Monday, 31 August 2015 08:40

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠቅላላ ሀብቱን ወደ 303.6 ቢሊየን ብር አሳደገ

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(1 Vote)

     የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት አምስት ዓመታት ጠቅላላ ሀብቱን ወደ 303.6 ቢሊየን ብር ማሳደጉን ገለፀ፡፡ የባንኩ የኮሙኒኬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ እንደተናገሩት፤ ባንኩ ከአምስት ዓመታት በፊት የነበረው ሀብት 74.2 ቢሊየን ብር ነበር፡፡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም የባንኩ ገቢ ወደ 23 ቢሊየን ብር ማደጉንና ከታክስ በፊት 12.6 ቢሊየን ብር ትርፍ ማግኘቱ ተገልጿል፡፡ ባንኩ አሁን ካሉት 965 ቅርንጫፎች ውስጥ 754ቱ ባለፉት አምስት ዓመታት የተከፈቱ ሲሆን የባንኩ ደንበኞችም ቁጥር 10.7 ሚሊየን ደርሷል፡፡ የኤቲኤም ተጠቃሚዎቹ ቁጥር 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን በቀጣይም ዘመናዊ የባንኪንግ ስርአቶችን በመዘርጋትና የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት፣ በ2025 በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን አልሞ እየሰራ እንደሚገኝ አቶ ኤፍሬም ተናግረዋል፡፡
የአገር ውስጥ ቅርንጫፎችን ከማስፋት በተጨማሪም በውጪ አገራት ቅርንጫፎችን ለመክፈት ጥናቶች በመጠናቀቅ ላይ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ባንኩ ለትላልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች 322 ቢሊየን ብር ያቀረበ ሲሆን ይህም የእቅዱ 187 በመቶ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከሶስት እጥፍ በላይ ማደግና የውጪ ምንዛሪ ገቢው መሻሻል ከዕቅድ በላይ አፈፃፀም እንዲያስመዘግብ አስችሎታል ተብሏል፡፡አንጋፋው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሁኑ ጊዜ 23 ሺህ የሚደርሱ ሰራተኞች በስሩ ያስተዳድራል፡፡

Read 1309 times