Monday, 24 August 2015 10:18

የካናዳው ኩባንያ በአለም ረጅሙን ማማ ሊገነባ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

20 ኪሎ ሜትር ቁመት ይኖረዋል፣ “የጠፈር አሳንሰር” ይገጠምለታል
   ቶዝ ቴክኖሎጂ የተሰኘው የካናዳ የጠፈር ምርምር ቴክኖሎጂ ኩባንያ በዓለማችን ትልቁ እንደሚሆን የተነገረለትንና 20 ኪሎ ሜትር ቁመት ያለውን ሰማይ ጠቀስ ማማ በመገንባት፣ ረጅሙን የጠፈር አሳንሰር ሊዘረጋ መሆኑን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
የጠፈር ተመራማሪዎችን ያለ መንኮራኩር በቀጥታ ወደ ጠፈር ማጓጓዝ የሚችለው  አሳንሰር፤ ጠፈርተኞችን በመንኮራኩር ወደ ጠፈር ለመውሰድ ከሚያስፈልገው ነዳጅ 30 በመቶ ያህል ያነሰ ነዳጅ እንደሚጠቀምና ወጪ ቆጣቢ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የጠፈር አሳንሰሩ ዲዛይነር የሆኑት ዶ/ር ብሬንዳን ኩይኔ እንዳሉት፣ ጠፈርተኞች በአሳንሰሩ ተሳፍረው ከመሬት በ20 ኪሎሜትሮች ርቆ ከሚገኘው የማማው አናት ላይ ከወጡ በኋላ፣ በቀላሉ በጠፈር አውሮፕላኖች እየተሳፈሩ ወደ ጠፈር ጠልቀው የሚገቡበትና ስራቸውን የሚያከናውኑበት ዕድል ይፈጠርላቸዋል፡፡
አሳንሰሩ የሚገጠምበት ሰማይ ጠቀስ ማማ፣ በአሁኑ ወቅት የአለማችን ረጅሙ ህንጻ በመሆን ክብረ ወሰን ይዞ ከሚገኘውና 830 ሜትር ርዝማኔ ካለው የዱባዩ ቡርጂ ከሊፋ ህንጻ በ20 እጥፍ ያህል ቁመቱ እንደሚረዝም የጠቆመው ዘገባው፤ ማማው  ከዚህ በተጨማሪም ለነፋስ ሃይል ማመንጫነት፣ ለኮሙኑኬሽንና ለቱሪዝም አገልግሎት እንደሚውልም ገልጿል፡፡
ማማው ቁመተ ረጅም ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በንፋስ የመገንደስ አደጋ ሊገጥመው አይችልም ወይ ለሚለው የብዙዎች አስተያየት ምላሽ የሰጡት የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ካሮሊን ሮበርትስ፤ ስጋት አይግባችሁ፣ መሰል አደጋዎችን መቋቋም እንዲችል አድርገን ነው ንድፉን የሰራነው ብለዋል፡፡
የአሜሪካ የፈጠራ መብቶች ቢሮ፤ የካናዳው ኩባንያ ላቀረበው ልዩ የሆነ የጠፈር ማማና አሳንሰር ፈጠራ እውቅና መስጠቱንና ፕሮጀክቱም ተቀባይነት ማግኘቱን ዘገባው አክሎ ጠቁሟል፡፡ 

Read 2338 times