Saturday, 04 February 2012 12:12

ባርነትን ያህል ከባድ ቀምበር!

Written by  ስብሃት ገ/እግዚአብሄር
Rate this item
(0 votes)

“በንዴት መቃጠል መቃጠል፣ አሁንም መቃጠል!” ጓድ ሌኒን

የተከበራችሁ አንባብያን:-

“እግዚብሔር ያሳያችሁ፣ አምላክ ያመልክታችሁ!” ባርነት’ኮ ከባድ ብቻ አይደለም፣ እድሜ ልክ የማይወርድ ቁራኛ ነው፡፡ ኧረ ስሙ ከዚህም የባሰ ቀፋፊ ነው! ደግሞ’ኮ አያፍርም፣ ቁጥራቸው ብዙ የሆነ ማህበረሰቦች በተገኙበት ሁሉ ባርነት ታይቷል፡፡ ከሁሉ የገነነው የባርነት ታሪክ፣ አፍሪካንና ደቡብ ዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካን ይመለከታል፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ ደቡብ ክፍል ወደ ቆላ የሚያመዝን ሙቀታም፣ ጥጥ አምራች ነው፡ አገሬዎቹን Red Indians እያስገደዱ ጥጥ አምራች ባሪያዎች ሊያደርጉዋቸው ሞከሩ፡፡ ኢንዲያኖቹ ያልለመዱት ሙቀት ስለሆነባቸው፣ እየደከሙ እየሞቱ፣ ለባርያ አዛዡ ጌታ ኪሳራ የሚያስከትሉ ብቻ ሆኑ፡፡ ተውዋቸውና ወደ አፍሪካውያን ዞሩ፡፡

አፍሪካ (በተለይ Gold Coast, ማለት የዛሬዋ Burkina Faso, በጣም ሞቃት ስለሆነች፣ ባሪያዎች በአብዛኛውን ከዚያ እየተፈነገሉ በመርከብ ታጉረው እየተወሰዱ፣ ለደቡብ ዩ ኤስ ባለ ሀብቶች በሽያጭ ይቀርቡ ነበር፤ እንደ ከብት፡፡ ገበያ ውስጥ በግ ተራ እንዳለ ሁሉ፣ ባርያ ተራም አለ፡፡ እንዲዋለዱና ዘራቸው ለደቡቦቹ ዘላቂ ትውልድ እንዲያፈሩ ለረዥም ዘመናት! Gold Coast በፈንጋዮቹ ዘይቤ Slave Coast ነበረች፡፡

እዚህ ላይ እጅግ የሚያሳዝንና የሚያሳፍር የባርነት ገጽታ ይከሰታል፡፡ ፈንጋዩ ፈረንጅ አይደለም በአደን ባርያን የሚማርከው፡፡

የተፈንጋዩ ታማኝ የቅርብ ዘመድ ነው ውሸት ፈጥሮ “ላንተ (ቺ) ብቻ የማሳይህ (ሽ) የሚያስገርም ስፍራ አለ” ብሎ (ላ) ወስዶ (ዳ) ሸጦት ማንም ዘመድ ሳያውቅበት ተመልሶ ኑሮውን (እና ፍንገላውን) ይቀጥላል ወይም ትቀጥላለች፣ የሚቀጥለውን ምስኪን የዋህ ዘመድ ወይም ጓደኛ እስኪፈነግሉ ድረስ…እብደቱ እየባሰ ይሄዳል፡፡ በሀብትና ድህነት መካከል የሚታይ ርቀት ከማሳዘኑ ጋር “እኔም በነሱ ቦታ ብሆን እንደነዚህ ሳይቆረቁረኝ ወይም ሳያሳብደኝ ሊቀር እንዴት ይችላል?” እላለሁ ለራሴ (ግን ምናልባት እኔም ሳይታወቀኝ የነሱን ያህል ኢሰብአዊ የሆነ ህይወት እየኖርኩ ይሆናል፡፡ ማን ያውቃል? አይን’ኮ ወደ ውጪ ሌላውን ታያለች እንጂ፣ ወደመጣችበት ዞራ ራሷን አታይም፡፡ ግራ የሚያጋባ ነገር!)

ቀጥለን ስለ አሜሪካ ስንተርክ፣ ሌሎቹ የበለፀጉ አገሮችንም ይወክላል (Scandinavia ከሚባሉት የሰሜን አውሮፓ የምር ዴሞክራሲ እና የፍትህ አገሮች በስተቀር፡፡ ለማስታወስ ያህል፣ እነዚህ ናቸው በጥንት ዘመን ባለ ረዣዥም መርከቦቹ አገር ዘራፊ Vikings የነበሩት)

ለመነሻ ያህል፣ በቅርቡ በመገናኛ ብዙሀን እንደተነገረን፣ ፕሬዚዳንት ኦባማ ለሚቀጥለው ምርጫ እየተዘጋጁ ናቸው፡፡ ስለዚህ የተቃዋሚው ፓርቲ ሹማምንት እንዲህ እያሉት ነው፡፡

“ውረድ ይቅርብህ፡፡ ባገራችን ሁለተኛውን Recession (የኢኮኖሚ ውድቀት ያመጣብን ያንተ አመራር ነው፡፡ ዛሬ’ኮ ባገራችን አንድ መቶ ሃያ አምስት ሚሊዮን ሰዎች ምግብም መጠለያም አጥተው እየተንከራተቱ፣ ለነገ ሌሊት ማደሪያ ቦታ ልመና እንኳ የሚሄዱበት እያጡ ነው፡፡ (ቅድም ያነሳነው የፖለቲከኞች “የአዞ እንባ” እየፈሰሰ መሆኑ እንዲታየን፣ ይህን የኦባማን ሀጢአት የሚያወሩት ራሳቸው እያንዳንዳቸው ሚልየነሮች ናቸው፣ ቢልየኔር የሆኑም ይኖሩባቸዋል!)

…ዝርያችን እብደቱ ከዚህም እየባሱ መሄድ መብቱ የተጠበቀ ይመስላል፡፡ ለምሳሌ በአስራ ዘጠኝ መቶ ስድሳዎቹ (አመተ ምህረት) ውስጥ Astor የሚባለው ቤተሰብ ለብቻው የአሜሪካ ገንዘብ ሰማንያ በመቶው “ህጋዊ” ባለቤት ነበር!

ከአሜሪካ እርዳታ እንጠይቃለን፡፡ ምን ልትሰሩበት ነው? ይሉናል፡፡ ልክ ከመሰላቸው ብድሩ ይፈቀዳል፡ካልመሰላቸው ቀረብን! ይህ ማለት ለአገራችን የሚበጃትን እነሱ ናቸው የሚያውቁልን እንጂ እኛ አናውቅም፡፡ አንገታችንን አቀርቀረን ዝም ብለን መቃጠል መቃጠል፣ አሁንም መቃጠል!

ብድሩን ከአለም ባንክ ወይም ከIMF (International Monetary Fund) እንበል ሰላሳ ሚልዮን ዶላር ብንበደር፣ ጊዜውን ጠብቆ የምንከፍላቸው አርባ ሚልየን ይሆናል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ጭምቅ ሙጥጥ አድርገው ከበሉን በኋላ፣ በሚቀጥለው ብድር እንድንጠይቅ “እስከ ዛሬ የነበረባችሁን እዳ ሰርዘንላችኋል” ይሉናል፡፡

አሉ ደግሞ NGO (Non – Government Organizations) የሚባሉ ገባሬ ሰናይ ነን፣ እዚህ የመጣነው እኛ ትርፍ ሳንፈልግ እናንተን ለመርዳት ነው ይሉናል፡፡ CARE የሚባለው ካቶሊካዊ ድርጅት በዚህ ንፁህ አገልግሎት ሊጠቀስ ይገባል፡፡ ኬር ታጥቆ ስራውን ከጀመረ ወዲህ በክረምት ጭቃው፣ በበጋ አቧራው እግረኞችን ያሰቃይ የነበረው ቀረልን፡፡ እነዚህ ጉራንጉር ሰፈሮች ድንጋይ ተነጥፎባቸው፣ ሰው ማን እንደሰራቸው ሳያውቅ መንግስትን እያመሰገነ እንደ ልቡ ይራመዳል፡፡

ሌሎቹ ኤንጂኦዎች ግን ግለሰቦችንና የግል ድርጅቶችን ለበጐ ስራ ገንዘብ እንዲያዋጡ ያሳምኑዋቸዋል፡፡ በዚህ ዘዴ የሰበሰቡት ስጦታ የማይታመን ነው፣ Graham Hancock ባያጋልጣቸው ኖሮ፡፡ አሁንም እግዜር ያሳያችሁ አምላክ ያመልክታችሁ፣ ለሶማልያ ወንዶች ካቦርት እና ቦት ጫማ፣ ለሴቶቹ fashion የተከተለ ታኮ (high heel) ጫማ ላኩላቸው (አሁንም ፍርዱን ለአንባብያን እንተዋለን) ለሌሎች ድሀ አገሮችም እንደዚሁ!

ደግነቱ ፕሬዚዳንት መለስና ጓዶቹ ነቁባቸው፡፡ ጉዳያቸው እየተጣራ ካገር ተባረሩ፡፡

…ይህን ሁሉ ጉድ ከዘከዘክን በኋላ፣ ወደ አገራችን መለስ ብለን ብንመለከትስ? ከነሱ እንሻላለን ወይ? የሚል ጥያቄ ይመጣል፡፡ ለዚህ መልስ ፍለጋ ወደነ ጓድ ሊቀመንበርና ወደ አብዮቱ እንመለከታለን፡፡

የአብዮቱን ድሎች ለመመልከትና በኋላ በመገናኛ ብዙሀን ለሰፊው ህዝብ እንድንመሰክር፣ ከምባታና ሀድያ ወደሚባል አገር ተላክን፡፡

አብዮታውያኑ ያለፈውን Feudal ስርአት ለማንኳሰስና ለማንቋሸሽ ከባላባቶቹ የወረሱትን ጠበንጃና ሌላ መሳሪያ አስጐበኙን፡፡ ቤቱ ሲታቀድ መኝታ ቤት የነበረው ክፍል ውስጥ ተከማችቶ ስናየው እጅግ የሚያስፈራ ነበር፡፡

ባላባቶቹ ጭሰኞቻቸውን ስንትና ስንት በደል ያደርሱባቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ እንግዳ ቤት የነበረው ክፍል ውስጥ አንድ መሶብ አየን፣ የጭሰኛው ሚስት የሰፋችው፡፡ መሶቡ ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ፣ ምግብ ሊበሉበት እንዳልተሰራ ያስታውቃል፡፡ ቁመቱ ደግሞ ከኔ በአንድ ክንድ ይበልጣል፡፡ ለምን ተሰራ? ባላባትየው እንዲህ አይነት መሶብ ያሰራው ለእንግዳ ቤቱ ጌጥ እንዲሆን ይመስላል፡፡

የሰፋችው የጭሰኛ ሚስት ናት፡፡ ቤተሰብዋን ለመመገብ ጊዜ ከየት ታመጣለች? ጌታው ባላባት ደግሞ ካማረችው መጥታ አብራው እንድታድር ሊያስገድዳት ይችላል፡፡ በመጠኑ ደህና ሰው ከሆነ ባሏ ሳያውቅ ይሆናል፡፡

ከይሲ አይነት ከሆነ ግን ባልየው እንዲያውቅ ያደርጋል፡፡ ማን አለበት?

ብልጠታቸው ወንድ ልጃቸው አስተዳደጋቸው ላይ ይታያል፡፡ እኩያው ከሆነ ከጭሰኛ ልጅ ጋር ያታግሉታል፡፡ እና አውቆ እንዲወድቅለት ይታዘዛል፡፡

ትግሉ እልህ አስይዞት የጌቶችን ልጅ ከጣለው፣ ሀይለኛ ኩርኩም ያቀምሱታል፡፡ በዚህ ዘዴ የጭሰኛው ልጅ ካደገ በኋላ፣ የወንድ ወኔው ስለተኰላሸ ለጌታው ልጅ እድሜ ልኩን እንደታዘዘ ይኖራታል፡፡

Man’s inhumanity to man ይላሉ እንግሊዞች (ሰው በሰው ላይ የሚፈጽመው ኢሰብአዊ ድርጊት…)

ባርያዎቹ በመርከብ ውስጥ ተጨናንቀው ውቅያኖሱን ሲሻገሩ የደረሰባቸው ሞት፣ ዘግናኝ ከመሆኑ የተነሳ፣ እኔንም አንባቢዎቼንም ከማሰቃየት፣ ቢቀርብን ይመረጣል፡፡

 

ባርነት በኛ አገር

የእኛም አገር የባርነት ታሪክ አላት፡፡

ለምን አይኖራትም? ቆፍጣናው ቀብራራው ሸላዩ ፎካሪው ህዝባችን ከማን ያንሳልና ነው? ባይሆን ይበልጣል እንጂ!!

ለማንኛውም ባርያ ስትገዛው ጀምሮ ሰው አይደለም፣ የተፀውኦ ስም እንኳ የለውም፡፡ ወንድ ከሆነ ገብሬ ነው ፣ ሴት ከሆነች ወይ አመቴ ወይ እንኮዬ ናት፡፡

ባሪያዎቻችንን ከገበያ መርጠን ስንገዛ (ወይም ፈንጋይ አምጥቶ ሲሸጥልን፣ ግንኙነታችን እድሜ ይፍታህ ቁርኝት ነው፡፡ ክፉ ቀን ካልመጣብን በስተቀር አንለያይም፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ቋንጃቸውን በቢላዋ እንቆርጠዋለን፣ ሮጠው ጠፍተው እንዳያመልጡ!

የእናቴ አባት ባልና ሚስት ባርያዎች ነበሩባቸው፡፡ ሴት ልጅ ወለደችለት፣ ላቅመ ሄዋን ስትደርስ እሷን ሁለተኛ ሚስቱ አደረጋት፡፡ ባርነት እርግማን ነው፡፡ ሰው እንደነበርክና ይህን አሳፋሪ ነውር እንደማትፈጽም፣ “ክብር” የሚባል ፀጋ እንደነበረህ እንኳ ያስረሳሀል፡፡ በአማራው አገር የሆነ እንደሆነ፣ ሲጠሩህም በግጥም ነው (በስምህ አይደለም) ስትመልስላቸውም በግጥም ነው፡፡

“ሰጠኝ መርቆ!” ብለው ጮኸው ይጣራሉ

“ጉዳቴን አውቆ” ብለህ ጮክ ብለህ ትመልሳለህ፡፡ ምግብ በልተው ከጠገቡ በኋላ ይጠሩሀል “ገብሬ”

“አቤት ጌታዬ” ብለህ እያነከስክ ትገባለህ

እያየሀቸው በእጃቸው ሙሉ ትርፍራፊውን ይዘግናሉ፣ ሽቅብ ያፈጡብሃል፡፡ በርከክ ብለህ አፍህ የሚችለውን ያህል ጐርሰህ፣ የተረፈውን በሁለት መዳፍህ ተቀብለህ፣ እጅ ነስተህ ትወጣለህ፣ እያኘክህ እያነከስህ፡፡ እንዲህ ጠርተው የውርደት ጉርሻህን ካልሰጡህ “ጌቶችን በምን አስቀይሜያቸው ይሆን?” የሚል ቅሬታና ፍርሃት ያድርብሃል፡፡ ባርያቸው ሴት ብትሆንም ፍርሃትና ቅሬታ ያሳድሩባታል፡፡

 

 

Read 2942 times Last modified on Saturday, 04 February 2012 12:14