Monday, 24 August 2015 09:41

ጽጌረዳዋ ከደረቀች በኋላ፣ ጐርፍ የሆነ ዝናብ ምን ይበጅ?!

Written by 
Rate this item
(14 votes)

የአባ ባሕርይ መዝሙር /3/ በግጥም መልክ በግዕዝ ቋንቋ የፃፉት የሚከተለው ምሣሌ ይገኝበታል፡፡ እንዳመቸ አቅርበነዋል፡፡
በአንድ ዘመን እንዲህ ሆነ፡፡ አንድ ሰው በመንገድ እየሄደ ሳለ፣ በድንገት ከየት መጣ ሳይባል አንድ አውራሪስ ከተፍ አለበት፡፡ ሰውዬው እግሬ አውጪኝ ብሎ ፈፋውን ጉድባውን እየዘለለ፣ ጫካውን እያቋረጠ መጭ አለ፡፡ ፍርሃቱ የትየለሌ ሆነ፡፡ ነብሱን ሳያውቅ ሸሸ፡፡ በመጨረሻ ገደል ገጠመውና ወደ ገደሉ ሲወድቅ አንድ የዛፍ ቅርንጫፍ ፈፋውን ታኮ ተዘርግቶ ኖሮ፤ ያን ሲያይ ሰውዬው አፈፍ አድርጐ ተንጠለጠለበት፡፡ እዚያው ተንጠልጥሎም ሳለ፤ ከጐኑ በኩል አራት እባቦች እየተሳቡ ሲመጡ አየ፡፡ ይብስ ብሎም ከበታቹ አንድ ዘንዶ አየ፡፡ ያ ዘንዶ ሰውዬውን ለመዋጥ አፉን ከፍቶ ወደ እሱ እየተንጠራራ ይጠብቀዋል፡፡
ቀን ያመጣው አይቀሬ ነውና ሁለት ጥቁርና ነጭ አይጦች ደግሞ፤ ሰውዬው የተንጠለጠለበትን የዛፍ ቅርንጫፍ ተጐምዶ እንዲወድቅ እየገዘገዙ የበኩላቸውን እኩይ ተግባር እየፈፀሙ ይገኛሉ፡፡ እኒህንም አየ፡፡
በዚህ ሁሉ መሃል፣ ሰውዬው በፍርሃትና በጭንቀት ተውጦ እያለ፣ ከዚያ ዛፍ ቅርንጫፍ ላይ የሚንጠፈጠፍ የማር ወለላ አየ፡፡ ሰውዬው አፉን ከፈተና ማሩ ወደ አፉ ይፈስለት ዘንድ ጠበቀ፡፡ የማር ወለላው ጥቂት በጥቂት ፈሰሰለት፡፡
ከቶውንም በምን ዘዴና ብልሃት ላመልጣቸው እችላለሁ ያላቸውን ፍርሃቶች፤ ከባዶቹን የእባብ፣ የዘንዶና የአይጥ ፈተናዎች በምን መንገድ አልፋቸዋለሁ? የሚሉትን ጭንቀቶች፤ በወለላው ጣዕም ምክንያት ለጥቂት ጊዜ ሊረሳቸው ቻለ፡፡
                                                   *   *   *
የሰው ልጅ እጅግ አስከፊ በሆነ መከራና ጣጣ አረንቋ ውስጥ ወድቆ እንኳ አንዳች ፋታ የሚያገኝባትን ቅንጣት ቅፅበት ይፈልጋታል፡፡ በእሷም ረክቶ ህይወቱን የሚታደግባትን ተስፋ ይጠነስሳል፡፡ ገደል የከተተውን አውራሪስ መሸሹ እኩይ ዕጣው ነው! ሙሉ በሙሉ ገደል ገብቶ እንዳይንኮታኮት ያ ቅርንጫፍ ተዘርግቶ መጠበቁ ሰናይ ዕጣው ነው፡፡ ከዚህ ዙሪያ ደግሞ እባብና ዘንዶ አሰፍስፈው መንጠራራታቸው፣ ለሰውዬው የታዘዙ እኩይ ዕጣዎች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ጠብታዋ ወለላ ማርም የሰውዬው ሰናይ ዕጣ ናቸው! መከራዎቻችን የተስፋ ዕልባት አላቸው፡፡ በብዙ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ነጥብ ብርሃን የማየት ችሎታ መኖር መታደል ነው!
አያሌ ውጣ - ውረዶችን ባየንባት አገራችን፤
“ኧረ እናንተ ሰዎች ተውኝ እባካችሁ
እንኳን የመሶቡን የጄን ተውኩላችሁ”
…ስንል ኖረናል፡፡ ለማን ነው የምንተወው? ለምንድን ነው የምንተወው? እስከመቼስ የምንተወው? የሚሉትን ጥያቄዎች አላነሳንም፡፡ በዚህ ውስጥ መታሰብ ያለባቸውን ኃላፊነታችንን የመወጣትና መብታችንን የማስከበር ፍሬ - ጉዳዮች ምን ያህል አስበንባቸዋል? በምን ያህል ዕቅድና የረዥም መንገድ ትግበራስ ውጤታማ እንደምንሆን እርግጠኞች ነን? ማለት የአባት ነው፡፡
ተጨባጭ ችግሮቻችንን በተጨባጭ መንገድ መፍታት አለመቻል አንዱ ተጨባጭ ችግራችን ነው፡፡ በሀሳብ አንደጋገፍም፡፡ ሀሳብ ካቀረብን ስለችግር እንጂ ስለመፍትሄ አይደለም፡፡ ስለሆነም በችግራችን ላይ ሌላ ችግር ጨምረን ነው የምንለያየው፡፡
የኮሚቴ መብዛት ችግር አለ ተብሎ፣ ያን የሚፈታ ኮሚቴ እናቋቁም ብለው ተለያዩ እንደተባለው  ነው፡፡ አንዱ መሰረታዊ ዕጣችን ስለጊዜ ያለን አስተሳስብ ነው፡፡ ሊቀ-ጠበብት አክሊለ ብርሃን የደረሱትን ማህሌት ልብ እንበል፡-
“በሰላማ ጊዜ የረጋ ወተት
ተንጦ ተንጦ ቅቤው ወጣለት”
ጊዜ የወሰደ ሰው አንድ ቀን ቅቤው ይወጣለታል ነው ነገሩ፡፡ ጊዜን አርቀን ለማሰብ ግን የአዕምሮም የልቡናም አቅም የለንም፡፡ (ለምሳሌ የሃያ ዓመት ዕቅድ አይገባንም፡፡)
ከቀደምት ዘመናት ጀምሮ በአገራችን ብዙ አጋጣሚዎችን አጥተናል፡፡ በተለይ ቀለም የቀመሰው ክፍል ብዙ ዕድሎችን አጥቷል፡፡ አንድም አንፃር በማብዛት፣ አንድም ከሥርዓቱ ጋር አብሮ የመሥራት ባህል ስለሌለው፡፡
“አገራችን የዕድል ሳይሆን የታጡ - ዕድሎች አገር ናት” ይላል አንድ ፈላስፋ (A land of missed opportunities not of opportunities) የእኛም ምሁራን እንዲሁ ቢሉ እንዴት መልካም ነበር! ዶክተር ጌታቸው ኃይሌ ከፃፉት ውስጥ “ጌታ ዲነግዴ የሳምንት ገበያ ሲደርስ ከከብቶቻቸው አንዱን በሬ ለመሸጥ ገበያ ይወስዳሉ፡፡ ግን አንዳንድ ጊዜ ገበያ እስኪፈታ እዚያው ውለው በሬውን ሳይሸጡት ይቀሩና መልሰው ያመጡታል፡፡ አባቴ፤ “ጌታ ምነው በሬውን መለሱት? ገዢ አጡ እንዴ?” ሲላቸው፤ “የለም ልጄ ገዢስ ሞልቶ ነበር፤ ግን ስጠይቃቸው፤ በቀዬው ለበሬዬ የሚበቃ የመስኖ ሣር ያለው አንድም ሰው አላገኘሁም፡፡ ለእነሱ ሸጬ በሬዬን ረሀብ ላይ እንዳልጥለው ብዬ መልሼ አመጣሁት” ይሉታል… የሚል ይገኝበታል፡፡ ይህንንም በምግብ ራስን መቻል ከሚለው የዛሬ ትግላችን ጋር አዛምዶ ማየት ደግ ነው! በሬው ተሸጦ የሚበላው እንዳያጣ የሚታሰብበትም ዘመን ነበር - ያኔ፡፡
በተደጋጋሚ ከሚነሱት የምሁር አምባ ችግሮች ወሳኙ፤ “ጠባብነትና ትምህክተኝነት የምሁሩ አባዜዎች መሆናቸውን አለመርሳት ነው!” የሚለው ነው፡፡ በሁለቱም ፅንፍ የተቸከልን ብዙ ምሁራን አለን! አምላክ ደጉን ያምጣልን!!
አበሻ “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” ይለናል፡፡ ችግሮቻችን መፍትሄ ሳያገኙ ሰንብተው ካንሠር አከል (Cancerite) ከሆኑ በኋላ ብንጮህላቸው ከንቱ መባዘን ነው፡፡ “ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ” የተባለውን ማጤን ነው፡፡
አገር እንደ ፅጌረዳ አበባ ብንመስላት፤ “ፅጌረዳዋ ከደረቀች በኋላ፣ ጎርፍ የሆነ ዝናብ ምን ይበጅ?!” የሚለው ይገባናል፡፡ ቀድመን እንዘጋጅ!!

Read 4326 times