Monday, 24 August 2015 10:17

የማንዴላ የልጅ ልጅ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተከሰሰ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ሌላ የልጅ ልጃቸውም በድብደባ ወንጀል ተከስሶ ነበር
   የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንትና የጸረ አፓርታይድ ታጋይ የኔልሰን ማንዴላ የልጅ ልጅ የሆነው ማንዴላ፣ አንዲትን ደቡብ አፍሪካዊት የ15 አመት ልጃገረድ አስገድዶ በመድፈር ወንጀል ተከስሶ ባለፈው ሰኞ ፍርድ ቤት መቅረቡን ዘ ጋርዲያን ዘገበ።
ልጃገረዷን ጆሃንስበርግ ውስጥ በሚገኝ አንድ መጠጥ ቤት ውስጥ አስገድዶ ደፍሯል በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው የ24 አመቱ ቡሶ ማንዴላ፤ ባለፈው ሰኞ  ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን በሳምንቱ መጨረሻ በጆሃንስበርግ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ ጉዳዩ እንደሚታይ ይጠበቃል፡፡
ቡሶ ማንዴላ ከሁለት ሳምንታት በፊት ልጃገረዷ በመጠጥ ቤቱ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ሳለች ተከታትሏት ሄዶ አስገድዶ ደፍሯታል መባሉን የጠቆመው ዘገባው፣ ጥቃቱ የደረሰባት ልጃገረድ ክስ መመስረቷን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉንም አስታውሷል፡፡
ተጠርጣሪው የማንዴላ የልጅ ልጅ ስለሆነ ብቻ ከሌሎች ወንጀለኞች ተለይቶ የሚታይበት ምክንያት የለም ያለው የጆሃንስበርግ ፖሊስ፤ እንደማንኛውም ተጠርጣሪ እንደሚያዝና ጉዳዩ በፍርድ ቤት ተጣርቶ የአገሪቱ ህግ ባስቀመጠው መሰረት ተገቢው ውሳኔ እንደሚሰጠው አስታውቋል፡፡
ተከሳሹ ማንዴላ ከሶስቱ ሚስቶቻቸው የመጀመሪያዋ ከሆነችው ኤቭሊን ማሴ ከወለዷቸው ልጆች ከአንዷ እንደተወለደና አያቱ ማንዴላ በህይወት ሳሉ በተናዘዙለት መሰረት 300 ሺህ ዶላር እንደወረሰ ያስታወሰው ዘገባው፤ ማንድላ ማንዴላ የተባለው ሌላ የኔልሰን ማንዴላ የልጅ ልጅም ከወራት በፊት አንድን የ40 አመት ደቡብ አፍሪካዊ ደብድቧል በሚል ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንደነበርም አክሎ ገልጿል፡፡

Read 3467 times