Saturday, 15 August 2015 15:56

ከአሜሪካ ተመልሰው ኢንቨስት ያደረጉ ሁለገብ ባለሀብት

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

በማኑፋከቸሪንግ፣ በሪል ኢስቴት፣ በመጠጥ ኢንዱስትሪ፣
በሆቴልና ሪዞርት፣ …. ተሰማርተዋል

   በርካታ ጐስቋሎች ደረታቸውን እየደቁ እምዬ! እያሉ በሚያሞካሿት፣ ብዙዎች በአፍሪካ ትልቁ የገበያ ማዕከል እያሉ በሚጠሯት መርካቶ በ1956 ዓ.ም ተወልደው አድገውባታል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኒው ኤራ፣ ሁለተኛ ደረጃ በያኔው ተፈሪ መኮንን በዛሬው እንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ት/ቤት ተማሩ፡፡
ደርግ፤ “አድሃሪ ነጋዴ፣ ሸቀጥ ደብቀሃል”…. በማለት ገደላቸው እንጂ አባታቸውም መርካቶ ውስጥ ታዋቂ ነጋዴ ነበሩ፡፡ አቶ ሙሉጌታ ተስፋኪሮስ በልጅነታቸው በንግድ ባይሰማሩም ከነጋዴ ቤተሰብ መወለዳቸው፣ በትልቁና በዋናው የንግድ ማዕከል ማደጋቸውና ዛሬ በንግድ (ቢዝነስ) የደረሱበት ደረጃ ሲታይ ንግድ ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉበት ነው ብንል የሚበዛባቸው አይመስለኝም፡፡
የአቶ ሙሉጌታ አባት አቶ ተስፋኪሮስ፤ የቤተሰቡ ኃላፊና አስተዳዳሪ ነበሩ፡፡ እሳቸው ከተገደሉ በኋላ የቤተሰቡ ሁኔታ ጥሩ አልነበረም፡፡ ወቅቱ በኢሕአፓ ሰበብ ወጣት ሁሉ የሚታፈስበት፣ የሚታሰርበት፣ የሚገረፍበት የሚሰቃይበትና የሚገደልበት…ስለነበር እዚህ ሆኖ ለአደጋ ከመጋለጥ ለመሰደድ ወሰኑ። አንድ ወር በእግር ተጉዘውና ድንበር አቋርጠው ሱዳን ደረሱና በ1975 ዓ.ም አሜሪካ ገቡ፡፡
በአሜሪካ የመጀመሪያ እቅዳቸው ትምህርት ነበር፡፡ ነገር ግን እዚያ፣ የሚረዳህ ከሌለህ  ለኮሌጅ የሚጠየቀው ክፍያ ነዋሪዎቹ ከሚከፍሉት እጥፍ ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ስደተኛ አሜሪካ ሲገባ ለቀለብ፣ ለቤት ኪራይ፣ ለትራንስፖርት፣ ለኮሌጅ ክፍያ… መሥራት አለበት፡፡ አንድ ብቻ ሳይሆን ቢያንስ ሁለት ቦታ መሥራት ግዴታ ነው፡፡ አቶ ሙሉጌታ የተለያዩ ሥራዎች እየሠሩ ቆይተው ነው በሁለተኛው ዓመት ኮሌጅ የገቡት፡፡
የተገኘው ሁሉ አሸሸ ገዳሜ ከተባለበትና ከባከነ በአሜሪካ ሰው አይኮንም፡፡ እየተቸገሩም ቢሆን መቆጠብ የግድ ነው፡፡ እየቆጠቡ ቆይተው ጥሪት ከቋጠሩ በኋላ አሁን የራሴን ቢዝነስ ብጀርምስ? አሉ። የሚሠሩትን ነገር ማጥናት ጀመሩና የግል ክሊኒንግ ሰርቪስ ቢዝነስ ጀመሩ፡፡ ትልልቅ ድርጅቶችን ኮንትራት ወስደው የጽዳት አገልግሎት ይሰጡ ጀመር፡፡ በአንድ ወቅት የዓመት 70 እና 80ሺህ ዶላር የፅዳት ኮንትራት ነበራቸው፡፡
አገራቸው ገብተው መሥራት የሚያስችላቸው ሀብት ከቋጠሩ በኋላ በአገራቸው ልማት ለመሳተፍ ፈለጉ፡፡ ለምን ያለችኝን ይዤ አገሬ ገብቼ እንደ አቅሜ ኢንቨስት አላደርግም? ጥቂትም ቢሆኑ ለአገሬ ዜጐች የሥራ ዕድል ፈጥሬ፣ አገሬን ከድህነት ማጥ ለማውጣት በሚደረገው ጥረት የበኩሌን ሚና መጫወት አለብኝ አሉ፡፡ አሜሪካን ከመልቀቃቸው በፊት ሦስት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ተመላልሰው አገሪቷ ያለችበትን ሁኔታ አይተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ሁሉም ነገር የተመቻቸና የተደላደለ ባይሆንም በአገሪቷ ሰላም ስለሰፈነ መሥራት ይቻላል ብለው አሰቡ፡፡
የአገራችንን ችግሮች እኛው ዜጐቿ ተጋፍጠን ካላሻሻልናቸው የውጭ ዜጋ መጥቶ አያሻሽልልንም። ሁላችንም በጋራ በችግሮቹ እየተፈተንን፣ እየተማማርንና እየተማከርን ካልሆነ ችግሮቹ ምን ጊዜ አይቀረፉም፣ አይወገዱም፡፡ ሁሉም ነገር ይሟላ ብለን ከጠበቅን የአገራችን ለውጥና ዕድገት ረዥም ጊዜ ይፈጃል በማለት ንብረታቸውን ሸከፉ፡፡ ጊዜ ሳያባክኑ 13 ዓመት ከኖሩባት አሜሪካ የዛሬ 18 ዓመት በ1989 ዓ.ም ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡
አቶ ሙሉጌታ ወደ አገራቸው እንደተመለሱ የጀመሩት ቢዝነስ ከአሜሪካ ወረቀት ማስመጣት ነበር፡፡ ነገር ግን አሰራሩን ስላላወቁ እንዳሰቡት አልሆነም - አከሰራቸው፡፡ እሱን ትተው ወደ ማኑፋክቸሪንግ መግባት ፈለጉ፡፡ መሳሪያውን ከቻይና በ2 ሚሊዮን ብር ያህል ገዝተው በአዲስ አበባ የዱቄት ፋብሪካ ተከሉ፡፡ ጥናት ሳያካሂዱ፣ መብራትና ገበያ በሌለበት አካባቢ ስለተከሉ ይኼኛውም እንደ በፊቱ አልተሳካም፤ አከሰራቸው፡፡
ኢንቨስተሩ ተስፋ ቆርጠው ወደ ለመድኳት አሜሪካ ልመለስ አላሉም፡፡ ይልቁንስ በቢዝነስ ዓለም ማግኘትና ማጣት፣ ማትረፍና መክሰር ያለ ነው፡፡ ዛሬ ባጣ ነጋ አገኛለሁ፡፡ እዚሁ በአገሬ ከወገኖቼ ጋር ወድቄ እየተነሳሁ፣ ብሠራ ይሻላል ብለው ትናንሽ ቢዝነሶች መሥራት ቀጠሉ። እንዳሰቡትም ትናንሾቹ ቢዝነሶች አላሳፈሯቸውም - ጥሩ ሆኑ፡፡
ትናንሾቹን ቢዝነሶች እየሠሩ ሳለ ሁለት ፕሮፌሽናል ሸሪኮች አግኝተው አካካሰ ሎጀስቲክስ ኃ.የተ.የግ.ማ መሠረቱ፡፡ ድርጅቱ ከጅቡቲ ወደብ ዕቃ ጭኖ በማጓጓዝ አዲስ አበባ ካደረሰ በኋላ አስፈላጊ የጉምሩክ ፎርሟሊቲዎችን አጠናቆ፣ ዕቃውን ለባለንብረቱ ያስረክባል፡፡ ሥራው ውጤታማ ሆኖ በፊት የከሰሩትን በዚህኛው መለሱ። ድርጅቱ አሁንም ጥሩ እየሠራ ነው፡፡ በመቀጠልም ሦስቱ ሸሪኮች በአፋር ክልል ጨው ማምረት ተሰማርተው በጋራ እየሠሩ ነው፡፡ ሸሪኮቻቸው በየግላቸው ኩባንያዎች ከፍተው ማሰራት ሲጀምሩ አቶ ሙሉጌታም የግል ኩባንያዎች አቋቁመው በማኑፋክቸሪንግ፤ በሪል እስቴት፤ እየሠሩ ነው፡፡
በለገጣፎ የተተከለው ሁለተኛው የዱቄት ፋብሪካ በቀን 850 ኩንታል ይፈጫል፡፡ ከዚያም በሽሬ፣ በአድዋ፣ በመቀጠልም 60 ዓመት ያስቆጠረ የዱቄት ፋብሪካ ኩሃ በአዳማ ከተማ ብዙ  ዓመት ያስቆጠረውን የረር ዱቄት ፋብሪካ ባንክ ጨረታ አውጥቶ ገዙ፡፡ በአጠቃላይ በዱቄት ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አምስት የዱቄት ፋብሪካ አላቸው፡፡ ወደ አግሮ ፕሮሰሲንግ በመግባት በአዳማ ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ብስኩትና የአልሚ ምግቦች ፋብሪካ ለማቋቋም አቅደዋል፡፡ የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ የሚያስተዳድራቸውን የመንግሥት ንብረቶች ወደ ግል ይዞታ ለማዞር ጨረታ ሲያወጣ በመጀመሪያ የዱቄት ፋብሪካዎቹን ተጫርተው ገዙ፡፡ ከዚያም የቤቶች ሥራ ድርጅትን (ሃውስ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ) በጨረታ በ51 ሚሊዮን ብር ገዙ፡፡ ኤጀንሲው የአዋሽ ወይን ጠጅ ፋብሪካንም ለመሸጥ ጨረታ አወጣ፡፡ መጀመሪያ የወጣው ጨረታ እርሻውን አያካትትም ነበር። ስለፋብሪካው ጥናት አካሄዱና ፕሮፖዛል አዘጋጅተው በ200 ሚሊዮን ልግዛው በማለት አስገቡ፡፡ ኤጀንሲው ያቀረቡትን ዋጋ ሳይቀበል ቀረ፡፡ ያቀረቡትን ጥናት መሠረት አድርጐ ከላይኛው አዋሽ 500 ሄክታር እርሻ ጨምሮ በድጋሚ ጨረታ አወጣ፡፡
እርሻውን ጨምሮ ለጨረታ የቀረበው ዋጋ አቶ ሙሉጌታ ብቻቸውን የሚሞክሩት አልነበረም። ስለዚህ አብሯቸው የሚሰራ የውጭ ኩባንያ ሲፈላልጉ፣ የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆነው ሰር ቦብ ጊልዶፍ በቦርድ ሊቀመንበርነት ከሚመራው “8 ማይልስ” ከተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ ጋር በሽርክና በ453 ሚሊዮን ብር አዋሽ ወይን ጠጅ ፋብሪካን ገዙ፡፡ በወቅቱ የአቶ ሙሉጌታ ድርሻ 49 በመቶ፣ የ“8 ማይልስ” 51 በመቶ ነበር፡፡
አዋሽ ወይን ጠጅ የ60 ዓመት አንጋፋ ፋብሪካ ነው። እድሳት ሳይደረግለት ቢቆይም፤ 600 ሠራተኞቹና የፋብሪካው ደንበኞች ለወይን ጠጁ ያላቸው ፍቅርና ታማኝነት ከፍተኛ ነው፡፡ በእርግጥም የገዛነው እሱን ነው ማለት ይቻላል ይላሉ አቶ ሙሉጌታ፡፡ ፋብሪካውን ከገዙት በኋላ ከሠራተኞቹ ጋር ብዙ ተወያይተው መሻሻል የሚገባቸውን ነገሮች ነቅሰው አውጥተው፣ የሚሰባበሩና በጊዜ የማይቀርቡ ዕቃዎችን ለማቅረብ፣ የተሰበሩ ወይም የሚለወጡ መሳሪያዎችን ለመለወጥ፣ እርሻው የተሻለ ምርት እንዲሰጥ በማድረግ 600 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት አድርገውበት፣ በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የተመረተው ወይን ጠጅ ሁሉ ይሸጣል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሁለተኛ ፋብሪካ ካስቴል ወይን ጠጅ ሥራ ጀምሯል፡፡ እኛም በገበያው ውስጥ ተወዳዳሪ ሆነን ለመቆየት አራት የወይን ዓይነቶች “ገበታ” በማለት ሁለት ቀይና ሁለት ነጭ ወይን ጠጆች አቅርበናል፣ ደንበኞቻችንም ወደዋቸዋል፣ ገበያቸውም በጣም ጥሩ ነው፡፡ በአገራችን 2ኛ የወይን ጠጅ ፋብሪካ በመከፈቱ በጣም ደስ ይለናል እንጂ አይከፋንም፡፡ ምክንያቱም ካስቴል ወይን ጠጅ በዓለም በ2ኛ ደረጃ የሚገኝ ነው። የኢትዮጵያን ወይን በዓለም ባስተዋወቀ ቁጥር ለእኛ በጣም ጥሩ ዕድል ይፈጥርልናል፡፡ ገበያው እንደሆን ለሁለታችን ቀርቶ ሌላም ቢመጣ ያስተናግዳል። በፊት ወይን ጠጅ ወደ ውጭ አገር ይላክ ነበር፡፡ አሁን ወደ ውጭ መላኩን አቁመን የጥራት ደረጃውን ከፍተኛና አስተማማኝ ደረጃ ለማድረስ እየሠራን ነው ሲሉ አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡
አቶ ሙሉጌታ በ200 ሚሊዮን ብር ካፒታል የጀመሩት ሌላው ትልቅ ፕሮጀክት ሙለር ሪል እስቴት ነው፡፡ ከመንግሥት የተሰጣቸው ቦታ ቢኖርም በአንዳንድ ያልተሟሉ ነገሮች እስካሁን መሬቱን አልተረከቡም። በቅርቡ እንረከባለን ብለዋል፡፡ ሙለር ሪል እስቴት እስካሁን ቦታ እየገዛ ነው ቤቶች የሚገነባው፡፡
በለቡ ቀለበት መንገድ ዳር ፣ በሳህሊተማርያም፣ በአያት አካባቢ እንዲሁም ሮፓክ የተባለውን የደቡብ አፍሪካ ኩባንያ ድርሻ በመግዛት፣ ለደንበኞቹ ቪላና አፓርትመንት እየሠራ ነው፡፡ ሪል እስቴት በኢትዮጵያ ረዥም ዕድሜ ስለሌለው ብዙ ችግሮች አሉበት፡፡ ግማሾቹ ከከተማ ወጣ ብለው ስለተሠሩ መሠረተ ልማት አልተሟላላቸውም፡፡ አንዳንዶቹ እስካሁንም መብራት፣ መንገድ፣ ውሃ የላቸውም፡፡ የግንባታ ማቴሪያሎች ዋጋ መናር፣ የሠራተኛ ጉልበት ዋጋ መጨመር፤ ሌሎች ችግሮችንም ተቋቁመው እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሪል እስቴት ሌላው ከፍተኛ ችግር ትልቅ ካፒታል መጠየቁ ነው፡፡ ይህን ችግር እየተወጡ ያለው ከቤት ገዢ ደንበኞች ቅድሚያ ክፍያ በመቀበልና ከራስ ኪስ በማውጣት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በጥቂት ሪል እስቴት አልሚ ድርጅቶችና በደንበኞቻቸው መካከል የሚፈጠር ያለመግባባት (ያለመተማመን) ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የቤት ሽያጭ ገበያ በጣም ተዳክሞ ቆይቷል፡፡
ሁሉንም ደንበኛ ማስደሰት ከባድ እንደሆነ አቶ ሙሉጌታ ያምናሉ፡፡ በሙለር ሪል እስቴት ወደ ፀብ ወይም ወደ አለመግባባት የደረሰ ደንበኛ እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ ያሉትን ችግሮች ከደንበኞቻቸውን ጋር ተወያይተን በመፍታት፣ የቤቶቹ ግንባታ እንደቀጠለ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከአቅም በላይ በሆኑ ችግሮች የተነሳ መዘግየት ይኖራል፡፡ የችግሮቹን ምክንያት ለደንበኞቻችን በማስረዳትና በመግባባት እየሠራን ነው ብለዋል አቶ ሙሉጌታ፡፡
ወደፊት በቤት ገዢና ሻጭ መካከል ችግር እንዳይፈጠር፣ ኩባንያዎች ቤት የሚሰሩበትን ቦታ ማሳየት፣ የተሰጣቸውን የቦታ ካርታ ማቅረብ፣ … ይኖርባቸዋል። ከገዡዎችም ብዙ ይጠበቃል፡፡ ቤት ሰሪ ነኝ ላለ ሁሉ ገንዘባቸውን አንስተው መስጠት የለባቸውም፡፡ ቤቴን የምትሰራበትን ቦታ አሳየኝ፤ ካርታው የት አለ? … በማለት መጠየቅና ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ የኩባንያውን ቀደም ያለ ታሪክ ማወቅም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ጥንቃቁ ከተደረገ በኋላ ችግር ከተፈጠረ መንግሥት በሚያወጣው ህገ ደንብና መመሪያ መጠየቅ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
ሪል ኢስቴት አትራፊ አይደለም፡፡ አትራፊ ያለመሆኑን ለማወቅ እኛ ቤት ሠርተን የምንሸጥበትን ዋጋና ሰዎች ባዶ ቦታ የሚጫወረቱበትን ዋጋ ማየት ነው፡፡ እኛ ሙሉ ለሙሉ ቤቱን ጨርሰን ከምናስረክብበት ዋጋ እጥፍ ነው ለባዶ ቦታ በጨረታ የሚቀርበው፡፡ ይህ እኛ በቤቱ ላይ ሲሚንቶ፣ ብረት፣ ፊኒሽንግ ማቴሪያል ከውጭ አገር አምጥተን ገጥመን… ሙሉ በሙሉ ጨርሰን የምንሸጥበት ዋጋ ከባዶ ቦታ ዋጋ ያነሰ ነው፡፡ የህም ትርፋችን በጣም አነስተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ መዘግየት ቢኖርም በመጨረሻ ግን ተጠቃሚዎች ገዢዎቹ ናቸው፡፡ ምክንያቱም እኛ ጨርሰን ካስረከብናቸው በኋላ ሦስት እና አራት እጥፍ ጨምረው ነው የሚሸጡት፡፡ አያት አካባቢ ለመኖሪያ አንድ ካሬ ሜትር ባዶ ቦታ በ20ሺህ ብር እየተሸጠ እኔ ተገንብቶ ሁለመናው ያለቀለትን ቤት አንድ ካሬ በ16ሺህ ብር ነው የምሸጠው፡፡ ስለዚህ ትርፋችን በጣም ትንሽ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
ሙለር ሪል ኢስቴት በ500 ካ.ሜ ላይ ያረፉ 12 ትላልቅ ጂ + 1 ቪላ ቤቶች አጠናቆ ለደንበኞቹ አስረክቧል። በ3 ሚሊዮን ብር የሸጡት ቤት ባለቤቶቹ 12 እና 13 ሚሊዮን ብር ለመሸጥ እያስማሙ ነው፡፡ ለቡ ቀለበት መንገድ ዳር የተሠሩ የነበሩ ቤቶች በ3 ሺህ በ4ሺህ ዶላር እየተከራዩ ስለሆነ ደንበኞችቻችን ደስተኞች ናቸው። ሳህልተማርያም አካባቢ 45 ቪላዎች ጀምረን 28ቱ አልቀው ደንበኞች ካርታቸውን እየተረከቡ ወደቤታቸው እየገቡ ነው። በአያት አካባቢ 24 ቪላዎች እየተሰሩ ሲሆን 50 በመቶ ተጠናቀዋል፡፡ በሌሎች ሳይቶች እየተሰሩ ያሉት ቤቶች በተለያየ ደረጃ ላይ ይገኛሉ በማለት አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡
በመኸል ከተማም ለሞል፣ ለገበያ ማዕከል ለቢሮ የሚሆኑ ህንፃዎች የመስራች እቅድ አላቸው፡፡ አንዱን ሕንፃ 22 የተባለ በሚጠራው አካባቢ እየሰሩ ነው። አቶ ሙሉጌታ በሆቴል ዘርፍም ተሰማርተዋል፡፡ ከበቀለ ሞላ መዝናኛዎች አንዱ የሆነውን የላንጋኖ ሐይቅ መዝናኛ ሆቴል በ80 ሚሊዮን ብር ከባንክ ገዝተውና በ20 ሚሊዮን ብር አድሰው እየሰሩበት ነው፡፡ ወደፊት ባለ 5 ኮከብ መዝናኛ ለማድረግ ዲዛይን አሰርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ካዛንቺስ አካባቢ ለሆቴል የሚሆን ቦታ ገዝተው ወደፊት ገንዘብ በተገኘ ጊዜ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ለመሥራት ዲዛይን እያሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ወደፊት የአገቲቷን ኢኮኖሚ ዕድገትና ፍላጎት እያዩ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የመሰማራት ራዕይ አላቸው። ሌላው ህልማቸው ደግሞ ለወገኖቻቸው የሥራ ዕድል መፍጠር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በግልና በሽርክና በሚሰሩባቸው ድርጅቶች 2000 ያህል ሰራተኞች አሉ። ይህን ቁጥር ወደ 10, 000 ማሳደግ ትልቁ ምኞታቸው ነው፡፡  

Read 3400 times