Monday, 24 August 2015 10:00

የዓለማየሁ ገላጋይ ትንቢታዊ ድምፆች

Written by 
Rate this item
(3 votes)

[የመጽሐፍ ቅኝት በአብነት ስሜ ]

    መቅድም
ወሪሳ በሚል ርእስ በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ 240 ገጾች ያሉት የአማርኛ ልቦለድ ታትሟል። የልቦለዱ ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ ይባላል። ይህ ብእሮግ የዚህ መጽሐፍ ቅኝት ነው። ቅኝቱን የማደርገው ልቦለድን-እንደ-ህልም-መፍታት በሚል ጽንሰ-ሐሳባዊ ማእቀፍ ውስጥ ነው። አንድ ደራሲ ከግለሰብ፣ ከቤተሰብና ከማህበረሰብ አልፎ የኅብረተሰብንም ህልም የሚያልምበት ጊዜ አለ። ይህ ሲሆን ደግሞ ደራሲ እንደ ህልም ዓላሚ፣ ድርሰት እንደ ህልም፣ ኀያሲ ደግሞ እንደ ህልም ፈች ይታያል።
ህልም እና ልቦለድ
የሰው ልጅ ሆኖ ህልም የማያልም የለም ይባላል። ችግሩ ምን ያህሉን ያስታውሰዋል ነው እንጂ ሁሉም ሰው ያልማል። ህልም ለጤናችንም ወሳኝ ነው ይባላል። የበቂ እንቅልፍ እጦት ጤናን እንደሚያቃውስ ይታወቃል። የዚህ ችግር ሁነኛው መንስዔ የእንቅልፍ ጊዜ ማጣቱ ሳይሆን እንዲያውም የህልም ጊዜ ማጣቱ እንደሆነ ከቅርብ ጊዜ ጥናትና ምርምሮች መረዳት ይቻላል። የህልም አስፈላጊነት እስከዚህም ይደርሳል።
በመስኩ ያሉ ባለሙያዎች ህልምን በየጊዜው መመዝገብ መቻል ጠቀሜታው የትየለሌ ነው ይላሉ። ከህልም ጥቅሞች ውስጥ አንዱ ላይ ብቻ እናትኩር። የሰው ልጅ በዕለት ተዕለት ህይወቱ በውጣ ውረዶች ውስጥ ያልፋል፤ ከአስጨናቂ ጉዳዮችና ጣጣዎች ጋር ይጋፈጣል። ታድያ አንዳንዴም ቢሆን ችግሩንና ህመሙን በግላጭ አፍርጦ ለማየት ጊዜ ያጣል። ያንን ስውሩ አእምሮ የሚባለው መዝግቦ ይይዝለታል።  ከጊዜ ማጣት ሌላ ድፍረትም የሚጠፋበት ጊዜ አለ።  የሰው ልጅ ጭንቁን፣ ጣሩንና  ሰቆቃውን ሆን ብሎ ለመርሳትና ከህይወቱ መዝገብ ውስጥ ለመሰረዝና ላለማስታወስ የሚጥርበትም ጊዜ አለ። ንቁው የአእምሮ ክፍል የሸሸውንና ያሸሸውን ስውሩ አእምሮ ደብቆ ይይዘዋል። ስለዚህ ችግሩ ይሸሸጋል እንጂ ጠፍቶ አይጠፋም፤የተረሳ ይመስላል እንጂ ተረስቶ አይረሳም።
ቀላሉንም ሆነ ከባዱን (አንዳንዴ ሰቅጣጩንም) ችግር ማታ አረፍ ባልን ጊዜ እየተግተለተለ ከፊታችን ይደቀናል። በዚህ ወቅት ሐሳብን እናመነዥካለን። የቻልነውን እንቆቅልሽ እንፈታለን፤ያልቻልነውን ለጊዜውም ቢሆን እናልፈዋለን። የፈራነውን ደግሞ እንሸሽገዋለን፤እንርቀዋለን።
በእውን ያልፈታነውን የህይወትና የኑሮ እንቆቅልሽ በህልም እናገኘዋለን። ለችግራችን መፍትሔ ስለምናገኝበት ነው ህልማችንን የምንመረምረው። አንዳንዱ ህልም ፊት ለፊትና ግልጽ ስለአልሆነ ህልም-ፈቺ እንፈልጋለን። የእእምሮ ጤና ችግር ያጋጠማቸውን ህሙማንም በህልማቸው ለመርዳት የሚደረግ የህክምና ሳይንስ አለ።
በህልም ውስጥ ትውስታ አለ። ትውስታው የትላንት፣ የበቀደም ብቻ ሳይሆን ያምና እና የካችአምና ሊሆን ይችላል። ከዚያም አልፎ ሀያና አርባ ዓመት ወደ ኋላ  የምንጓዝበት አጋጣሚ አለ። ይህ እንግዲህ በህይወት ዘመናችን ስለሆነው ነው። ትውስታ ከህይወት ዘመን ያለፈም እንደሚሆን በዘርፉ ጥናቶች በተደጋጋሚ ተጠቁሟል።
ይህ ምን ማለት ነው? አንድ ሰው የራሱን ብቻ ሳይሆን የአያቱን፣ የቅድመ አያቱንና  በጣም ወደ ኋላ ሔዶ የዘርማንዘሩን ወይም የነገዱን የጥንት ውሎና ክራሞት የሚያስታውስበት አጋጣሚ የትየለሌ ነው። ታዲያ ትውስታው ከሚገለጥባቸው መንገዶች ውስጥ ህልም አንዱና ዋነኛው ነው።
አሁን የህልምና የድርሰትን ቁርኝት እንይ። አንድ ደራሲ በፈጠራ ጽሑፉ ላይ በሚያተኮርበት ጊዜ ተመስጦው ህልምን ከማየት ጋር ይመሳሰላል። በዚህ አተያይ ደራሲው በድርሰቱ የሚያቀርብልን ህልሙን ነው ማለት ይሆናል። ህልሙ ደስ የሚልና ግልፅ የሚሆንበት ጊዜ አለ። በዚህ ጊዜ ፍችና ትንታኔ ውስጥ አንገባም። የአንዳንዱ ደራሲ ህልም ግን ከተራ ህልም ያለፈ ይሆናል። እንደዚህ ያለው ደራሲ የሀገሩን ህልም ነው የሚያልመው። በሌላ አነጋገር ደራሲው “ነቢይ” ነው፤ድርሰቱም “ትንቢት” ነው።
የአእምሮ ጤና ችግር ያጋጠመውን ግለሰብ ለማከም ህልሙ እየተመዘገበ ይመረመራል። የችግሩ ነቅ የት ነው? ህመሙን ያመጣው እሾህ የተተከለው ከምን ስፍራ ነው? በሌላ አነጋገር ሰንኮፉ ይፈለጋል። ሰንኮፉ ሲነቀል ብቻ ነው ቁስሉ ሙሉ በሙሉ ሊሽርና ህመሙም ሊድን የሚችለው።
የግለሰቦች ስብስብ ነችና ሀገርም እንደ ግለሰብ ትጨነቃለች፤በሰቆቃ ውስጥ ታልፋለች፤ ትቃትታለች፤ትጓጉራለች። በአንድ ቃልም ትታመማለች። ወይም ደግሞ ሁላችንም እንደ ሀገር እንደ ኅብረተሰብ እንታመማለን። ሁሉም ሰው ግን ሊታመም አይችልም። የሀገርን ህመም የሚታመም ደራሲ አለ። እንዲህ ዓይነቱ ደራሲ ህመማችንን ይታመማል፤ ህመማችንን ያልማል። ህልሙ ውስጥ ህመሙ አለ። ድርሰቱ ውስጥ ደግሞ ህልሙ አለ። ድርሰቱ የሀገር ህልም ነው። የሀገርን ችግርና ህመም ደግሞ በድርሰቱ ህልም ውስጥ መመርመር አለብን። የድርሰቱን ፍችና አንድምታ ትርጓሜ መውጣት ማለት ህመማችንን መመርመር ማለት ነው፤ መድኃኒትም ከዚያ ይገኛል። እኛ አልታመም ያልነውን ህመም ደራሲው ይታመማል። እኛ አላልም ያልነውን ህልም ደራሲው ያልማል። ህልሙን መስማትና መፍታት የኛ ፈንታ ነው። መፍታቱ ቢቸግረን እንኳ መስማቱን ግን መስማት አለብን። መፍታቱ ባስቸገረ ጊዜ ኀያሲ የዚህን ሥራ መስራት አለበት። ይህ የሒስ አንዱ ፈርጅ ነው።
በሀገራችን ተንሰራፍቶ ያለው የልቦለድ ሒስ ስልት በአብዛኛው መዋቅራዊ ነው። የትልም፣ የግጭት፣ የገፀባህርያት አሳሳል፣ የቋንቋ አጠቃቀምና የትረካ ቴክኒክ በመሳሰሉት ላይ ያተኩራል። ከዚህ የሚያፈነግጠው አልፎ፣ አልፎ ነው።
በቀደሙት ዘመናት በነበሩ አንዳንድ የአማርኛ ልቦለዶች ውስጥ ማኅበራዊ ሕፀፆች በተምሳሌታዊ አካሔድ ተገልጠዋል። በቅድመ-ሳንሱርና በድኅረ-ሳንሱር (አንዳንዱ የብዙኃኑ ሳንሱርና ትርጓሜ ነው) ይኼ ንጉሡን ለመንካት ነው፤ይኼ ፕሬዚደንቱን ለማሽሟጠጥ ነው እየተባለ ተነግሯል። የልቦለዱ ደራሲ ከዋናው ገፀባህሪ ጋርም እየተነፃፀረ ሲታይ ቆይቷል። በበዓሉ ግርማ ኦሮማይ ውስጥ ያሉ ገፀባህርያትም በወቅቱ ከነበሩ ባለሥልጣናት ጋር ያላቸው ተመሳስሎ በየደረጃው ተተንትኗል። ሒስ ግን ከዚህም በላይ መሄድ አለበት። ለምሳሌ በዳኛቸው ወርቁ አደፍርስ ውስጥ በመጨረሻ ወደ ገዳም የምታመራው ፂወኔ፤በሀገር ደረጃ ደራሲው እንደ ኢትዮጵያ ሳያያት አልቀረም ተብሎ እንደተገመተው ዓይነትና ከዚያም ያለፈ የአንድምታ ትርጓሜ ያስፈልገናል።
የዓለማየሁ ገላጋይ ወሪሳ
ወሪሳ በአንደኛ መደብ የተተረከ ልቦለድ ነው። ተራኪው የአማርኛ አስተማሪ ነኝ ይላል፤ ሊቅነቱ ግን ተረት ላይ ነው። በታሪኩ ውስጥ በቅርቡ ከክፍለሀገር ወደ አዲስ አበባ የተቀየረ አስተማሪ ነው። የተራኪው የአክስት ልጅ እስር ቤት ገብቷል። አክስት ስትሞት፣“ልጇ ከከርቸሌ እስኪወጣ ቤቱን እንድጠብቅላት ተናዘዘችብኝ” ይላል ተራኪው። ተራኪው በዚህ አኳኋን ነው ወሪሳ የሚባል ሰፈር የገባው። ወሪሳ ከእሪ በከንቱ የሚጎራበት የ“ወሮበሎች” ሰፈር ነው። እንዲህ የሚባል ሰፈር አዲሳባ ውስጥ ይኑር-አይኑር አላቅም። ከሌለ  የደራሲው ምናባዊ ፈጠራ ነው። የሰፈሩ የአስፈሪነት ገለፃ በመጽሐፉ የመጀመሪያ ዓረፍተ ነገር ይጀምራል። ተራኪው ገና ሲጀምር፣ “እኔ እንደ ኢየሱስ በወንበዴዎች መካከል ተቸንክሬአለሁ”ይለናል። ሰፈሩ ባጭር ቃል ሲዖል ነው፤ያስፈራል፤በጣም ያስፈራል። ተስፋ ያስቆርጣል።
ወሪሳ ተከታታይነትና ተለጣጣቂነት ያላቸው አስፈሪ ህልሞች የታጨቁበት ማህደር ነው። ህልሞቹ የተዘፈቅንበት ማኅበራዊ ውጥንቅጥ ነፀብራቅ ናቸው። ምን ያህል ወርደናል! ምን ያህል ተዋርደናል! ምን ያህል በክተናል! ያስብላሉ። የወሪሳ ህልሞች “እገሌ የጎዳና ተዳዳሪውን፣እገሌ የተማረውን፣ እገሌ ካድሬውን፣ እገሌ ተቃዋሚውን፣ እገሌ ገዥውን ፓርቲ፣ እገሌ ቤተክህነቱን ይወክላል” በሚል ብዙም ረብ በሌለው ፈሊጥ መፈታት ያለባቸው አይደሉም።
ህልሞቹ በትእምርታዊነት (ሲምቦሊዝም) የተሞሉ ናቸው። ተራ ቅዥት አይደሉም። በቅጡ ሊተነተኑ ይገባል። በትንተናው ደግሞ ደራሲው እንዲህ ሊል ፈልጎ ነው የሚለውንም አካሄድ ለጊዜውም ቢሆን ወደ ጎን ገፋ ማድረግ አለብን። እኔ እንደሚመስለኝ ደራሲው ምንም ሊል አልፈለገም። ህልሙን ነው የጻፈው። ህልሙ ደግሞ የሀገርና የኅብረተሰብ ህልም ነው። እኛ ማድረግ የሚገባን ህልሙን ማንበብና  መፍታት፣አንድም እንዲህ ማለት ነው እያልን ከሦስትና ከአራት የዘለሉ ትርጓሜዎች ማውጣት። ህልሙ ውስጥ ያገር ህመም አለ። ያን ያገር ህመም ሰንኮፍ መመርመር፣ ማመልከትና መንቀልም አለብን። ሌላው አማራጭ ሸፋፍኖ መተው ነው። ወይም ደግሞ ህመማችንን የታመመልንን ደራሲ ማንቋሸሽና ማውገዝ። ሌላ ደራሲ እስኪታመምልን መጠበቅ።
የወሪሳ ጥቂት አንድምታዎች
በወሪሳ ታሪክ ውስጥ ተራኪውን በብዙ ሺህ ትብታቦች አስረው የቁም ስቃዩን የሚያሳዩት አንድ ገፀባህሪ አሉ። አምበርብር ይባላሉ። በአባትም ሆነ በእናት ከሰው ልጅ የተወለዱ አይመስልም። ዋናውን አስማዲዮስ ቁጭ ነው። ለነገሩ የሰው ልጅ ከዲያብሎስ ተንኮልና ክፋት በላይም እንደሄደ እናውቃለን። አምበርብር ሥጋ የለበሰውን ዲያብሎስ ያስንቃሉ። አንደበታቸው ውስጥ ሀምሳ ሺህ እባብ ያለ ይመስለኛል። እንደዚህ ዓይነቱ ሰው በምድራችን ላይ ይኖራል ወይ ብዬ ለመገመት አልቸገርም፤ሞልቷል። ሁላችንም ወደዚያው እያመራን ይመስለኛል። አንበርብር የሁላችንም ወኪል ናቸው። ለነገሩ የወሪሳ ሰፈር ሰዎች ሁሉ ከሰውነት ክብር ወርደዋል። ሁሉም ደግሞ የኅብረተሰባችን ነፀብራቅ ናቸው። ገሀዱን እውነታ ነው በወሪሳ ህልም ውስጥ የምናየው።
ተራኪው የአማርኛ አስተማሪ የገባበት ውጥንቅጥ በጣም፣ እጅግ በጣም የሚያስፈራ ብቻ አይደለም። የሚሰቀጥጥና የሚዘገንን ነው። መጽሐፉን ሳነብ ከአስፈሪ ህልም ውስጥ ለመባነን እንደሚጓጉር ሰው ሆኜ ነው። እንደዚህ ስል በዕድሜ ገፋ ያልኩ ጎልማሳ እንደሆንኩ ልብ በሉ። ተራኪው ታምሟል፤ ይጓጉራል፤ ዛር እንደሰፈረበት ሰው መውጫ ቀዳዳ አጥቷል። ህመሙ የሁላችንም ህመም ነው። ተራኪው የታመመውን ህመም ሁላችንም ታምመናል። አምበርብር ተራኪውን እንደ ክፉ ዛር ተቆራኝተውታል። ተራኪው የገባበት ጣጣ በክፉ ዛር ተይዞ ባርያና አገልጋይ ከሆነ ሰው ጋር ይመሳሰልብኛል። የተራኪው ታላቅ ተስፋ የሚያንሰራራው አምበርብር ታመው ለሞት የተቃረቡ በመሰሉ ጊዜ ነው። ሰውዬው የበደሏቸውን ሰዎች እየጠሩ ይቅርታ ይጠይቃሉ። የይቅርታቸው መቋጫ ግን እርግማን ነው። ተበዳዩን መልሰው አጥፊና ተፀፃች ያደርጉታል። ይባስ ብለው ሊጠይቃቸው የተሰበሰበውን የጎረቤት ሰው ራእይ አየሁ ይሉታል። የእሪ በከንቱ ሰው አምበርብርን ታመው ባለመጠየቁ ምክንያት እግዚአብሔር እንዲህ ይላችኋል፤ “የእሪ በከንቱ ሰው ታምሜ ጠየቅኸኝ? ተርቤ አበላኸኝ? ታርዤ አለበስኸኝ? ይላል እግዚአብሔር” በዚህ ሳቢያ የሰፈሩ ሰው አምበርብርን ምግብ እየያዘ መጠየቅና መንከባከብ ይጀምራል። በሦስት ቀን ውስጥ እሰበሰባለሁ ያሉት ሰውም ዕድሜያቸው እየረዘመ ይሔዳል።
እኔ ህልም ነው ባልኩት የወሪሳ ልቦለድ ውስጥ ያሉት የአምበርብር ባህሪ በብዙ መልኩ ሊተረጎም የሚችል ነው። አምበርብር የአንድ በሽታ ትእምርት ናቸው። ይኼ በሽታ ክብራችንን የገፈፈ የትንሽነት፣ የአጭበርባሪነት፣ የተንኮል፣ የሤራ ነቀርሳ ነው። አምበርብር በሽታችን ናቸው። ጣጠኛው ተራኪ፣እንደዚሁም የወሪሳና የእሪበከንቱ ሰው አምበርብርን ሊገላገላቸው አልቻለም። ይባስ ብሎ እሳቸው ባጠፉት ጥፋተኛ፣ እሳቸው በበደሉት በደለኛ ሆነ። በኩነኔያቸውም ተኮነነ፤ ተፀፀተ። ከሞት ደጃፍ ነኝ ያሉትን ሰው (ይኸ ሌላው ተንኮላቸው ነው) እድሜ ሊቀጥልላቸው ይሮጥ ገባ።
ይኸ ቀድሞ የገባንበትና አሁን የምንዳክርበት ጣጣ ነው። ለዘመናት የነበሩንን ገዢዎች ጥፋትና ኀጢአት እኛው ተሸክመናል። ክፉ መሪ ሲነሳ አምላክ ስለ ጥፋታችን ያመጣብን ቅጣት ነው እንላለን። ስለ አረመኔ መሪዎቻችን እንማልዳለን፤ እንፀልያለን። የእግዚአብሔር ሥዩም ነኝ ካለ ለዲያቢሎስም እንሰግዳለን። መቼም ዲያብሎስማ፣ ዲያብሎስ ነኝ ብሎ አይመጣም።
ሶሻሊዝም የሚባል ሥርዓት አምጥተን መከራችንን በላን። አይ፣ ጥፋቱ የኛ ሆነ እንጂ “ሶሻሊዝም” የተባለ ሥርዓትማ እንከን አይወጣለትም ነበር ብለን ሙሾ ተቀመጥን። መንግሥቱ ኃይለማርያም “ጥሎን ጠፋ፤ ጥሎን ፈረጠጠ” ብለን እስከ አሁንም ድረስ የምናላዝን አለን። ሌሎችም፣ “ጥሏችሁ ጠፋ” እያሉ ሆድ ያስብሱናል። ኃይለሥላሴ ከሞቱ ፀሐይ ትጨልማለች፤ መንግሥቱ ሥልጣን ከለቀቀ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች እያልን ዘምረናል። ሰው እንዴት ከበሽታው መገላገልን ይፈራል? በሽታ ተውሳክ ነው፤ ተደራቢ ነው፤ ይበላናል። ቀስ በቀስም ያጠፋናል። ከበሽታ አምጪ ተውሳኮች ውስጥ ቫይረስና ባክቴሪያ የሚባሉ አሉ ሲባል እሰማለሁ። ታዲያ በሽታ አምጪ ለሆኑ (ሰላማዊዎችም አሉ ይባላል) ባክቴሪያዎችና ቫይረሶች የምናዝን ህዝቦች አይምሮአችን ጤነኛ ነው? ለሚያሳድዱኣቸው ጅቦች የሚፀልዩ አህዮች ጤነኞች ናቸው? ሙጀሌን መንግሎ ማውጣት እንጂ ማስታመም ያስፈልጋል? ለሙጀሌ ይፀለያል?
የዛሬ አስር ዓመት ገደማ የኤችአይቪ ምርመራ አድርገው ነፃ የተባሉ ሴት “ባይልልኝ ነው” ብለው እንዳዘኑ በቀልድ መልክ የተነገረ እውነተኛ ታሪክ ሰምቻለሁ። ይኸ ነገር የብዙዎቻችን አባዜ እንደሆነ እገምታለሁ። ለሌላው ከማዘን ተቸግረን እንዲታዘንልን የምንፈልግ ብዙ አለን። በዘመኑ ቋንቋ የተረጂነት መንፈስ የሚሉት ይኸ ሳይሆን አይቀርም። በእዚሁ በእኛ አገር ባህታዊያንና መናኞች ዓለምን የናቁ ናቸው። ገላቸውንና ልብሳቸውን አያጥቡም፤ ቅማልም አይገድሉም። ዓለምን ያልናቅን ደግሞ ሌሎች የቅማል ዓይነቶችን ነው ይዘን የምንዞር።ይኸ ነገር በሁሉም የሰው ልጅ ውስጥ ያለ የባህሪ እንከን ነው። ፈረንጅና ሀበሻ አይልም። በሥነልቦና ትንተና ውስጥ የስኬታማነት ፍርሀት የሚባል ነገር አለ። ስኬታማ መሆንን፣ ማሸነፍን፣ መበልፀግን የሚፈሩ ሰዎች አሉ። ፍርሀታቸው ከነሱ በላይ ያሉ ሰዎች እንዳይጠሏቸው ነው። እነዚህ ስኬታማ ከሆኑ የሌላ ባርያ መሆናቸው ያቆማል። የባርያ አሳዳሪዎችም ይታመማሉ። ነገሩ፣“ሞኝን ማን ይጠላዋል” ዓይነት ነው።
አንድ የዛሬ ሀያ አምስት ዓመት ገደማ ያነበብኩት መጽሐፍ አለ። “Flowers for Algernon” ይባላል። የሳይንስ ልቦለድ ነው። ዋናው ገፀባህሪ የአእምሮ ዕድገት ዝግመት አለበት። ተራኪው እሱ ራሱ ነው።  በአንድ ዳቦ ቤት ተላላኪ ሆኖ ይሠራ ነበር።  የሰውን ልጅ የአእምሮ ችሎታ በህክምና ከፍ ማድረግ ይቻላል ብለው የተነሱ ሳይንቲስቶች፣በተራኪው አእምሮ ላይ የቀዶ ጥገና ያደርጋሉ። የልጁ የአእምሮ ችሎታ ሰማይ ጥግ ይደርሳል። በዚያው ልክ ደግሞ ቁጡ ይሆናል። ብቸኛ ይሆናል። ልቦለዱ የዚህ ሰው የዕለት ማስታወሻዎቹ ስብስብ ነው። ታዲያ በአንደኛው የዕለት ማስታወሻው ላይ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን የሚመስል ሐሳብ ይጽፋል፤ “ድሮ “ሞሮን” እያለሁ ሰዎች ይወዱኝ ነበር። ዙሪያዬን ከበው ይስቃሉ። እኔም ደስተኛ ነበርኩ። አሁን ግን ብቻዬን ነኝ። ይከፋኛል። ሰው እንደ ድሮው አይወደኝም፤ አይጠጋኝም።”
እንግዲህ መወደድ የፈለገ ሰው ከሰውነት ተራ ይወጣል። ዝቅ ይላል። ትንሽ ይሆናል። ፍቅርና ሀዘኔታ አይጠገብም። ሱስ ይሆናል። ትንሽ ያደርጋል። ሁሌም ህፃን ሆኖ የመቅረትን አደጋ ይጋርጥብናል። ስንኩል ያደርገናል። ለማኝ እንሆናለን።
ኢትዮጵያ ክፋትና ክፉ ሰው አሸንፎ የሚኖርባት አገር ነች። ጀግና ነን እንላለን እንጂ እንደኛ ያለ ፈሪ ህዝብ የለም። ትንሽ ክፋትና ትንሽ ድፍረት ያለው ሁሉ ነው እያርበደበደ ሲገዛን የኖረው። ጀግና ብንሆንማ ሁላችንም እንነግሥ ነበር፤ ሁሉም ወንድ ንጉሥ፣ ሁሏም ሴት ደግሞ ንግሥት ትሆን ነበር። ጀግና ብንሆንማ መሪነት የሥራ ድርሻ ብቻ ይሆን ነበር። ጀግና ብንሆንማ መሪያችን ደመወዝ የምንከፍለው አገልጋይ ብቻ ይሆን ነበር። ጀግና ጠቢብም ነው፤እኛ ጥበብ የሚባል ነገርም አልነበረን። ክርስትናን ከማንም ቀድመን ተቀበልን እንላለን። ሁለት ሺህ ዓመት ግን ሰይጣን ነው በእግዚአብሔር ስም ሲገዛን የኖረው። ይህ ጥበብ ቢኖረን ኖሮ እንዲያ አይሆንም ነበር። አሜሪካ ጀግና ናችሁ ብትል ጠላትዋን እንድንወጋላት ነው። አምበርብርም መጣባቸው የተባለውን ባላንጣቸውን እንዲገድልላቸው ሲሉ ተራኪውን ያልሆነውን ጀግንነት ያላብሱታል። ፈረንጆች ጥበበኞች ናችሁ ቢሉን ሸቀጣቸውን ለመሸጥ ነው። ከተራበ ልጁ አፍ ቀምቶ ወተት የሚሸጥና መጫወቻ ቆርቆሮ የሚገዛ ህዝብ ሞኝና ተላላ እንጂ ጥበበኛና ጀግና አይደለም። ከባድ የሆነውን የምድር ወገብ የፀሐይ ግለት እንዲከላከልበት ተፈጥሮ የቸረችውን አፍሪካዊ ጥቁርነትና ከርዳዳ ፀጉሩን፣ የምድር ዋልታ ሰዎች የብርድ መከላከያ ወደሆነው ፈረንጃዊ ነጭና ለስላሳ ፀጉር የሚቀይርለት ቀለምና ቅባት ለመግዢያ ሲል መሬቱን፣ ክብሩንና ነፍሱን የሚሸጥ ህዝብ፤ጥበበኛና ጀግና አይደለም። እርስ በራሱ እየተፈጃጀ የፈረንጅ ታንክና ጠመንጃ የሚያሻሽጥና የሚሸምት፣በርሱም የሚፎክር ህዝብ ጥበበኛና ጀግና አይደለም። ነብር ሲያይ ፍየል፣ ጅብ ሲያይ አህያ፣ ፍየል ሲያይ ቅጠል፣ ድመት ሲያይ አይጥ፣ ተኩላ ሲያይ በግ፣ እሳት ሲያይ ገለባ የሚሆን ህዝብ ጥበበኛና ጀግና አይደለም። ዲሞክራሲን፣ ልማትንና ትምህርትን በልመና አገኛለሁ የሚል ህዝብ ጥበበኛና ጀግና አይደለም።
ይኸ ሸፍነንና ደብቀን የምናባብለው ቁስላችን ነው።  ይኸ ቁስል መገለጥ አለበት። መታጠብ አለበት። መታከም አለበት። መሻር አለበት። ቁስላችን በተነካ ቁጥር የምንጮህ ከሆነ ግን ምን ግዜም አንድንም። ምናልባት አንዱ ጀግንነታችን ቁስላችንን በነካውና በገለጠው ላይ ይመስለኛል። ለዚያ ጊዜ እንበረታለን። ውዳሴ ከንቱ ለሚመግበን ብቻ የምናጨበጭብ ተላላዎች ነን።
(ይቀጥላል)

Read 2235 times