Monday, 31 August 2015 08:40

የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጐች ቁጥር ከተገመተው 55 በመቶ ጨመሯል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

መንግስት ለአስቸኳይ እርዳታ 33 ሚ. ዶላርቢያሰባስብም፣ ተመድ 230 ሚ. ዶላር ያስፈልጋል ብሏል
• “አብዛኛው ተረጂ የሚገኘው በኦሮምያ ክልል ነው”

   የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ በተከሰተው የዝናብ እጥረት ሳቢያ የምግብ እህል እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ከዚህ በፊት ከተገመተው በላይ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንና 4.5 ሚሊዮን መድረሱን አስታወቀ፡፡
አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣን በበኩላቸው፤ ችግሩን ለመፍታት ክልሎች ራሳቸው ከሚመድቡት በጀት በተጨማሪ መንግሥት 700 ሚ. ብር መድቦ ለተረጂዎች ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቅሰው ከተረጂዎች መካከል 40 በመቶ ያህሉ በኦሮምያ ክልል እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ትብብር ቢሮ ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ አጃንስ ፍራን ፕሬስ ትናንት እንደዘገበው፣ በአመቱ የዝናብ መጠኑ ከተገመተው በታች መሆኑን ተከትሎ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ከተገመተው 2.9 ሚሊዮን የ55 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 4.5 ሚሊዮን ደርሷል፡፡
በኢትዮጵያ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ትብብር ቢሮ ሃላፊ ዴቪድ ዴል ኮንቴ እንዳሉት፤ በዝናብ እጥረቱ ክፉኛ የተጎዱት የአገሪቱ አካባቢዎች ምስራቃዊ አፋርና ደቡባዊ ሶማሌ ክልሎች ሲሆኑ በአንዳንድ የኦሮምያ፣ የትግራይና የአማራ ክልሎች አካባቢዎችም፣ ባልተለመደ ሁኔታ የከብቶች ግጦሽና የውሃ ሃብቶች እጥረት ተከስቷል፡፡በአሜሪካ መንግስት የሚደገፈው “ፋሚን ኧርሊ ዋርኒንግ ሲስተምስ ኔትወርክ” የተባለ የርሃብ ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ ተቋምም፤ በኢትዮጵያ በርካታ እንስሳት በመኖ እጥረት ተጠቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ ማስጠንቀቁንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡የኢትዮጵያ መንግስት ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ 33 ሚሊዮን ዶላር አሰባስቧል ያለው ዘገባው፤ ይሄም ሆኖ ግን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ መንግስት በመጪዎቹ አራት ወራት ጊዜ ውስጥ 230 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ማስታወቁን አመልክቷል፡፡የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ሃላፊዎች ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ምግብ የማከፋፈሉ እንቅስቃሴ ፈጣን አለመሆኑ እንዳሳሰባቸው ጠቁሞ፣ ለዚህ ችግር መከሰት አስተዋጽኦ ካበረከቱ ጉዳዮች መካከልም በጅቡቲ ወደብ ያለው መጣበብ አንዱ ነው ብሏል፡፡

Read 1359 times