኩሪያ ኃይሌ፣ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፣ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ አቶ መለሰ አለሙንና ዶ/ር ተከስተብርሃን አድማሱን የደኢህዴንና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አድርጎ መርጠዋል፡፡ እኒህን ጨምሮ አቶ ክፍሌ ገ/ማሪያም፣ የብሄራዊ ባንክ ገዢ የነበሩትን አቶ ተክለወልድ አጥናፉ፣ አቶ ታገሠ ጫፎ፣ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ አቶ ሣኒ ረዲ እና ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም የደኢህዴን ስራ አስፈፃሚ ሆነው ተመርጠዋል፡፡
የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማሪያም ከኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚነት ሲነሱ ዶ/ር ካሱ ኢላላ ከድርጅቱ በክብር ተሸኝተዋል፡፡ አራቱ ድርጅቶች በዋናነት የመጀመሪያውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈፃፀም ከገመገሙ በኋላ በሁለተኛው አፈፃፀም ጉዳይ ላይ የመከሩ ሲሆን በየክልሎቹ የታዩ የመልካም አስተዳደርና አመራር ችግሮችን የፈተሹ ግምገማዎችን ማካሄዳቸው ተጠቁሟል፡፡ ከትናንት ጀምሮ እየተካሄደ በሚገኘው 10ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ፣ ከእያንዳንዱ ድርጅት፣ 250 በአጠቃላይ አንድ ሺህ ድምፅ መስጠት የሚችሉ የጉባኤ አባላትን ጨምሮ አጋር ፓርቲዎችና ጥሪ የተደረገላቸው ከ500 በላይ የአደረጃጀት አባላትና ደጋፊዎች እየተሳተፉ ሲሆን በጉባኤው ማጠናቀቂያ ግንባሩን የሚመሩ የስራ አስፈፃሚ አባላትና ሊቃነ መናብርት ይመረጣሉ፡፡
የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በድጋሚ በሊቀመንበርነት እንደሚመረጡ ከወዲሁ ተገምቷል፡፡
በኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ድርጅቱ በተለይ በመልካም አስተዳደር ጉዳይ ላይ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን ገልፀው በጉባኤው ከፍተኛ ውይይት እንደሚደረግበት ጠቁመዋል፡፡ ጉባኤው እስከ ሰኞ በሚኖረው ቆይታ የተጠናቀቀውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈፃፀም፣ ገምግሞ ለቀጣዩ የትኩረት አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሏል፡፡

Read 7225 times