Print this page
Monday, 24 August 2015 10:01

የማስታወቂያዎቻችን እንከኖች!

Written by  ከዳዊት አርዓያ- (www.facebook.com/Dawit.Ara)
Rate this item
(10 votes)

     ማስታወቂያ “ጥበብ ነው ወይንስ ሳይንስ?; የሚለው ክርክር ገና አሸናፊው ያልለየለት፣ ያልተቋጨ  ሙግት ነው፡፡ ሁለቱም ወገኖች የየራሳቸውን ማሳመኛ ለማቅረብ ይሞክራሉ፡፡ ጋዜጠኛ ዳንኤል ብርሃኑ ‹‹የማስታወቂያ መሰረታዊ ሃሳቦች›› በሚል መጽሀፉ ‹‹ማስታወቂያ ሳይንስ አይደለም፤ማሳመኛ ነው፤ማሳመን ደግሞ ጥበብ ነው›› ይላል - ዊልያም በርናባስን ጠቅሶ፡፡
እስቲ አፍታ ወስደን ጥቂት ለማሰላሰል እንሞክር። ያየናቸውን፣ የሰማናቸውን፣ያነበብናቸውን …ማስታወቂያዎች በህሊናችን እንመላልስ፡፡ በእርግጥ ጥበብን የተላበሱ ማስታወቂያዎች አሳማኝ ናቸውን? በምሳሌና በማስረጃ እየተነተንን ለመዳሰስ እንሞክር፡፡
የሚዲያውን ባህሪ ያልተረዱ ማስታወቂያዎች
1- በባለጥቁርና ነጭ ቀለም በታተመ ጋዜጣ፣ መጽሄት ወይም ሌላ የህትመት ውጤት ላይ ታትሞ ያየነውን ማስታወቂያ፣ ባለ ቀለም ህትመት ባላቸው ብሮሸሮች ወይም በከተማ መሀል በሚሰቀል ቢልቦርድ ማየት እጅግ የተለመደ ስህተት ነው፡፡
ቀለማት መልእክትን፣ ስሜትን ያስተላልፋሉ። ድባብን፣ ሁኔታን ይገልጻሉ፡፡ ብለን የምናምን ከሆነ፣ለተፈለገው ዓላማ የተዘጋጀ ማስታወቂያ ሊኖረን የግድ ነው፡፡ ለ ‘A4’ ወረቀት ተሰናድቶ ስናየው ማራኪና መልእክቱንም በተገቢው መንገድ ያስተላለፈ ማስታወቂያ፤ እጅግ ግዙፍ በሆነ ቢልቦርድ ላይ ሲቀመጥ ሳቢነቱን ሊያጣ ይችላል፡፡ በውስጡ ያሉት ምስሎች አለመጠን ይገዝፋሉ፡፡ በባለ ሙሉ ቀለም አምሮ የታየን ማስታወቂያም ጥቁርና ነጭ ቀለም ብቻ ሲሆን መልእክቱን ሙሉ ለሙሉ ሊያጣ የሚችልበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ለዚህም ጋዜጣና መጽሄት ላይ ወጥተው ለማንበብ አበሳችንን ያሳዩን ማስታወቂያዎችን ማስታወስ በቂ ነው፡፡ በአብዛኛው የሀገርኛ ፊልም ማስታወቂያዎች የዚህ ችግር ሰለባዎች ናቸው፡፡ ከታሰቡበት ቀለም ውጪ በመታተማቸው  ምክንያት ከዋናው ርዕስ በቀር አብዛኛው ጽሁፋቸው የማይነበብ፣ በጋዜጣና በመጽሄት የውስጥ ገፅ የታተሙ የፊልም ማስታወቂያዎች ቁጥር ጥቂት አይደለም፡፡
2- ለቴሌቪዥን አገልግሎት ተብለው የተሰሩ ማስታወቂያዎችን በቀጥታ ለሬዲዮ መጠቀም ሌላው ችግር ነው፡፡ ምስል እያገዘው ከእይታ ጋር ተዳምሮ የሚቀርብን መልእክት በድምጽ ብቻ ለሚተላለፍ ሚዲያ ስናመጣው የሚያጎድለው ነገር በርካታ ነው። በቴሊቪዥን የተላለፈን የመኪና ማስታወቂያ በሬዲዮ ሲለቁት አስተዋዋቂው፤‹‹አሁን ለዚህ 300ሺ ብር አያንሰውም?›› ሲለን ‹‹ለየቱ?›› ማለታችን ተፈጥሯዊ ነው። አላየነውማ! የምስልና ድምጽ ቅንብር ማስታወቂያው ሬዲዮ ላይ ሲመጣ ምንም ጉድለት አያመጣም ተብሎ የሚታሰብ ከሆነ ደግሞ ቀድሞውኑ ቴሌቪዥን ላይ መቅረብ አልነበረበትም ወደሚል ድምዳሜ ይወስዳል፡፡
ያልተገባ ንፅፅር
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ማስታወቂያ የሚታየው በቴሌቪዥን ነው፡፡ ኳስ በመጫወት ላይ ሳለ በዘግናኝ ሁኔታ ከጉልበቱ በታች ያለው አካሉ የሚሰበር የእግር ኳስ ተጫዋች ያሳየናል፡፡ ምስሉ በብዙዎች የሞባይል ስልክ ላይ የሚገኝና የተሰለቸ ነው፡፡ ጣቢያው በተለያየ የዕድሜ ደረጃ ያሉ ሰዎች የሚያዩት ከመሆኑ አንጻር እንዲተላለፍ መፈቀዱ አስገራሚ ነው፡፡ ያንን አጭር ግን ዘግናኝ ስብራት ተመልክተን ስናበቃ፣ ምን ነክቶት እንደሆነ በማይታወቅ ሁኔታ አንድ ብርጭቆ ሲሰበር ይታያል፡፡ ቀጥሎ ተራኪው በሚያስገመግም ድምጹ እንዲህ ይለናል፡-
‹‹ብርጭቆ ቢሰበር ይጣሉት፡፡ እግርዎ ቢሰበር ግን ወደኛ ይምጡ፡፡ እገሌ የአጥንት ህክምና ክሊኒክ››
ጉድ በሉ እንግዲህ ይሄንን መካሪ! እግሬ ቢሰበር እንደ ብርጭቆው ከቤት አውጥቼ እንዳልወረውረው ሰግቶ ወደሱ እንድመጣ ሲነግረኝ፤ ሆስፒታሉን እንድጠቀም ሲያግባባኝ፡፡ እግሩ ተሰብሮበት የጣለ ሰው አለ እንዴ? ምናልባት ይህ ባለሙያ ‹‹ስብርብር አለልሽ ጉልበቴ›› የሚለው የሸዋንዳኝ ዘፈን ላይ ብርጭቆ ‘’ከሽ’’ ሲል ያሰማን አቀናባሪ ይሆን እንዴ? ወይስ ዘፈኑን ሲሰማ ተጽእኖ አሳድሮበት ይሆን?
ግጥም በግድ
እነዚህ ዓይነቶቹ ማስታወቂያ ነጋሪዎች /አስነጋሪዎች አላልኩም/ ግጥም ይወዳሉ፡፡ ግን አይችሉም፡፡ መውደድና መቻል እንደሚለያይ ደግሞ አልተረዱም፡፡ ስለዚህ እንዲህ ይሉናል፡-
ቤኮ / ምርጥ ነው‘ኮ!
‹‹ነው›› የሚለውን ቃል ተከትላ የመጣችው ኮ፣ ጉሮሮን ከማዳለጧ በተጨማሪ እቃው ቤኮ መሆኑ ቀርቶ፣ ‹ቤቃ› ቢሆን፣ ‹በቃ› በሚለው ከመተካት አታመልጥም - ‹‹ምርጥ ነው በቃ!›› ትባል ነበር፡፡
በወንድና በሴት የባህል አልባሳቶች/ እምር ብሎ ከች!
ይኼኛውም በግድ በግጥም ለማስተዋወቅ ከመጓጓት የመጣ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለማስታወቂያ ባለሙያዎቻችን ሳይገጥሙ ማስተዋወቅ እንደሚቻል ጠቆም አድርገናቸው እንለፍ፡፡
የሙያዊ ቃላት ናዳ
ሙያዊ ቃላት በማዥጎድጎድ በቀዳሚነት የሚታወቁት የጥርስ ህክምና ክሊኒኮች ናቸው፡፡ ሁሉም ሊባል በሚችል ሁኔታ ‹ኦርቶዴንቲክ አፕሊያንስ›፣ ‹ማግዝለሪ አፕሊያንስ› እያሉ እንኳን እኛ እነሱም ባልገባቸው ነገር ያደርቁናል፡፡ እንግዲህ መልእክቱ የሚነገረው ለሁሉም ሰው ነው - ቀለም ለዘለቀውም ቀለም ላልዘለቀውም፡፡ ማስታወቂያውን ለመረዳት የግድ ‹‹ምን አለ?›› ‹‹ምን ማለቱ ነው?›› መባባል ያለብን አይመስለኝም፡፡ የማስታወቂያ ዓላማ ደግሞ ግራ ማጋባት አይደለምና፣ ኳስ በመሬት ቢያደርጉ ከኛ ይበልጥ እነርሱ ይጠቀማሉ፡፡
አልተገናኝቶ
በአልተገናኝቶ ቡድን ውስጥ የሚካተቱት የማስታወቂያ ዓይነቶች የሚያስተዋውቁትና የሚተዋወቀው ነገር የተምታታባቸው ናቸው፡፡ እንደ መግቢያ የሚጠቀሙበት ዓረፍተነገር ዋናውን ሀሳብ ከያዘው ዓረፍተነገር ጋር የማይግባቡ፣ ፈጽሞ የተፋለሱ ይሆናሉ፡፡ ወይም ምርቱ ጥሩ እንደሆነ የሚጠቅሱት ምሳሌ፣ ከነገሩ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አይኖረውም። በምሳሌ እንመልከተው፡-
ቴሌቪዥንን ለማስተዋወቅ በቴሌቪዥን የሚተላለፍ ማስታወቂያ ነው፡፡ የቴሌቪዥኑን ስም ካስተዋወቀን በኋላ ‹‹የእነ ነይማር ስፖንሰር›› ይለናል፡፡ ቴሌቪዥኑን እንድንገዛው የሚገፋን እነ ነይማርን ስፖንሰር ማድረጉን ተገን በማድረግ ነው፡፡ ለገዢው የሚጠቅመው ትክክለኛ መረጃ ግን  የቱ ነው? ዋስትና ያለው መሆኑ፣ ጥራቱ ፣ የተሰራበት ጥሬ እቃ ወ.ዘ.ተ ነው ወይስ እነ ነይማር . . .? የቴሌቪዥን አምራች ድርጅቱ ስፖንሰር የሚያደርጋቸውን ግለሰብና ቡድን መጥቀስ ከምርቱ ጥራት ጋር ምን ያገናኘዋል? ዋናው ተዋዋቂ ማነው?  ቴሌቪዥኑ? ክለቡ? ወይስ ተጫዋቹ? ግራ የሚያጋባ ማስታወቂያ እኮ ነው፡፡
የሚተዋወቀው ድርጅት የጥርስ ህክምና ክሊኒክ ነው፡፡ የማሽኖቹንና የህክምናውን አይነት ከዘረዘረ በኋላ፣ ለየት የሚያደርገን ነገር ብሎ…
‹‹ለየት የሚያደርገን ነገር የታካሚውን ታማሚ ጥርስ ቀርጸን በሲዲ መስጠታችን ነው›› ይላል፡፡
 አሁን ማን ይሙት የበሰበሰ ጥርሱን ለመመልከት የሚጓጓ የዋህ በዚህ ዘመን አለ? ከታካሚው የጥርስ ጤንነት ጋር በቀጥታ የሚገናኝበት መንገድስ በየት በኩል ነው? ወዳጅ ዘመድ ቤታችንን ሲጎበኝ፣‹‹ውይ የጥርሴን ሲዲ ሳላሳይህማ አትወጣም!›› ስንባባል አይታያችሁም?
 የተዛባ መረጃ የሚያስተላልፉ
አንዲት ጠና ያለች  ሴት ከህንጻ ስር ያለ በሚመስል ፓርኪንግ ጋ ወደቆመ መኪናዋ በመሄድ ላይ ሳለች ጥቂት ሰዎች መኪና ሲዘርፉ (ግምት ነው) ትመለከትና ሞባይሏን በማውጣት እንደ ሽጉጥ ደግና ‹‹ዞር በል! ወሮበላ ሁላ! እዘረጋሃለሁ›› በማለት አስፈራርታ ታባርራቸዋለች። በድንገት ሞባይሏ ሲጠራ ፈገግ ትላለች፡፡ (በሌላኛው የማስታወቂያው ዓይነት ሞባይሉ በአነስተኛ አጣና መሰል ቱቦ ብረት ይተካል) ወደ መኪናው ገብታ ስትረጋጋም ‹‹እንዴ? የሰው መኪና!›› ትላለች፡፡ ከዚያም ‹‹ግላኮማ በድንገት የዓይንን ብርሃን ይነጥቃል›› ይለናል፤ የማይታየው አስተዋዋቂ፡፡
ጥያቄ 1 - ግላኮማ በድንገት የዓይንን ብርሃን ይነጥቃል፡፡ ይነጥቃል ማለት ሙሉ ለሙሉ ከማየት ወደ አለማየት ያሸጋግራል ማለት ነው እንጂ ያልተከሰተን ነገር ያሳያል ማለት ነው?
ጥያቄ 2 - የማይታየውን ሳይሆን ትክክለኛውን ነገር ነው ያየችው ካልን ደግሞ የሰው መኪና ሲዘረፍ ዝም ማለት ነበረባት ማለት ነው? ያስብላል:: ዘራፊን በማባረሯ ከመደሰት ይልቅ የሰው መኪና በመሆኑ ደንግጣለችና፡፡
ጥያቄ 3 - ያየችው ነገር የማይታየውን ነው፤ ዓይኗ ነው ያሳሳታት----ካልን ደግሞ መኪናውን ማን ከፍቶላት ገባች ከሚለው ጥያቄ በተጨማሪ ይህ ታዲያ ‹‹ስኬዚዮፎሪንያ›› የተባለ ያልታየን ነገር እንደታየ፣ የሌሉ ድምጾችን፣ ምስሎችንና ንግግሮችን እንዳሉ አድርጎ የሚያሳይ የአዕምሮ ህመም እንጂ የዓይን ህመም ነው እንዴ? ያስብላል፡፡
የቃላት ድረታ
‹‹ምግብ ማብሰል ትችያለሽ?›› ብሎ የሚጀምር ማስታወቂያ ደግሞ አለላችሁ፡፡ የምግብ ማብሰል ውድድር የሚያካሂድ ፕሮግራም ማስታወቂያ ነው፡፡ የምስል ቅንብሩ ጥሩ ቢሆንም የአስተዋዋቂው ድርቅና ይገርማል፡፡ ‹‹ምግብ ማብሰል ትችያለሽ ? አንተስ ? ›› ካለ በኋላ፣ ‹‹የእውነት ግን ምግብ ማብሰል ትችላላችሁ?›› ብሎን እርፍ! መጀመሪያ የጠየቀን የውሸቱን ነበር ወይስ አላመነንም? ወይስ የአየር ሰዓት መሙያ ቃላት ቸግሮት ይሆን? ያስብላል፡፡
 በጥበቡ ላይ ያጠላው መጥፎ ጥላ
 ከጥቂት ዓመታት በፊት የነበሩ የአማርኛ ፊልሞች በሬስቶራንቶች ወይም ካፌና ባር ውስጥ በሚቀረፁበት ወቅት ካፌውን ወይም የቤቱን ስም የሚገልጽ ታፔላ ወይም ፖስተር በተዋናዮች አስታከው በማሳየት፣ ሳሳ ያለ ማስታወቂያ የመስራት አዝማሚያ አሳይተዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜዎቹ ‹‹ላምባ›› የተሰኘው ፊልም፣ አምባሳደር ልብስ ስፌትንና ወጋገን ባንክን የማስተዋወቅ ተግባሩን በስሱ አከናውኗል፡፡
እከሌ ሆቴል እንገናኝ፡፡ እንትን ባር፣ክለብ፣ካፌ እጠብቅሀለሁ፡፡ የሚሉት ደግሞ ደፈር ያሉት አስነጋሪዎችና ነጋሪዎች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ግን ምስጋና በሚለው የፊልሙ የመጨረሻ ክፍል ላይ በጽሁፍ ምስጋናቸውን በማስፈር ነው ቦታው የት እንደነበር የሚነግሩን፡፡ አሁን አሁን እየታዩ ያሉ ጅምሮች ግን አደገኝነታቸው የከፋ ይመስላል፡፡
 ‹‹ሞጋቾቹ›› የተሰኘው በ EBS የሚተላለፈው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ፤ ስፖንሰሩ የሆነውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለማስተዋወቅ ሲል ብቻ፣ የኤቲኤምና የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎቶችን የታሪኩ አካል ለማድረግ በእጅጉ ሲባዝን እናየዋለን፡፡ ‹‹በቃ ብር ካልያዝሽ በሞባይሌ ትራንስፈር አደርግልሻለሁ››፣‹‹እንዴ! አታውቂም እንዴ? በኤቲኤም ካርድ ተጠቅመሽ ዘመናዊ ሁኚ እንጂ›› እየተባባሉ ማስታወቂያ የተጫነውን ዲስኩር፣ ድራማ ነው ብለው ያቀርቡልናል፡፡
 ‹‹አዲናስ›› የተሰኘው ፊልምም፤‹‹እኔማ አብሮኝ ያረጀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ነው ምርጫዬ›› በማለት የስፖንሰራቸውን ስም፣ የቃለ ተውኔቱ አንድ አካል ሲያደርጉ  ታዝበናል፡፡ ምናልባት ስፖንሰር ባይደረጉ ኖሮ ወይም ስፖንሰር አድራጊ ድርጅቱ ሌላ ቢሆን ቃለ ተውኔቱም ይቀየር ነበር ማለት ነው?
ይበልጥ የሚያሳፍረው ደግሞ ‹‹ወርቅ በወርቅ›› የተሰኘው የሰራዊት ፍቅሬ ፊልም ላይ ያለው ነው፡፡ ከፊልሙ ጋር ግንኙነት የሌለው ማስታወቂያ ያለምንም መቆራረጥ የፊልሙ አንድ አካል ሆኖ ይተላለፋል። አንዱ ገፀባህሪ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲመለከት ያሳየንና በቴሌቪዥኑ ውስጥ የሚታየውን ማስታወቂያ እኛም አንድ ሳናስቀር እንኮመኩማለን፡፡ ከአንድም ሁለት ማስታወቂያ እንመለከታለን፡፡ ፊልሙን አቋርጦ ገብቶ ቢሆን ይቅርታ እንድናደርግለት እድል በሰጠን ነበር። የቀረበው ግን የታሪኩ አንድ አካል በመሆን ነው፡፡ አስቂኙ ነገር የፊልሙ ዋና ገጸባህሪ ሰራዊት፣ ሽማግሌውን አሰልጣኝ ሆኖ ሲተውን ይቆይና በሚተላለፈው የቲቪ ማስታወቂያ ደግሞ ወጣቱን የማስታወቂያ ባለሙያ በመሆን ይታያል፡፡ ይቺ ናት ንቀት አትሉም? ተመልካችን መናቅ!
ድርጊቱ ምናልባት ገንዘብ ለመሰብሰብ ይጠቅም ይሆናል፡፡ ምናልባት ተመልካችን ጉሮሮውን አንቆ ማስታወቂያውን ለማስተላለፍ ይጠቅም ይሆናል፡፡ አዝማሚያው ግን አደገኛ ነው፡፡
የኪነጥበብ ስራና የማስታወቂያ ድንበር ሊለይ ይገባል፡፡
 ስለምንም የማያወሩ ማስታወቂያዎች
አንዲት ሴት ጸሀይ እንዳቃጠላት፣ ሙቀት እንዳደከማት ሆና ስትጓዝ እናያለን፡፡ ከዚያም አንድ በቀጭኑ የሚፈስ ወንዝ ትመለከትና በደስታ ፊቷን አብርታ እየሮጠች ወደ ወንዙ ትሄዳለች፡፡ በምትሮጥበት ወቅት ልብሷን እያወላለቀች ነው፡፡ እዚያ ወራጅ ፏፏቴ ላይ ስትደርስ ትጠመቃለች (ትታጠባለች)፡፡ ይህንን ትእይንት ሲመለከት የነበረ ሰው ፈገግ ብሎ ያጨበጭባል፡፡ አለቀ። ብታምኑም ባታምኑም ማስታወቂያው ተጠናቀቀ። የባንክ ማስታወቂያ ነው፡፡ ስለምን ማውራት ፈልገው እንደቀረጹት፣ ምኑን ዳይሬክት እንዳደረጉት፣ ኤዲተሩ ምን እንደገባው ፈጣሪ ይወቅ፡፡ መልዕክቱ እንዲተላለፍለት የፈለገው ድርጅትና መልዕክቱን ያስተላለፈው ጣቢያ ምኑን እንደገመገሙትም ግራ ያጋባል፡፡
ትውፊትን የሚያበላሹ ማስታወቂያዎች
ከንግግር ይልቅ በዜማና በግጥም ተውቦ፣ በሙዚቃ መሳሪያ ታጅቦ የሚቀርብ ማስታወቂያ በታዳሚው ህሊና ውስጥ ዘለግ ላለ ጊዜ የመቆየት ዕድል እንዳለው ሁሉም ይስማማበታል፡፡ ነገር ግን የዚህ የማስታወቂያ ዘርፍ ዋና አላማ የድምጻዊውን ችሎታ፣ የቅንብሩን ጥበብ አሊያም የገጣሚውን የቅኔ ብቃት ማሳየት አይደለም። የብዙዎቹ ማስታወቂያዎች ችግርም ይኸው ነው፡፡ በአብዛኛው በድምጻዊው ችሎታ ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው፡፡ የግጥም ይዘታቸውም የቀለለ ከመሆን አልፎ የተቃለለ የሚሆንበት ጊዜ ይበዛል፡፡ ከሁሉም የሚብሰው ግን ‹‹የህዝብ›› በመባል የሚታወቁትን፤ ‹እከሌ› የተባለ ባለቤት ሊጠራላቸው የማይችልን፤ ባህላዊ ዜማዎች  እያነሱ በዘፈቀደ የመጠቀማቸው ነገር ነው፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት የወቅቱን ገነን ያለ ዘፈን ማንንም ሳያስፈቅዱ ወስደው የማስታወቂያ ማድመቂያ ያደርጉት ነበር፡፡ የስራው ባለቤቶች፤ አልበዛም እንዴ? ስራችንን ተጠቅማችኋልና ከጥቅማችሁ አካፍሉን ማለት ሲጀምሩ፣ትንሽ እየቀነሰ መጣ፡፡
አሁን አሁን እየተረባረቡባቸው የሚገኙት ትውፊታዊ የህዝብ ዜማዎችን ነው፡፡ ‹‹አሲና በል አሲና ገናዬ፣ አበባየሆሽ፣ ሆያዬ፣ አሸንዳ›› የመሳሰሉ በዓላት ማድመቂያ የባህል እሴቶች፣ በተለይ የቢራ ፋብሪካዎቹ የግል ንብረት እየሆኑ ከመጡ ጥቂት እንቁጣጣሾች አልፈዋል፡፡ የባህል ወታደር፣ የትውፊት ዘበኛ በሌላት ሀገር ይሄ የሚጠበቅ ቢሆንም እባካችሁ አትበርዙብን፤ እውነታን ከሸቀጥ አትቀይጡብን ብለን ልንለማመናቸው ግድ ይላል፡፡
ተደጋጋሚ ውሸት እውነት ይመስላልና ‹‹አበባየሆሽ›› የሚለውን የህዝብ ዜማ የሰማ ታዳጊ ህጻን፣ ‹‹ዜማው የጊዮርጊስ ቢራን ማስታወቂያ አይመስልም?›› ሳይለን በፊት ሁሉም ነገር ወደነበረበት ቢመለስ ደግ ይመስለኛል። ‹የህዝብ ነው› ማለት፣ ‹የሁላችንም ነው› ማለት ነው እንጂ፤‹የማንም አይደለም› ማለት አይደለም፡፡
ቀጥታ ትርጉም ማስታወቂያዎች
የተወሰኑ ምርቶች ለውጪው ማህበረሰብ አገልግሎት ታስበው ይዘጋጁና ተንቀሳቃሽ ምስላቸውና መልዕክታቸውን የሚያስተላልፉበት መንገድ እንዳለ ሆኖ ቋንቋቸው ብቻ በኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ሲቀርብ እናስተውላለን፡፡ ይህ መሆኑ ብቻውን ክፋት የለውም። አስቸጋሪው ነገር ከኛ ማንነት፣ አስተሳሰብና አኗኗር ጋር የሚሄዱና የማይሄዱ መሆኑን በጥሞና አስተውሎ መምረጡ ላይ ነው፡፡
የሞዴስ ማስታወቂያ ነው፡፡ የተሰራው በአፍሪካዊያን ነው፡፡ ለኛ የሚተላለፈው በትርጉም ነው፡፡ ተርጓሚዋ ሴት ናት፡፡ የምትተረጉመው በዜማና በግጥም የተባለውን ነው፡፡ ይሁን እንጂ እርስዋም አማርኛ አትችልም፡፡ በኮልታፋ አንደበቷ ነው የምትንተባተብብን፡፡ ‹‹ማዬት ዬሌም፣ ማዬት ዬሌም›› ትለናለች፡፡ ምን ጉድ ነው! ጭራሽ አማርኛም ከውጪ እናስመጣ እንዴ?
ተዓማኒ ያልሆኑ ማስታወቂያዎች
ግነት አንዱ የማስታወቂያ ባህርይ ነው፡፡ ታዳሚው ለነገሩ ጉጉት ኖሮት የተባለውን ያደርግ ዘንድ ያልበዛ ግነት እንደ ቅመም ጣል ይደረግበታል፡፡ ያለመታመን ጫፍ ላይ ያልደረሰ፣ ከመታመን ቅጥር ያልወጣ ሚዛናዊ ግነት ይቻላል፡፡ (ግነቱ ከበዛ ግን ኩሸት ይሆናል)  
የሳሙናን ማስታወቂያ ለመስራት ቤተሰቦቿን በፊሽካ ጠርታ እንደ ወታደር ካሰለፈች በኋላ አፍንጫዋን በመጠቀም የጥራት ደረጃ ፍተሻ የምታደርገውን እናት አይተን፣ ምን ነካቸው ያላልን ጥቂቶች ብንሆን ነው፡፡
እንዲህ እንዲህ እያልን ከሄድን ብዙም የሚተርፉ ማስታወቂያዎች ላገናኝ እንችላለን፡፡ አሁን ደግሞ  እንዲበዙልን ከምንሻቸው ማስታወቂያዎች አንዱን እናድንቅ፡-
የዚህ ማስታወቂያ ዓላማ ማሳየት ነው። የሚያሳየውን ደግሞ በትክክል አውቋል፡፡ ጫማ፡፡ የጫማ ማስታወቂያ ነው፡፡ መደርደሪያ ላይ ቁጭ ብሎ ያሳየናል፡፡ የወንድ እና የሴት፡፡ ሰዎች መጥተው ያነሱታል፡፡ ከዚያ ሲራመዱ እናያለን፡፡ የካሜራው ትኩረት ከጉልበት በታች ያለው አካል ላይ ብቻ ነው፡፡ በአስፋልት፣ በኮብልስቶን፣ በደረጃ----ይሄዱበታል፡፡ አሁን ተቀመጡ፤ ቢሮ ውስጥ ናቸው፡፡ ደግሞ መንገድ ላይ ሲሄዱ… ሴቷ ቆማ እየጠበቀችው ነው። አብረው መጓዝ ጀመሩ፡፡ ካፌ ተቀመጡ፤ የተመቻቸው ይመስላል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ‹ጠንካራ፣ ምቹ፣ አስተማማኝ› የሚል የሰው ንግግር አንሰማም፡፡ ማጀቢያ ሙዚቃ ብቻ! ሳር ላይ ናቸው። ጫማውን አውልቀው አስቀምጠውታል፡፡ ቀጥሎ እየደነሱ ነው፡፡ መለያያቸው ደረሰ፤ሴቷ እግሯን ከፍ አደረገች፤ እየሳመችው ነው መሰል፡፡ ማስታወቂያው ከማብቃቱ ጥቂት ሰከንዶች በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ድምጽ ይሰማል- ‹‹አንበሳ ጫማ›› በቃ! ምንም ግርግር የሌለው፤ ፋብሪካ ለፋብሪካ ያላንከራተተን፣ ቆነጃጅት ‹ሲያምር›፣ ‹ስወደው› ያላሉበት፣ ራሳቸውን ነው ወይስ ምርቱን ነው የሚያስተዋውቁት ያላስባለን፣ የሚሰራውን የሚያውቅ ሰው ያሰናዳው፤ማሳየት ያለበትን ነገር ጠንቅቆ ያሳየ የተሳካ ማስታወቂያ!
በመጨረሻም
ማስታወቂያ የድምር ችሎታዎች ውጤት እንጂ፤ የድምጽ ማማር ብቻ ወይም ቃላትን አሳክቶ መናገር የመቻል ብቻ ወይም በካሜራና ኤዲቲንግ የመራቀቅ ብቻ… ውጤት አይደለም!  አንድ ታዋቂ የሀገራችን የማስታወቂያ ባለሙያ ቆየት ባለ ቃለ መጠይቁ እንዲህ ብሎ ነበር፡- ‹‹ማስታወቂያዎቼን እንዲያዩልኝ የምፈልገው ቴሌቪዥናቸውን ከፍተው ብቻ ሳይሆን ከሸጡትም በኋላ ነው!›› ጥበባዊ ደረጃቸው ከፍ ሲል፣ የይድረስ ይድረስና ሁሉም አያምልጠኝ አይነት አሰራሮች ሲወገዱ… ይህንን ማድረግ ይቻላል፡፡ አሁን ግን ቢያንስ ሬዲዮናችንን ሳንዘጋው በፊት----ቴሌቪዥናችን ላይ አፍጥጠን ባለንበት ቅፅበት እንኳን የምናደምጣቸውና የምንመለከታቸው ማስታወቂያዎች እንዲበዙልን ይሁን፡፡

Read 4143 times