Monday, 24 August 2015 10:10

አምባና ትዝታ

Written by  አብደላ ዕዝራ
Rate this item
(6 votes)

    ለሎሬት ጸጋዬ የልደት ቀን መርበትበት
                       
   ነቢይ መኮንን ለሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ህልፈት የተቀኘው ለልደቱም ትዝ ይለኛል፤ “ሞተ ቢሉኝ እንኳን በአካል /በነብሱ ነብሴን የሚያከር/ አለው የውበት መዘውር /መሸብህ ይበሉኝ አንተን?/ ፀሐይና ከዋክብቱን፥ ሰማይ ላይ የዘራኸውን?” የጸጋዬ አካል እድሜው ቢያበቃም ብዕሩ በየወቅቱ የሌላን አእምሮና ምናብ እየገራ ይቀጥላል። “የባለቅኔ ቀለሙ // ሰከነ እንጂ ከሰለ አንበል፥ ቢከሰከስ እንኳን አፅሙ” ብሎ ነበር ሎሬት ጸጋዬ የካሳ ተሰማ ህልፈት የቆጨው እለት። ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 11 የልደት ቀኑ እንደ ነገሩ በዝምታ ደበዘዘ። ይቅርታ ይደረግልኝና የጸጋዬ ባለቤትና ልጆቹ ምነው ጀርባቸውን አዞሩበት? አንጋፋ ደራሲና ባለቅኔ አበራ ለማ በስደት ላይ - ኖርወይ - እያለ ለጸጋዬ እጅጉን ተብሰክስኮ አኩሪ ተግባር ፈፅሟል። የኖርወይ ደራሲያን ማኅበር ለሎሬት ጸጋዬ ጥበብና አእምሮ እውቅና ለግሶ ሸልሞታል። ባለቅኔው ሞት ቢቀድመውም፥ ቤተሰቡ ሽልማትና ገንዘቡን ተረክበዋል፤ ለምን ከሽልማቱ ቆረሰው “እሳት ወይ አበባ”፥ “የከርሞ ሰው” ፥ “የእማማ ዘጠኝ መልክ” ... ለማሳተም አልተጣደፉም? ሚካኤል ሽፈራው የጸጋዬን ሰላሳ አምስት ዋና ዋና ተውኔቶች ጠቅሷል። [ምሥጢረኛው ባለቅኔ፥ ገፅ 357-361]።
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ የጸጋዬን ታሪካዊ ተውኔቶች አሳትሟል። ማንኩሳ አሳታሚ - ዓይናለም መጻሕፍት - የበዐሉ ግርማን ልቦለዶች ዳግም በማተሙ ተደራሲ ፈንድቋል። የሎሬት ጸጋዬ ቤተሰብ፣ አቶ ዓይናለምን የመሰለ ግለሰብ ቢያማክሩ የባለቅኔው ግጥሞች፥ ተውኔቶች፥ ትርጉሞች እና የጥናት ወረቀቶች ታትመው ለአንባቢያን ሊዳረሱ ይችላሉ። ነገሩ ከልብ ካለቀሱ ... ነው። ሞት ሎሬት ጸጋዬን ከቀማን እኮ ከመንፈቅ በኋላ አስር አመት ሊሞላው ነው። ሎሬት ጸጋዬ ለሌላው የተቀኘው፥ ለብዕሩም እንደ ትንቢት መደመጡ ይከነክናል፤ “የብዕር አሟሟት ሌላ፥ /ሲፈስ የብሌኑ ኬላ/ የፊደል መቅረዝ አሟሟት /ከውስጥ ነው እንደጋን መብራት”። የሎሬት ጸጋዬ የፈጠራና የምርምር ውጤት መጋረዱ ተገቢ አይደለም፤ ለኔ በአማርኛ ሥነግጥም ተወዳዳሪ የሌለው ብርቅና ዕንቁ ባለቅኔ ነው።
ይህን የቁጭት ድባብ ለማርገብ ባለቅኔው በተባዕትና እንስት አንደበት - personna – ስለፍቅር፥ ስለማይሰክነው የወንድና የሴት ፍትግያ የተመሰጠባቸውን ሁለት ባለ አንድ አንጓ ግጥሞች ገረፍ አድርገን ዜማውን እናጣጥምለት።
መሸ ደሞ አምባ ልውጣ
አምባ ወጥቼ እኩለ-ሌት፥ ስለት ገብቼ በስሟ
ከርሞ ሰይጣን በሷ አስቶኝ፥ ልገላገል
 ከሕመሟ
ጠበሏ አፋፍ በጨረቃ፥ ደጋግሜ፥ ማሕሌት
ቆሜ
ሆዴ ቃትቶ ባር ባር ብሎ፥ እርቃኔን ከሷ
 ታድሜ
ደጀ ሰላሟን በአራት እግር፥ ተንበርክኬ
ተሳልሜ
በሥጋዬ እሚነደውን፥ በጸሎት ላቤ አጣጥሜ
እፎይ ብዬ አመስግኜ፥ ውዳሴዋን ደጋግሜ ....
ገና ከደጅዋ እልፍ ሳልል፥ ደሞ ይምጣ የቁም
 ሕልሜ ?
ሌት በጥምቀቷ የነጣው፥ ነጋ፥ ደፈረሰ ደሜ።
ለሷ እንጂ ለኔ አልያዘልኝ፥ አዬ የስለት
 አታምጣ !
በውጣ ውረድ በጠበል፥ ባሣር ወዜ ቢገረጣ
ልክፍቷ እንደሁ አልለቀቀኝ፥ መሸ ደሞ አምባ
 ልውጣ !
[እሳት ወይ አበባ ፥ 1951፥ ገፅ63]
ጸጋዬ በዚህ ጥልቀት ሲቀኝ፥ ዕድሜው ገና ሃያ አንድ ነበር፤ የቋንቋ ምጥቀቱና የአስተሳሰብ አድማሱ ከመነሻው የረቀቀ ነበር። አምባ በከፊልም ቢሆን ሜዳነት የተለገሰ ኮረብታ ነው። እንዲሁም ብዙ ቤቶች የተሰባሰቡበት መንደርም ይሆናል። እኩለ ሌሊት ተናጋሪው እየተቅበዘበዘ ሰው ዝር ከማይልበት አምባ -ቤተ ክርስትያን የመሰለ መቼት- በጨረቃ ብርሃን ልቡን ፈልቅቆ ፍቅሩን ያስታምማል። ከመንፈሳዊ ስብከት ያቀረረውን የሄዋንና የሰይጣን መመሳጠር እያባነነው ይሳላል፤ “ከርሞ ሰይጣን በሷ አስቶኝ፥ ልገላገል ከሕመሟ” ብሎ ቢመኝም ለአካሏ የሚነደውን ፍትወት ማፈን አይችልም። ይህ በየዕለቱ የሚኖረው ትግል የማያበቃ ነው። ግጥሙን በጥሞና ብናነበው ተናጋሪው መንፈቀ ሌሊት ከክፍሉ ሳይወጣ፥ በምናቡ እንደ ቀናዊ ህልም የተቧጠጠበት ትምኔታዊ ጉዞ ነው።
የስጋና የመንፈስ ፍልሚያ ሰምና ወርቁ ነው፤ ፍቅር እንቅልፍ እየነሳን ዳር ላይወጣ እንደ ልክፍት ይመዘምዘናል። ግጥሙ ይተንተን ከተባለ ከስሜት ባሻገር የግለሰብ ማቅማማት፥ በጐ እንደ እኩይ እየተመነዘረ ስንላተም፥ ሥነልቦናዊ መገጣጠብ አንድምታዎቹ ጨረር ቋጥረዋል። እንስት፥የወንድ ልብ ከተተረተረላት ራመድ ራመድ ብሎ አፈፍ ሲያደርጋት እንጂ ግራ ቀኝ እየገላመጠ ሲያመነታ መች ትደፋፈራለች? ፍቅር እኮ የወደድናትን ላለመነፈግ፥ እንዳናወላውል ብርታት ይለግሰናል፤ ልብ ደግሞ ሌላው ሲያቅማማ ካጤነ ለድንገት ቅብጠት ሰለባ ሊሆንም ይችላል። “ገና ከደጅዋ እልፍ ሳልል፥ ደሞ ይምጣ የቁም ሕልሜ?/ ሌት በጥምቀቷ የነጣው፥ ነጋ፥ ደፈረሰ ደሜ።” የምናፈቅራት ሴት ከናፈቀችን፣ የጊዜ መንቀራፈፍ ያስበረግጋል።
ሎሬት ጸጋዬ ከአያሌ አማርኛ ገጣሚያን የተነጠለው በግጥሞቹ የተለበለበች እንስት ድምጿ እንዲደመጥ መፍቀዱ ነው፤ በአንደበቷ ይቀኛል። “ማን ነው ‘ምንትስ’?”፥ “ተወኝ” እና “ትዝታ” ግጥሞቹ ተጠቃሽ ናቸው።
             ትዝታ
ዓይንህን በዓይኔ ፀንሼ፥ የቀስቱን ጮራ
 እንደቋጠርኩ
ሌሊት በሕልሜ አማምጨህ፥ ሕመምህን
 እየፈጠርኩ
ቀን ጥላህን እንደለበስኩ
የፍቅራችንን ነበልባል፥ በቁም ሰመመን
 እንዳቀፍኩ
ልብ ውስጥ እንዳዜሙት ሙሾ፥ የሲቃ ስልት
 እንዳቃጨልኩ
የነፍሴን የእሳት ዘለላ፥ ጐዳናህ ላይ
እንዳነጠብኩ
እንደገደል ዳር ቄጠማ ፥ የሥጋት እንባ
እንደቃተትኩ
ሕይወቴን ላንተ እንዳሸለብኩ
ሕልምህን በጄ እንደዳሰስኩ
ያን የመጀመሪያ ሞቴን፥ በመሸ ቁጥር
እንደሞትኩ
አለሁ፥ እንደብኩን መረብ፥ ትዝታህን
እንዳጠመድኩ።
[እሳት ወይ አበባ፥ 1959፥ ገፅ199]
ይህ ግጥም ከላይ እስከ ታች ቁልቅል ይነባባል፤ ባልተለመደ ሁኔታ ከታች --- “አለሁ፥ እንደብኩን መረብ፥ ትዝታህን እንዳጠመድኩ።” --- ተነስተን ወደ ላይ እያነበብን ብንወጣ የትርጉም መዛባት ሳያስከትል በመንታ አቅጣጫ ያስደምማል። ከእያንዳንዱ ሀረግና ስንኝ የሚነዝሩት ዘይቤና ምስል ገለልተኛ አይደሉም፤ ምናብን ይናደፋሉ። ሙሉ ግጥሙ “ ኩ ኩ ኩ” በሚለው ፊደል ቤት መምታቱ፥ የተናጋሪዋ ልብና ህሊና ላይ ያልሰነፈው ቅጥቀጣ ይስተጋባል፤ ሰቆቃዋ ፈታኝ ነው። በዚህ ጥበባዊ ውበት ስለ ፍቅርና የአንዲት ሴት በስሜት የመለብለብ ርቀትና ቅርበት እስኪላተም የተቀኘበት ግጥም በአማርኛ አላነበብኩም።
“እንደገደል ዳር ቄጠማ ፥ የሥጋት እንባ እንደቃተትኩ” የመሰለ ስንኝ እንደ ድፍን ግጥም ሌጣውን አቅም አለው። መጠበቅ ጐዳት፤መዘንጋት ተሳናት፤ ያለ ማቅማማት ኅላዌዋን የለገሰችው ተባዕት ችላ ያላት ይመስላል። አሜሪካዊ ደራሲ ሄሚንግዌይ፤ “ሽማግሌውና ባህሩ” (መስፍን ዓለማየሁ ተርግሞታል) በተባለ ድንቅ ልቦለዱ ይታወቃል። ሎሬት ጸጋዬ በ“ትዝታ” ግጥሙ ስለቀረፃት ሴት የታዘበው አለ። “The most painful thing is losing yourself in the process of loving someone too much, and forgetting that you are special too.” ሌላውን በማፍቀር ማንነትሽን እስከ መነፈግ መብቃት ያማል፤ አንቺም ልዩ ሴት መሆንሽን መርሳት የለብሽም ባይ ነው። የጸጋዬ ሴት ይህ ሰቆቃዋ የተባዕቱን እሺነት ለማፍረጥ ከተጠናወታት እልህ የፈለቀ በመሆኑ፥ ስቃይ ትኮተኩታለች። የተሰወረ ቁስል ነው፤ ለማከም የሚያዳግት። ከሰመረ ፍቅር ይልቅ የወንዱ ትንፋሽ ያጠረበት ብኩን ትዝታ አከለ። ይህች አፍቃሪ የተለየ ጥንካሬ ይኖራት ይሆን ? ቁስሉም አልጠገገ፥ ልክፍቱም አልቀዘዘ፤ ግን ኅላዌ እየተፈረካከሰ ለፍቅር ያላትን ሥጋና መንፈስ መገበር እንዴት ወንዝ ያሻግራል? ወንድ በወንድ ለምን አይተካም?
ሎሬት ጸጋዬ በአካል ቢለየንም፥ መንፈሳችን የተሰለበው የብዕሩ ውጤት ለብርሃን ሳይበቃ በመጋረዱ ነው፤ በቤተሰቡም ችላ መባሉ ይሰቅቃል። ለሀገራችን ሥነጽሑፍ የሚቆረቆር ማንም አቅም ያለው ግለሰብ፥ ለድንቁ ባለቅኔ ብዕር ዘብ መቆም ይኖርበታል። የጸጋዬ የፈጠራ ውጤት አለመታተም እንደ ተደፈጠጠ በረሮ ቁብ ሳይሰጠው፥ ለምዕራቡ እግር ኳስ ከጐህ እስከ ዕንቁጣጣሽ ላንቃውን እየወለወለ የሚያገሳ ግለሰብ በዕውነት የረባ ሰው ነው ወይ? ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን “ተስፋ ባጣ ምድረ በዳ / ያንድ እውነት ይሆናል ዕዳ” ብሎ የተቀኘው ለራሱም ጭምር ይመስላል።

Read 4239 times