Saturday, 15 August 2015 15:41

“ግሪን ኮፊ” የቴፒ ቡና ተክል ልማት ድርጅትን ጠቅልሎ ገዛ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    ግሪን ኮፊ አግሮ ኢንዱስትሪ፤ የመንግሥት ይዞታ የነበረውን የቴፒ ቡና ተክል ልማት ድርጅት በ1 ቢ. ብር  ጠቅልሎ መግዛቱን አስታወቀ፡፡
ትናንት ረፋድ ላይ በሂልተን ሆቴል በተደረገው የሽ    ያጭ ውል ስምምነት፣ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገ/መስቀልና የግሪን ኮፊ አግሮ ኢንዱስትሪ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደለ አብርሃ ውሉን ተፈራርመዋል፡፡
አቶ ታደለ በተለይ ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት፣ ግሪን ኮፊ ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት የቴፒ ቡና ተክል ልማት ድርጅትን ድርሻ 51 በመቶ በመያዝ፣ መንግሥት ደግሞ ቀሪውን 49 በመቶ ይዞ በሽርክና ለመሥራት ተስማምተው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ 12 ሺህ ሄክታር ስፋት ያለውን የእርሻ ልማት፣ በ1 ቢሊዮን ብር እንደገለፁት አቶ ታደለ፤ የፊርማ ሥነ - ሥርዓቱ የተፈፀመው የዋጋውን 35 በመቶ፣ 265 ሚሊዮን ብር ባንክ አስገብተው ሲሆን ቀሪውን 65 በመቶ በ5 ዓመት ውስጥ ከፍለው ለማጠናቀቅ መስማማታቸውንም አስረድተዋል፡፡
12ቱ ሺህ ሄክታር መሬት ባረጁ የቡና ዛፎች የተሸፈነ ስለሆነ፣ ከ8-9 ሄክታሩን የተሻለ ምርት በሚሰጡ አዳዲስ ዝርያዎች መተካቱን ጠቁመው፣ ቀሪውም በየዓመቱ 1000 ያህል ሄክታር በአዲስ ምርታማ ዝርያ ይተካል ብለዋል፡፡ ከእርሻ ልማቱ አጠገብ የጋምቤላ ክልል ይዞታ የሆነውን 3ሺህ ሄክታር መሬት ክልሉን ጠይቀው ስለፈቀደላቸው አዲስ ፕሮጀክት ቀርፀው እንደሚያለሙትም አቶ ታደለ አክለው ገልፀዋል፡፡
ከእርሻው የሚገኘውን የቡና ምርት ኤክስፖርት በማድረግ 20 ሚሊዮን ዶላር እንደሚገኝ የጠቀሱት ባለሀብቱ፤ እርሻው ለማር ምርት አመቺ በመሆኑ በዓለም ተወዳጅ የሆነውን ኮፊ ሀኒ የተባለ የማር ዓይነት በአነስተኛ መሳሪያ እያዘጋጁ ወደ ውጭ ሲልኩ ቆይተዋል፡፡ አሁን በብዛት (50 እና 60 ኮንቴይነር ኮፊ ሀኒ) ወደ ውጭ በመላክ ከ4-5 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ፋብሪካ እየገነቡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የቴፒ ቡና እርሻ ልማት በረከት ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች እያመረቱ ለመላክ አቅደዋል፡፡ ብዙም ባይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ፓልም ኦይል የሚገኘው በቴፒ እርሻ ልማት ብቻ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ታደለ፤ ለሙከራ ከማሌዢያና ኢንዶኔዢያ የተለያየ ዝርያ አምጥተው በ120 ሄክታር መሬት ላይ በመትከል ምርቱ ደርሶ አይተውታል፡፡ በአነስተኛ መሳሪያ እያዘጋጁ በየወሩ አንድ መኪና ዘይት ለተለያዩ ድርጅቶች የሚያቀርቡ ሲሆን፤ ወደ ዘይት ከመለወጡ በፊት ያለውን ድፍድፍ፣ የሳሙና ፋብሪካዎች በጥሩ ዋጋ በሰልፍ እንደሚገዙና በየወሩ አንድ መኪና ድፍድፍ እንደሚሸጡ ተናግረዋል፡፡ የፓልም እርሻውን ወደ 10,000 ሄክታር ለማሳደግ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ኩባንያ ማግኘታቸውን ጠቅሰው፣ የእርሻ መሬት ለማግኘት ከክልሉ ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንም አቶ ታደለ ገልፀዋል፡፡
በቴፒ እርሻ ልማት ውስጥ ባሉ 6 እርሻዎች፣ 16ሺ ሰራተኞች ተቀጥረው እንደሚሰሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 1512 times