Monday, 24 August 2015 09:52

“…ነግረኸዋል?”

Written by  ተስፋዬ ድረስ -
Rate this item
(4 votes)

    ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ እኔና ባለቤቴ የገጣሚ ተፈሪ ዓለሙን የግጥም መጽሀፍና የግጥም ሲዲ ለመመረቅ በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ተገኝተናል፤ ከሌሎች በርካታ እንግዶች ጋር፡፡
ወደ ቀኜ ዞር ስል የማስታወቂያ ባለሙያውን ተስፋዬ ማሞን አየሁትና በአንገት ዝቅታ ሰላም አልኩት፡፡ እሱ ከወንበሩ ብድግ ብሎ በወንበሮቻችን መካከል ያለውን ሸለቆ ተሻግሮ በመምጣት ሁለታችንንም ጨብጦ ወደ ወንበሩ ተመለሰ፡፡ የተስፋዬ የሰላምታ ሙቀትና ትህትናው ደስ የሚያሰኝ ነበር፡፡
ወደ ባለቤቴ ዞሬ፤ “ተስፋዬ ደስ ይለኛል” አልኳት።
“ነግረኸዋል?” አለችኝ፤ በፍጥነት፡፡
“አልነገርኩትም” አልኳት፡፡
እኔና ባለቤቴ ይህን ተባብለን ስናበቃ ወደ ጀመርነው ጨዋታ መለስ አልን፡፡ ሆኖም፤ “ነግረኸዋል?” የሚለው ጥያቄ ዕረፍት ስለነሳኝ ከወንበሬ ተነሳሁና አንድ እርምጃ ተራምጄ ከጎኑ በመቆም፤ እሱ እንደተቀመጠ፤ “ተስፍሽ” አልኩት። “ባለቤቴ፤ በለጠችኝ፤” አስከትዬም ከእስዋ ጋር የተባባልነውን በሹክሹክታ ነገርኩትና ተሳስቀን፣ ስሜቴን ስለነገርኩትም አመስግኖኝ ወደ ወንበሬ ተመለስኩ፡፡
ከዚያ “ነግረኸዋል?” የሚለው ጥያቄ ራሱን በራሱ ማባዛት ጀመረ፡፡ “ነግረኻቸዋል?” ብሎ ይጠይቀኝ ጀመር ከውስጤ የሚሰማኝ ድምጽ፡፡ በሕይወት ዘመኔ እንደምወዳቸው፣ እንደማደንቃቸው ያልነገርኳቸው ሰዎች በአይኔ ላይ በሰልፍ ተመላለሱ፡፡ አንደኛው አቶ መንግሥቱ መኩሪያ ናቸው፡፡
ፍቀዱልኝና ስለኚህ ሰው ልንገራችሁ፡፡ አቶ መንግሥቱ የኛ ሰፈር ልጆች ሆያሆዬ ለመጫወት ወደ ቤታቸው በሄድን ቁጥር (ክብረመንግሥት)፣ አንድም አመት ሳያጎድሉብን፤ ከኪሳቸው መዘዝ አድርገው “አንድ ብር” የሚሰጡን ሰው ነበሩ፡፡ ይታያችሁ፤ በዚያን ጊዜ ትልቁ የቡሔ ስጦታ ቢበዛ ሀያ አምስት ሳንቲም ነበር፡፡
ሰውየው ብር ከመስጠታቸው በላይ ደስ ያሰኘን የነበረው ብሩን ከሰጡን በኋላ እንደ ሌሎቹ አባወራዎች ብዙ ጨፍሩልኝ የማይሉ ሰው መሆናቸው ነው፡፡ እርግጥ ነው፤ እሳቸው ብዙ እንድንጨፍር ባይጠብቁም፣ እኛ በአፋችን “ሆያ ሆዬ” ከማለት አልፈን፤ ሀርሞኒካ እየነፋን ቤታቸውን እናደምቅ ነበር። ቤታቸው ደግሞ ወለሉ ጣውላ በመሆኑ በዱላ ሲደቀደቅም ሆነ ሲጨፈርበት ጥሩ ያዳምቅ ነበር፡፡
አቶ መንግሥቱ የሆያሆዬ ጊዜ ተስፋችን ብቻ አልነበሩም፡፡ የሰፈር ልጆች ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ሌላ ከተማ ለመሄድ ጎረቤቶቻችንን እየዞርን ስንሰናበትም ሁለት ብር (በተማሪ) መዥረጥ አድርገው ያሽጉ (ን) የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ ችሮታና “ጎሽ”ታቸው ወደር አልነበረውም፡፡ “በዚያን ጊዜ ሁለት ብር ምን ይገዛ ነበር?” የምትሉ አንባቢያን ካላችሁ፣ ያ ገንዘብ አጭሬው ከጭብጥ የሚያልፍ አውራ ዶሮ (ቀይ፣ ወሠራ፣ ገብስማ … ነጠላ፣ ድምድም ራስ … በአይነት) ባለቤት ያደርጋችሁ ነበር እላችኋለሁ፡፡
አንዴ እሺ ብላችሁኛል፤ ከአቶ መንግሥቱ መኩሪያ ጋር ከተያያዙ የግል ትዝታዎቼ ትንሽ ልጨምርላችሁ።  ትልቅ ከሆንኩ፣ ስራ ከያዝኩ፤ ደሞዝተኛ ከሆንኩ፤ ወዲህ ሁሉ ወደ አገር ቤት ስሄድ አቶ መንግሥቱ ቢራ ይጋብዙኝ ነበር፡፡ በስሜት ከልጅነቴ ውስጥ ባለመውጣቴ ግን “እኔ ልክፈል” ማለት ያስፈራኝ ነበር።
ታዲያላችሁ፤ ከጥቂት አመታት በኋላ “ነፍስ አወቅሁ”ና አገር ቤት ስሄድ ለማድረግ ካቀድኳቸው ነገሮች መካከል አንደኛው፤ አቶ መንግሥቱ መኩሪያን በክብረመንግሥት ከተማ ውስጥ አለ ወደሚባል ሆቴል ወስዶ ራትና ቢራ መጋበዝ ሆነ - እና ደግሞ እኔም ሆንኩ የሠፈራችን ልጆች ሁሉ እንደምንወዳቸው፣ እንደምናከብራቸውና እንደምናደንቃቸው መንገር፡፡ እኚህ ሰው ድፍን አንድ ብር ከኪሳቸው አውጥተው፣ እጃቸውን ከአናታቸው በላይ ከፍ አድርገው ሲያሳዩን ይሰማን ስለነበረው ሀሴት፤ ምን ይሄ ብቻ? የእንጨት መሰንጠቂያ ፋብሪካ ሠራተኛ ቢሆኑም የልብሳቸው ፅዳትና ንፅህና ምን ያህል ይማርከን እንደነበር፤ እያሳሳቅኹ መንገርም ሆነ እቅዴ፡፡
ታዲያላችሁ፤ አንደበቴን ለምስጋናና ለሙገሳ አዘጋጅቼ፣ ኪሴን በብር አጭቄ ወደ አገር ቤት ስሄድ አቶ መንግሥቱ መኩሪያ በህይወት አልነበሩም፡፡ እኒያ ደግ ሰው በታመሙ ጊዜ እንዴት ሳልሰማ፣ ማለቴ እንዴት ሳይነገረኝ ቀረ? ብዬ አዘንኩ፡፡ ያው ባዳ ስለሆኑ ነው አይደል? የባዳ መርዶ በየሜዳው ነውና በሰማሁ ጊዜ እሪ ብዬ አለቀስኩ፤ ልቤ ተሰበረ፡፡ እነሆ፣ እስከዛሬ ድረስ ሳስታውሳቸው ስሜቴ ይደፈርሳል፡፡ ምክንያቴ ግልጽ ነው፤ “አልነገርኳቸውም፡፡”
ወደዚያው ወደ ብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ልመልሳችሁና ባለቤቴ የሰራች(ው)ኝን ሌላ ነገር ልንገራችሁ፡፡ ነገሩ ከተነሳሁበት ርዕስ ጋር በጥሩ ሁኔታ አብሮ የሚሄድ ነው፡፡
ዝግጅቱ አለቀና በክብር ወደ ተጋበዝንበት የቴአትር ቤቱ የኮክቴል አዳራሽ በመሄድ ላይ እያለን ባለቤቴ አርቲስት ሐረገወይን አሰፋን ከማየትዋ ተወርውራ አንገትዋ ላይ ተጠመጠመችባት፡፡ ሁለቱ እቅፍቅፍ ብለው ይሳሳሙ ጀመር፡፡ ከዚህ ቀደም የሚተዋወቁ ስለመሰለኝ የበኩሌን እንደማደንቃት (በተለይ፣ በተለይ በአንድ የሬዲዮ ትረካዋ ምን ያህል እንዳደነኩዋት) ነግሬያት ተለያየን፡፡
አለፍ እንዳልን “ትተዋወቃላችሁ ለካ!” አልኩዋት ባለቤቴን፡፡
“እንዲያውም፤ አንተዋወቅም!” አለችኝ፡፡
“እና …” አልኩዋት፤ መተቃቀፉ ከየት የመጣ ነው? ልላት ብዬ፡፡
“ላሳይህ ብዬ ነዋ!” አለችኝ፤ እየሳቀች፡፡
“ምኑን?” አልኩዋት፡፡
“የሚያደንቁትን ሰው እንዴት እንደሚነግሩት ነዋ” አለችኝ፡፡ እንዲህ እቅፍ አድርጎ ስሞ መንገርም አለ ማለትዋ ነው፡፡
የሚገርመው፣ ከዚህ ቀደም ከባለቤቴ ጋር በአንድ ዝግጅት ላይ ታድመን ሳለ አንዲት ታዋቂ አርቲስት ከአጠገብዋ ተቀምጣ ምንም ስላላለቻት “ምነዋ ዝም አልሻት?” ስላት “አላደንቃትም፡፡ የማላደንቀውን ሰው ደግሞ ‹አድናቂሽ ነኝ ብዬ› አልሸነግልም፤ ራሴንማ አላታልልም” ነበር ያለችኝ፡፡
ወደዚሁ ዝግጅት ለመጨረሻ ጊዜ መለስ ልበልና ሌላ ማድነቄን ስለነገርኩት ሰው ላጫውታችሁ። የእለቱ ዝግጅት ወሳኝ ሰው ጋዜጠኛ ደረጃ ሀይሌ ነበር፡፡ ምርጥ የመድረክ አስተዋዋቂ፣ ድሮና ዘንድሮን አያያዥ፣ አድንቆ አስደናቂ፣ የተረሱ እንቁዎቻችንን፤ ለምሳሌ (ታደሰ ሙሉነህን - በስም ካልጠራሁ እንዳይቀየመኝ ብዬ ነው) አስታውሶ አሞጋሽ ሆኖ ነው ያመሸው፡፡ የእለቱን “ሙሽራ” ተፈሪ ዓለሙን፣ እንዲሁም ሌሎች ሰዎችን በስም ሲጠራ የቤት ስራውን በሚገባ ሰርቶ እንደመጣ ምስክር አያሻውም። በድምጹ ብቻ ሳይሆን በሞቀ ስሜትም አዳራሹን ከዳር እስከ ዳር፣ ከጥግ እስከ ጥግ፣ ከወለል እስከ ጣሪያ የሞላ ሰው ነበር፤ ደረጀ፡፡
ደረጀ አያውቀኝም፡፡ የማውቀውና የማደንቀው እኔ ነኝ፡፡ ስልኩን ከየት ላገኝ እንደምችል ሳስብ ቆይቼ ለታገል ሠይፉ በሞባይሌ የጽሁፍ መልዕክት ልኬ፣ የስልክ ቁጥሩን እንዲልክልኝ ጠየኩት፡፡ ላከልኝ፡፡ አመሰግነዋለሁ፤ ታገል (ልንገርህ ብዬ ነው)!
በማግስቱ ለደረጀ ደወልኩለት፡፡ አላነሳም። ጥቂት የአድናቆት ቃላትን ጽፌና ማንነቴን ገልጬ ተልዕኮዬን አበቃሁ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ደረጃ ደወለ፡፡ በድምጹ ለየሁት፡፡ የ”ነግረኸዋል?”ን ታሪክ ነገርኩት፡፡ ተሳሳቅን፡፡ እሱም ብዙ “ያልነገራቸው” ሰዎች በሞት እንዳመለጡት አጫወተኝ፤ እንደሚቆጨውም ጭምር፡፡ ጎበዝ፤ እናንተስ? “ነግረኸዋል? የሚለው ጥያቄ ማንን አስታወሳችሁ? አለመንገር ትልቅ የህሊና ሸክም ነው (አለኝ መሰለኝ ደረጀ)፡፡

Read 2300 times