Monday, 24 August 2015 10:19

15 ሺህ ቻይናውያን በኢንተርኔት ወንጀል ታስረዋል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

- ፖሊስ በህገ ወጥነት የተጠረጠሩ 66 ሺህ ያህል ድረ ገጾችን እየመረመረ ነው
       - ቻይናውያን በአሜሪካ ላይ 700 ያህል የኢንተርኔት ጥቃቶችን ፈጽመዋል


     የቻይና ፖሊስ የአገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ በሚጥሉ አገር አቀፍና አለማቀፍ የኢንተርኔት ወንጀል ተግባራት ላይ ተሰማርተው ተገኝተዋል ያላቸውን 15 ሺህ ያህል ዜጎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ባለፈው ማክሰኞ ማስታወቁን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
የቻይና የደህንነት ሚኒስቴርን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የአገሪቱ ፖሊስ ከኢንተርኔት ጋር የተያያዙ 7 ሺህ 400 የወንጀል ክሶችን ሲመረምር ቢቆይም የተጠቀሱት 15 ሺህ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት በምን ያህል ጊዜ ውስጥ እንደሆነ አልገለጸም፡፡
የቻይና መንግስት ባለፈው ወር ኢንተርኔትን ማጽዳት የተሰኘ መሰል ወንጀሎችን መከላከል የሚያስችል የስድስት ወራት ብሄራዊ ዘመቻ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን የጠቆመው ዘገባው፤ ተጠርጣሪዎችን በማሰር የተጀመረው እርምጃ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአገሪቱ የደህንነት ሚኒስቴር ማስታወቁን ገልጿል፡፡
ዘመቻው በኢንተርኔት የሚሰሩ ወንጀሎችን ከመከታተልና ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ ከማቅረብ በተጨማሪ ተደራጅተው በኢንተርኔት ወንጀል የሚሰሩ ቡድኖችን የማጥፋት ተልዕኮ እንዳለውም ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የቻይና ፖሊስ ህገወጥና ጉዳት የሚያስከትሉ መረጃዎችን በሚያስተላልፉ እንዲሁም የወሲብ፣ የጦር መሳሪያዎችና የቁማር ማስታወቂያዎችን በሚያሰራጩ 66 ሺህ ያህል የአገሪቱ ድረገጾች ላይ ምርመራ ሲያደርግ መቆየቱንም አስረድቷል፡፡
ኤንቢሲ ኒውስ በበኩሉ፤ የተደራጁ ቻይናውያን የኢንተርኔት ዘራፊዎች የአሜሪካን ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣናት የኢሜይል ቁልፍ ሰብረው በመግባት የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን እንደፈጸሙ መረጋገጡን ዘግቧል፡፡
ቻይናውያን የኢንተርኔት አጭበርባሪዎች ባለፉት አምስት አመታት በአሜሪካ ላይ ለ700 ጊዜያት ያህል ጥቃት ፈጽመዋል ያለው ዘገባው፤ ከ600 በላይ የሚሆኑት ስኬታማ ጥቃቶች የተፈጸሙትም በአሜሪካ የመንግስት፣ የግልና የኩባንያ ድረገጾችና የኢሜል አድራሻዎች ላይ መሆኑንም ገልጿል፡፡

Read 3006 times