Saturday, 08 August 2015 09:40

ወደ አገሩ ሲመለስ “አዲስ አበባ አሸነፈች፤ ቺካጐ ተሸነፈች” የተባለለት አርቲስት

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(14 votes)

  በ15 ዓመት 30 ት/ቤቶች አሠርቶ፣ ከ225 ሺህ ዜጐች በላይ አስተምሯል
              አያት አካባቢ ሪል እስቴት እየሠራ ሲሆን ሌሎች ቢዝነሶችም አሉት
                 4ኛው አዲስ አልበሙ ለዲያስፖራ በዓል ይለቀቃል
              ከ30 ጋንግስተሮች ከፍተኛ አደጋ ማምለጥ ችሏል
                          
   በቺካጐ - አሜሪካ 1000 ሰዎች የሚያስተናግድ ትልቅ ክለብ ነበረው፡፡ እነሱ በሳምንት ሁለት ቀን ይዘፍናሉ። ሌላውን ቀን ባንዱ ይጫወታል፡፡ በ2008 (እ.ኤ.አ) የአሜሪካ ኢኮኖሚ ቀዝቀዝ ብሎ ስለነበር የባንዱ ገቢ እየቀነሰ መጣ። ከዚያ በፊት ወደ ኢትዮጵያ ይመላለስ ስለነበር የአገሪቷን ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ ሰላሟን ጭምር ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ልመለስ? አልመለስ? እያለ ሲያመነታ ነበር፡፡
በምርጫ 97 ወቅት ከፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅና ከፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ጋር ሆነው በመንግሥትና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል እርቅ ለመፍጠር ሞክረዋል። በዚህ አጋጣሚ ከመንግሥትና ከጠቅላይ ሚ/ር መለስ ጋር ብዙ ጊዜ ተነጋግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚ/ሩን በተደጋጋሚ በግል የማነጋገር ዕድልም አግኝቷል፡፡ እሳቸው ለምን ወደ አገርህ ገብተህ ኢንቨስት አታደርግም? እያሉ ያነሳሱት ነበር፡፡ ስለዚህ ማመንታቱን ትቶ ወደ አገሩ ለመመለስ ወሰነ፡፡
ቺካጐ ያለውን ቢዝነሴን ዘግቼ ወደ አገሬ ልመለስ ነው ሲል አሜሪካ ያሉ ታዋቂ የጋዜጣ፣ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጋዜጠኞች፡- “ቺካጐ ትሪቡን” “ሲቢኤስ”፣ “ኤንቢኤስ”፣ “ሲኤንኤን፣…የዓለም ታዋቂ ሚዲያዎች ካሜራቸውን በከባድ መኪና ደግነው ቤቱ ድረስ በመሄድ በጥያቄ እንዳጣደፉት ይናገራል፡፡
ለምንድነው ይህን የዓለም ሕዝቦች መገናኛ የሆነውን የቺካጐ የባህል ማዕከል (መልቲንግ ፖት) ዘግተህ የምትሄደው? ለደንበኞችህስ ምንድነው ያሰብከው?... እያሉ ጥያቄያቸውን አዥጐደጐዱለት፡፡ በዚህ ጊዜ አንድ ሐሳብ መጣለት - አገሩን ማስተዋወቅ፡፡ የዓለም ጋዜጠኞች እቤቱ መጥተውለት እንዴት ይህን ዕድል ይለፈው?! አሁን ኢትዮጵያ እያደገች ነው፡፡ 60 በመቶ የሥራ ኃይሏ ከ25 ዓመት በታች የሆነ ወጣት ነው፡፡ በዚህ ላይ የጉልበት ዋጋ ርካሽ ነው፣ ለኤሌክትሪክ የሚከፈለው ኪራይ እጅግ ዝቅተኛ ነው፣ ተዝቆ የማያልቅ ጥሬ ሀብት ሞልቷል… በማለት ነገራቸው፡፡
 በማግስቱ ታዲያ የአገሬው ትልቁ ጋዜጣ “ቺካጐ ትሪቡን” የእግር ኳስ ጨዋታ ይመስል “አዲስ አበባ ዎን፤ ቺካጐ ሎስት” (አዲስ አበባ አሸነፈች፤ ቺካጐ ተሸነፈች) በማለት በፊት ገጹ ዘገበው፡፡
ወደ ክበቡ የሚመጡት ሰዎች ቺካጐ ውስጥ አሉ የተባሉ ፕሮፌሰሮች፣ ዶክተሮች፣ ሀብታም ነጋዴዎች፣ የኮርፖሬሽንና የኩባንያ ማናጀሮች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣… ብቻ የማይመጣ ሰው አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ ለ27 ዓመታት እዚያ እየመጣ ፣ እየተዋወቀ፣ እየተጋባ፣ ልጆቹ ሲመረቁ እዚያ እየሄደ ተዝናንቷል፤ ተደስቷል፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ ሴኔተር ሆነው በክለቡ ተዝናንተዋል። በቅርቡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ኢትዮጵያን ሲጐበኙ አብረዋቸው የመጡት የንግድ ሚኒስትሯ ፔኒ ፕሪትስከር፣ ዴቪድ ፕሪትስከር የተባለው ልጃቸው ከኮሌጅ ሲመረቅ ከቤተሰባቸው ጋር በዚያ ነበር የተዝናኑት፡፡
ለአንድ ሳምንት የቆየ ፕሮግራም አዘጋጅተው ነው ሕዝቡን የተሰናበቱት፡፡ በዚያን ወቅት በርካታ ፈረንጆች አልቅሰዋል፡፡ የሕዝቡና የጋዜጠኞቹ ሁኔታ ለአገር የሚበጅ ነገር እንዲያስብ አመቺ ሁኔታ ፈጠረለት፡፡ እነዚህን ሁሉ የከበሩ ሀብታም ሰዎች ዝም ብዬ ከምበትን ለምን ቱሪስት አድርጌ ወደ አገሬ እንዲመጡ አላደርግም? በማለት አሰበ። አገሬ ገብቼ ቢዝነስ እሠራለሁ  እንጂ የቺካጐውን ክለብ በአዲስ አበባ እከፍታለሁ የሚል ሐሳብ በጭራሽ አልነበረውም፡፡ ሆኖም የለመደው ሕዝብ በቱሪስትነት መጥቶ ኢትዮጵያን እንዲጐበኝ ለማነሳሳት “በእርግጥ ክለቡን ጭራሽ ልዘጋው ሳይሆን አዲስ አበባ ልወስደው ነው” አለ፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ጓዙን ጠቅልሎ የመጣው የዛሬ 4 ዓመት ነው፡፡ አሁን  በአያት አካባቢ ቤት (ሪል እስቴት) እየሠራ ነው። በሽርክና የገዙትን የኮንስትራክሽን ማሽነሪም ያከራያሉ፡፡ ሁለት ዶክሜንተሪ ፊልሞችን ሠርቷል፡፡ አንዱ ባስገነባቸው 30 ት/ቤቶች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በውጭ ያለው 2 ሚሊዮን ያህል ኢትዮጵያዊ ትንሽም ቢሆን የበኩሉን ጥረት ቢያደርግ አገሪቷን ሊለውጥ እንደሚችል ለማሳየት የሠራው ነው፡፡ ይህ ፊልም የዛሬ ዓመት ተኩል ገደማ በሲኤንኤን ኢንሳይድ አፍሪካ ፕሮግራም በጥቂቱ ቀርቧል፡፡ ሌላው ከአቢሲኒያ ፓይለት ማሠልጠኛ ት/ቤት ባለቤት  ከካፒቴን ሰለሞን ጋር በመሆን የማሻን ደን የሚያሳይ ትምህርታዊ ዶክሜንተሪ ፊልም ነው፡፡
በዘፋኝነቱ ደግሞ ለዲያስፖራዎች በዓል የሚለቀቅ “አይዞኝ” የተባለ አዲስ አልበም ሠርቷል፡፡  አልበሙ ኤልያስ መልካ፣ ሄኖክ መሐሪ፣ አየለ ማሞ፣ ታደለ ገመቹ ሁንአንተ ሙሉ የተሳተፉበት ሲሆን ሁለት ኦሮምኛ፤ የተቀሩት አማርኛና ሬጌ (እንግሊዝኛ) የሚበዛባቸው 12 ዘፈኖችን ያቀነቀነው እስካሁን ታሪኩን የተረኩላችሁ አርቲስት ዘለቀ ገሠሠ ነው፡፡
ዘለቀ ገሠሠ የተወለደው በአንድ ወቅት የኢትዮጵያና የኢሊባቡር (ኢሉአባቦራ) ዋና ከተማ በነበረችው ጐሬ ነው። እስከ 13 ዓመቱ ድረስ በትውልድ መንደሩ ሲማር ቆይቶ፣ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመከታተል ወደ አዲስ አበባ መጣ። ሕይወቱን እየመራበት ያለው የሙዚቃ ፍቅር የተጠነሰሰው እዚያው ጐሬ ሳለ ነው፡፡ ጐረቤቱ ሚሽነሪዎች ስለነበሩ ወደ ሙዚቃ ዓለም ያስገቡት እነሱ ናቸው፡፡ እቤታቸው እየሄደ ፒያኖ ይጫወት ነበር፡፡ በሙዚቃ እንዲገፋ ምክንያት የሆኑት ደግሞ እናቱ ናቸው። አዲስ አበባ እንደመጣ ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው ያኔ ፕሪንስ ዘነበወርቅ፣ አሁን ሚስፎርድ በሚባለው ት/ቤት 9ኛ ክፍል ገባ፡፡ ሚስ ፎርድ አሜሪካዊ ስለሆኑ እናቱ  “አንተ ከእነሱ ጋር ተለማምደሃልና እሳቸው ጋ ገብተህ ተማር” አሉት፡፡ እዚያ ት/ቤት ሁለት ዓመት እንደተማረ፣ ወደ ያኔው ልዑል መኮንን፣ አሁን አዲስ ከተማ መሰናዶ ት/ቤት ተዛወረ፡፡
ወቅቱ ተማሪዎች “መሬት ለአራሹ” እያሉ የሚጮሁበት ጊዜ ስለነበር በትምህርቱ አልገፋም፡፡ ዘለቀ ሙዚቃ መጫወት የጀመረው 9ኛ ክፍል ሳለ ነው፡፡ ያኔ ጀነራል ዊንጌት ይማር የነበረው ታላቅ ወንድሙ ሙሉጌታ ገሠሠ፣ ድራመሩና ኪ ቦርድ ተጫዋቹ ከሳንጆሴፍ፣ ዘለቀ ከሚስ ፎርድ ት/ቤት ሆነው፣ አራት ወጣት ሙዚቀኞች ናይጄሪያ ኤምባሲ አካባቢ በ1964 ዓ.ም ዳሎል ባንድን መሠረቱ፡፡ ዳሎል ባንድ በዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ምረቃ፣ በ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የወላጆች በዓል ቀን እየተጋበዘ ሙዚቃ ያቀርብ ነበር፡፡
ምኒሊክ ወሰናቸውና አያሌው መስፍን ወጣቶቹ በነበራቸው የሙዚቃ ችሎታ በጣም ይወዷቸው ነበር። ስለዚህ ት/ቤት ሲዘጋ ምኒሊክና አያሌው አማርኛ፣ ዘለቀ እንግሊዝኛ እየዘፈኑ የትያትርና ድራማ ክበቦችን ይዘው በየክፍለሀገሩ እየተዘዋወሩ ሙዚቃ ያቀርቡ ነበር፡፡ ይህን የትያትርና ሙዚቃ ትርዒት ከ66ቱ አብዮት በፊት ለአንድ ዓመት፣ ከአብዮቱ በኋላ ለሁለት ዓመት ቀይ ሽብር እስኪጀመር ድረስ በየክፍለ ሀገሩ ቀርቧል፡፡
የዳሎል መበተን
ወጣቶቹ ሙዚቀኞች የሚጫወቱት የምዕራቦቹን ዘፋኞች የጀምስ ብራውን፣ ስቲቪ ዎንደር፣ አሪታ ፍራንክሊን፣… ዘፈኖች ስለነበር ሶሻሊስቱ ደርግ ደስ አላለውም፡፡ ወቅቱ የወሎ ድርቅ የተከሰተበት ጊዜ ነበር። በየ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ያሉ 10 የወጣት ባንዶች በድርቅ ለተጐዱ ረሃብተኞች ገቢ ማሰባሰቢያ በስታዲየም ትልቅ የሙዚቃ ድግስ (ኮንሰርት) አዘጋጁ፡፡ 10ሺህ ቲኬቶች ከሸጡ በኋላ ደርግ ሙዚቃዎቹን ሳንሱር አድርጐ፣ ዝግጅቱ በሚቀርብበት ዕለት ይህን የኢምፔሪያሊስት ሙዚቃ ማቅረብ አትችሉም ብሎ ከለከላቸው፤ ካልቾ የቀመሱም ነበሩ፡፡
የዕድገት በሕብረት ዘመቻ ታውጆ ስለነበር፣ 10ኛ ክፍል የደረሱ ሁሉ የመዝመት ግዴታ ነበረበት፡፡ የዳሎል ባንድ አባላትም ለዘመቻ ተመዘገቡ፡፡ ወጣቶቹ ሙዚቀኞች አንድ ሐሳብ መጣላቸው፡፡ እኛ ተበታትነን ከምንዘምት አንድ ላይ ሆነን፣ በየዘመቻ ጣቢያ እየዞርን ዘማቾቹን እናነቃቃ በማለት ሐሳባቸውን ለዘመቻ መምሪያ ሄደው አቀረቡ፡፡ በቢሮው የነበሩት ኮሎኔል (አሁን በሕይወት የሉም ተገድለዋል) ዱላ ቀረሽ ስድብ አውርደውባቸው ተባረሩ፡፡
በዚያን ወቅት ት/ቤቶች ተዘግተዋል፤ ሙዚቃቸው የኢምፔሪያሊስት ነው ተብሎ ተከልክሏል፡፡ በዚህ ላይ ኪቦርድ ተጫዋቹ ጓደኛቸው ተገድሎና ሬሳው ፒያሳ ተጥሎ ሲያዩ በጣም አዘኑ፤ ተስፋ ቆረጡ፤ አገር ጥለው ለመሰደድ ቆረጡ፡፡
ለአንድ ሳምንት በእግራቸው ተጉዘው ጂቡቲ ደረሱ። በጂቡቲ መጥፎ ዕድል አጋጠማቸው፡፡ በስደተኝነት ለመመዝገብ የሄዱበት ጣቢያ አዛዥ የኢሳ ጐሳ አባል ነበር፡፡ ያ ሰው ኢትዮጵያና ሱማሌ ባደረጉት ጦርነት በመሸነፋቸው፣ ለኢትዮጵያውያን ጥሩ አመለካከት ስላልነበረው ደርግ እንዲያስራቸው በመኪና አሳፍሮ ወደ ኢትዮጵያ መለሳቸው። መኪናው እየተጓዘ ሳለ ሳይጠበቅ ከባድ ዶፍ ዝናብ ጣለና መኪናው ጐርፉን መሻገር ስላቃተው እዚያው አውርዷቸው ተመለሰ፡፡
ወጣቶቹ ስደተኞች ተስፋ ሳይቆርጡ ዞረው ወደ ጂቡቲ ተመለሱ፡፡ የጅቡቲ ድንበር አጥር ስላለው ሾልከው ገቡና በስደተኝነት ተመዝግበው ለአንድ ወር ታሰሩ፡፡ ከእነዘለቀ ቀድሞ ታላቅ ወንድሙ ሙሉጌታ ገሠሠ ጅቡቲ ገብቶ ነበር፡፡ ሙሉጌታ፣ በዚያን ወቅት ሥልጣን ላይ የነበረ የጅቡቲ ጠቅላይ ሚ/ር ዘመድ የሆነ የሚያውቀው ሙዚቀኛ ልጅ አግኝቶ ወደ ወህኒ ቤቱ አምጥቶ አስተዋወቃቸው። ልጁ የባለሥልጣን ወገን ስለሆነና ሰዎቹን ስለሚያውቅ አስፈትቷቸው ጅቡቲ ገቡ፡፡
የሙዚቃ ፍላጐታቸው ስላልበረደና ተመሳሳይ ስሜት ያላቸው ወጣቶች ስለተገናኙ፣ ያስፈታቸውን ልጅ ወኪላቸው አድርገው “ብራዘርስ ባንድ” የተባለ የሙዚቃ ክለብ አቋቋሙ፡፡ ታላቅ ወንድማቸው አዲስ ገሠሠ፤ በንጉሡ ጊዜ የአውሮፕላን አብራሪነት ትምህርት ለመማር አሜሪካ ተልኮ ነበር፡፡ ደርግ ሥልጣን ሲይዝ ሳይመለስ እዚያው ቀረ፡፡ በጂቡቲ ለ6 ወራት ሙዚቃ ሲጫወቱ ከቆዩ በኋላ የአዲስን አድራሻ እንደምንም አፈላልገው መጻጻፍ ጀመሩ፡፡ በጂቡቲ ቆይታቸው ዕድለኞች ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ጥሩ እየሠሩ ከመሆኑም በላይ፤ ልጁ ትልቅ ቤት ተከራይቶላቸው ስለነበር፣ ስደተኞቹ ሙዚቀኞች ለ20 ሌሎች ስደተኞች መጠለያ ሆነው ነበር፡፡
አሜሪካ መግባትና ውጣ ውረድ
አዲስ ገሠሠ አሜሪካ የሚገባበትን ዘዴ ያውቃል። የተማሪ ቪዛ አውጥቶላቸው የአውሮፕላን ቲኬት ልኮላቸው በ1971 ወንድማማቾቹ ሙሉጌታና ዘለቀ ገሠሠ አሜሪካ ገቡ። የያዙት የተማሪ ቪዛ ስለሆነ ኮሌጅ ገብቶ መማር እንጂ ሥራ መሥራት አይችሉም፡፡ አዲስ ገሠሠ ቺካጐ ስለሆነ እነዘለቀም ማረፊያቸው ቺካጐ፣ ትምህርታቸው ኤሊኖይ ሆነ፡፡ በአሜሪካ ኮሌጆች ስትማር ስኮላር ሺፕ (ነፃ የትምህርት ዕድል) ካላገኘህ በስተቀር የውጭ ዜጋ ለትምህርት የሚከፍለው ነዋሪዎቹ ከሚከፍሉት እጥፍ ነው፡፡
ለመኖር፣ ለቤት ኪራይ፣ ለት/ቤት ክፍያ፣… ከአንድ በላይ ሥራ ማግኘት ፍላጐት ሳይሆን ግዴታም ነው። “ከ24 ሰዓት ውስጥ 4 ሰዓት ነው የምንተኛው፡፡ 4ቱ ሰዓት የትምህርት ሲሆን ቀሪው ሥራ ላይ የምትቆይበት ነው፡፡ እኔ ግሮሰሪ ውስጥ ክለርክ ነበርኩ፡፡ ክለርክ ማለት ዕቃ ያወርዳል፣ ይደረድራል፣ ቤት ይጠርጋል… የዚህ ዓይነት ከባድ ሥራ እየሠራን ነው ለኮሌጅ የምንከፍለው፡፡ እየቆየን ስንሄድ መንጃ ፈቃድ አውጥተን ታክሲ መሥራት ጀመርን፡፡ እንዲህ እየሠራን፣ እየተማርን፣ ሙዚቃ እየተጫወትን ነው አሜሪካ የኖርነው” ይላል ዘለቀ፡፡
የዳሎል ዳግም ልደት
ያለ ዕረፍት ቀን ተሌት እየሠሩ፣ ጂቡቲ ለቀሩት የዳሎል ባንድ አባላት የአውሮፕላን ቲኬትና አስፈላጊ ዶክመንቶች ልከው እንዲቀላቀሏቸው አደረጉና ኤሊኖይ በገቡ በዓመታቸው ዳሎል ባንድ እንደገና በአሜሪካ ተመሠረተ፡፡ የመጀመሪያ ሙዚቃቸውን ያቀረቡት በሚማሩበት ኢሊኖይ ኮሌጅ ነበር፡፡ በአሜሪካ ለጥቁሮች የሚከበር (ፌብሩዋሪ ብላክ ሂስትሪ መንዝ) የሚባል ወር አለ፡፡
ለዚያ በዓል አከባበር ሙዚቃ እናቅርብ በማለት ጠየቁ። አሜሪካኖቹ አላመኑም፡፡ አንድ ጥሩ መምህር ነበሩ፡፡ እስቲ እንሞክራቸው ብለው ፈቀዱላቸው፡፡ ዳሎል ባንድ ሙዚቃውን አቀረበ፡፡ ተመልካቹ በጣም ተደስቶ አጨበጨበላቸው፡፡ ወጣቶቹ ያጨበጭቡልናል ብለው ስላልጠበቁ፣ ሞራላቸው ተበረታታና የተሻለ መጫወት ቀጠሉ፡፡
በዚያን ወቅት አሜሪካ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ባንድ አልነበረም፡፡ ሙዚቃቸውን ይዘው ዋሽንግተን ሄዱ። እዚያ፣ የመጀመሪያውን ኢትዮጵያዊ ሬኮርድ ካምፓኒ የጀመሩት አቶ አመሃ እሸቴ የተባሉ ሰው ብሉ ናይል የተባለ ሬስቶራንት ነበራቸው፡፡ ያኔ እዚያ የነበሩት አቶ አብነት ገ/መስቀልም በሙዚቃው ረድተዋቸዋል፡፡  በዚያ ሬስቶራንት ለዘመን መለወጫ ዝግጅታቸውን አቀረቡ። እዚያ የነበረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በጣም ወዶላቸው ተመለሱ፡፡ ለፋሲካ በዓልም በዋሽንግተን ደግመው ካቀረቡ በኋላ፣ ዳሎል ባንድ ካሊፎርኒያም ሄዶ ትልቅ ዝግጅት አቀረበ፤ በጣም ተወደደለት፡፡
ከቦብ ማርሌ ቤተሰብ ጋር ትውውቅ
ካሊፎርኒያ እያሉ እንደ ዕድል ሆኖ ስቲቪ ወንደርን አገኙ፡፡ ስቲቪ ኩባንያ ውስጥ የሬዲዮ ማናጀር ሆና የምትሠራ ኢትዮጵያዊት ዶክተር ነበረች፡፡ ሙዚቃቸውን ሲያቀርቡ አይታቸው ኖራ፣ ስቲቪ‘ኮ የኢትዮጵያ ወዳጅ ነው፡፡ የኢትዮጵያንና የጃማይካን ሙዚቃ በጣም ይወዳል።  ላስተዋውቃችሁ ብላ አስተዋወቀቻቸው። ስቲቪ በስቱዲዮው 5 ሙዚቃ ቀድቶላቸው እንዴት የአሜሪካ ሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ መግባት እንደሚቻል ነገራቸው። መጀመሪያ ዴሞቴፕ አንድ አምስት ዘፈን ቅዱ፤ ፎቶ ተነሱ። ከዚያ ታሪካችሁንና ስልካችሁን ጽፋችሁ እንደ ፓኬጅ አድርጋችሁ ለየኩባንያው ላኩ ብሎ መከራቸው፡፡
የባንዱ መሪ ዘለቀ ማናጀሩ ደግሞ አዲስ ገሠሠ ነበሩ፡፡ እንደተመከረው አድርጐ ፕሮፋይላቸውን ለ25 ኩባንያዎች ላከ፡፡ በአጋጣሚ ፓኬጁ የተላከለት አንደኛው ኩባንያ ለንደን የሚገኘው የቦብ ማርሌ አይላንድ ሬከርድስ ነበር። ያኔ ቦብ ማርሌ ካረፈ ዓመት እንኳ አልሞላውም። የኩባንያው ኃላፊ አስቸኳይ መልዕክት ለቦብ ማርሌ ሚስት ለሪታ ማርሌ ጃማይካ ላከላት፡፡ ሪታ ደስ ብሏት “ቦብም‘ኮ ሕልሙ ከኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ጋር መሥራት ነበር። እሱ አሁን በሕይወት ባይኖርም በቅርቡ ሙት ዓመቱን ስለምናከብር እዚያ ላይ ቢገኙ ጥሩ ነው” በማለት በዘለቀ ቁጥር ደወለችለት፡፡
ስልኩን አንስቶ ሄሎ ሲል “ሪታ ማርሌ ነኝ” ስትለው ያልጠበቀው ነገር ስለሆነበት ደንግጦ ስልኩን ሊጥለው ነበር። የቦብን ሕልም ነግራው በሙት ዓመቱ ላይ ቢገኙ ደስ እንደሚላት ገለፀችለት፡፡ ሐሳቡን ቢቀበልም አንድ ችግር እንዳለባቸው አጫወታት፡፡ ያን ጊዜ የነበራቸው የተማሪ ቪዛ ስለሆነ ከአሜሪካ ውጭ መጓዝ እንደማይችሉ ነገራት፡፡ ልዩ ደብዳቤ ጽፋ ለጃማይካ ቆንስላ ላከች፡፡ የጃማይካ ቆንስላ ደግሞ ለአሜሪካ ሚግሬሽን ጽፎ የዳሎል ባንድ አባላት ጃማይካ ገቡ፡፡
የቦብ ሙት ዓመት የተከበረው ተራራ ላይ ነበር፡፡ ዳሎሎች እዚያ ላይ ሙዚቃቸውን ሲያቀርቡ ያላያቸው የዓለም የሙዚቃ ኢንዱስትሪ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ ተመልካቹም በጣም ተደሰተ፤ ሪታም እጅግ ፈነጠዘች፡፡ ያኔ እነ ዚጊ ማርሌ ልጆች ነበሩ፡፡ ቦብም ሆነ ልጆቹ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ባህል የቆረቡ ክርስቲያኖች ናቸው። ሪታ፤ “እናንተን ማግኘቴ የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሆነ ነው፡፡ ከልጆቼ ጋር እንድትቀራረቡ እፈልጋለሁ” አለችው ዘለቀን፡፡ አዲስ ገሠሠን የልጆቹ ማናጀር አድርጋ እዚያው አስቀረችው። የክብር ዶክተሩን የመሐሙድ አህመድን “አሽቃሩና” የካሜራዊውን ዘፋኝ ማኑ ዲባንጐን “ሶል ማኮሳ”ን ዘለቀ “ሬጌ ማኮሳ” ብሎ ሲጫወት ሪታ በጣም ወደደችው፡፡ ስለዚህ በበአሉ ዕለት ካልቀዳህልኝ ብላ ወጥራ ያዘችው። የቦብ ስቱዲዮ የሚገኝበት ከበዓሉ ስፍራ 100 ኪ.ሜ ወደ ዋና ከተማዋ ኪንግስተን ሄደው ቀዳቻቸውና እነ ዘለቀ ከጃማይካ ሳይወጡ ነጠላ ዘፈኑ ተለቀቀ፡፡
ከዚያማ የሪታና ዳሎል ባንድ ፍቅር በፍቅር ሆኑ። እነዘለቀም ጃይማካ ሲሄዱ በኢትዮጵያዊ ባህል መሠረት የሐበሻ ቀሚስ፣ የአገልግል ምግብ፣ የእንጨት መስቀል… ይዘውላት ስለሚሄዱ ቤተሰብነታቸው በጣም ጠነከረ። ሪታ ማርሌም ከመውደድ አልፋ  የዳሎል ባንድ ማናጀር ሆነች። በዚህ ዓይነት ፍቅራቸው ጠንቶ፣ ትላልቅ ፌስቲቫሎች በሚዘጋጁበት ጊዜ ሁሉ እንዲቀርቡ ስለምታደርግ ጃማይካን ብዙ ጊዜ ተመላለሱባት፤ ሦስት ወይም አራት ነጠላ ዘፈኖች አወጡባት፡፡
ስኬት በአሜሪካ
ቺካጐ ውስጥ የሚጫወቱበት ናይት ክለብ በመንግሥት ተዘግቶ ጨረታ ወጣ፡፡ ዘለቀ፣ የቢዝነስ ፕሮፌሰሩን አማክሮ በባንዱ ስም ለመጫረት ፈለገ፡፡ ጨረታውን ያወጣው ፌዴራል መንግሥት ስለሆነ ሪታ ማርሌ “ማናጀራቸው እኔ ነኝ” ብላ ነግራላቸው ጨረታውን አሸነፉ፡፡ ያን ጨረታ ማሸነፋቸው አሜሪካ ውስጥ መነጋገሪያ ሆነ፡፡ በዚያን ወቅት ፕሬዚዳንቱ ሬጋን ነበሩ፡፡ “የሬጋን የሬጌ ኮኔክሽን! ሪፐብሊካኖቹ ለኢትዮጵያውያኖቹ ክለብ ስጧቸው” በሚል ትልቅ ዜና ሆነ። ይህ ሁሉ ሲሆን አሜሪካና ጃማይካ እየተመላለሱ ነበር የሚሠሩት፡፡ በዚህ መሃል አልበም አስቀርፁ ተባሉና “ላንድ ኦፍ ዘ ጀነሲስ” የተባለውን “ሆያ ሆዬ”፣ “ሰላም ሰላም”፣… የሚሉትን ዘፈኖች የያዘው የመጀመሪያ አልበማቸው  ጃማይካ ውስጥ በቦብ ማርሌ ስቱዲዮ ተቀረፀ፡፡
የቦብ ልጆች እነ ዚጊ ማርሌ እያደጉ ነበር፡፡ የዳሎል ባንድ አባላት በየኮንሰርቶቹ ሲጫወቱ ሲያይ፣ ዚጊ ማርሌ ከእነሱ ጋር ለመጫወት ልቡ ተነሳሳና እናቱን፣ “የአባቴም ምኞት ይኼው ነበር፡፡ እኔ ‘ኮ ከእነሱ ጋር ነው መጫወት የምፈልገው” አላት፡፡
ሪታ፣ አዲስንና ዘለቀን፣ “ዚጊ እንዲህ ይላል፤ ምን ይመስላችኋል?” በማለት አማከረቻቸው፡፡ እነሱም ታዲያ ምን ችግር አለው? አብረን እንሠራለን አሏት፡፡ ከዚጊ ማርሌ ጋር እየሠሩ ሁለት አልበም አወጡ፡፡ እነዚያ አልበሞች እያንዳንዳቸው ሦስት ሦስት ሚሊዮን ኮፒ ስለተሸጡ ትሪፕለም ፕላቲንየም ተባሉ፡፡ (አዲስ አልበም ወጥቶ አንድ ሚሊዮን ኮፒ ከተሸጠ ፕላቲኒየም፣ ሁለት ሚሊዮን ከተሸጠ ደብል ፕላቲኒየም፣ ሦስት ሚሊዮን ከተሸጠ ትሪፕለም ይባላል)፡፡
የግራሚ አዋርድም አሸነፉ፡፡ ዚጊ ማርሌ መጣ ሲባል ሕዝቡ እንደ ጉድ ነው የሚያያቸው፡፡ ዓለምን ዘጠኝ ጊዜ ዞረዋል፡፡ አውሮፓ ውስጥ 40ሺህ፣ 80ሺህ 100ሺህ ሕዝብ እየወጣ ይታደማቸው ነበር፡፡ ከዚጊ ጋር አንድ አልበም ከሠሩ ለዘጠኝና ለአሥር ወር ዓለምን ይዞራሉ፡፡ እነዘለቀ ትምህርቱን መከታተል ስላልቻሉ አቋርጠው ከዚጊ ጋር ለ4 ዓመት ዓለምን ዞሩ፡፡ ከዚያ ሲመለሱ ደግሞ የቺካጐውን ክለብ ማጠናከር ያዙ፡፡
የዳሎል ባንድ አባላት ኤል ፒ የተባለች 8 ዘፈን የያዘች አልበም አውጥተው ነበር፡፡ ክለቡም ቺካጐ ውስጥ ትልቅ ስምና ዝና አገኘ፡፡ ከሰኞ እስከ እሁድ መቆሚያ ቦታ የለም። ዳሎሎች ሁለት ቀን ይጫወታሉ፤ በተቀሩት ቀናት ሌሎች የሬጌ ባንዶች ነበር የሚጫወቱት፡፡ በቃ የቺካጐ የባህል ማዕከል ሆነ፡፡
ከዚጊ ጋር መለያየትና የዳሎል መከፋፈል
ከዚጊ ጋር እየሠሩ ጥሩ ገቢ፤ ጥሩ ስምና ዝና እያተረፉ ነበር፡፡ ነገር ግን በዚሁ ከቀጠሉ ሕልማቸውን መርሳት ሆኖ ተሰማቸው፡፡ የዳሎል ባንድ ሕልም የኢትዮጵያን ሙዚቃ ማንሳትና ማሳደግ ስለሆነ ዚጊን የእኛንም እንሥራ አሉት፡፡ ከእሱ መለየታቸውን ባይወደውም ሊጫናቸው ስላልፈለገ ቅር እያለውም ቢሆን “ኦኬ! ዩ አር ፍሪ” አላቸው። የራሳቸውን ሙዚቃ መሥራት እንደጀመሩ በመሃከላቸው ልዩነት ተፈጠረ፡፡ የልዩነቱ ምክንያት በሬጌው እንቀጥል ወይስ ሌሎች የአማርኛ፣ ጉራጊኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግሪኛ… ዘፈኖች እንጨምርበት የሚል ነበር፡፡ አልተስማሙም። ዘለቀ፣ ሙሉጌታና መላከ ረታ ሆነው “ባሮ” የተሰኘ ክለብ አቋቁመው ተለዩ፡፡ ሴሎቹ  አንድ የዶሚኒካ ዘፋኝ ጨምረው “ጊዜ ባንድ”ን መሥርተው በሬጌ ቀጠሉ፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን ክለቡ አልፈረሰም፣ የጋራ ሀብታቸው ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ዘለቀ “ዶንት ሌትሚዳውን”፣ “ሺቨሪንግ ሚ” … የተሰኙ ዘፈኖች የያዘውን የራሱን አልበም አወጣና መላውን አሜሪካ እየዞረ አልበሙን አስተዋወቀ፡፡ የቺካጐው ክለብ ዕድገት
እየሰፋ ሲሄድ፣ ሁለቴ አፍርሰው ከላይም ከታችም አስፍተው ባለሁለት ፎቅ አደረጉት፡፡ ሙሉጌታ ገሠሠና መላከ ረታም የየራሳቸውን አልበም አወጡ፡፡ ስለዚህ፣ ዘለቀ፣ “ዳሎል ቅርንጫፍ አወጣ እንጂ አልፈረሰም” ይላል፡፡     
የዘረኝነትና ጣጣ
ዳሎል ባንድ በአሜሪካ ጥሩ እየራ ሳለ ብዙ ጊዜ ችግር ገጥሞታል፡፡ ችግርን ተቋቁሞ ማለፍ ነው እንጂ ህይወት ያለ ችግር መች ይጣፍጣል ይላል ዘለቀ፡፡ የባንዱ አባላት በሙሉ አፍሪካዊ  ጥቁሮች ናቸው፡፡ በመላ አሜሪካ እየዞሩ ኮንሰርት ሲያቀርቡ፣ በቴክሳስና በአለባማ ዘረኛ ነጮች አደጋ ሊያደርሱባቸው ሞክረው ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ኮንሰርት አቅርበው እንደጨረሱ ህዝቡ በሰጣቸው ሞራል ተደስተው ወደሚቀጥቀለው ከተማ እየጨፈሩ ሲጓዙ፣ 30 የሚሆኑ ጋንግስተሮች አደጋ ሊያደርሱባቸው በሞተር ሳይክል ተከተሏቸው፡፡
የባንዱ አባላት ባቀረቡት ኮንሰርት ተደስተው ያጀቧቸው ነበር የመሰሏቸው፡፡ ሊያስቆሟቸው ሲሞክሩ ግን ጋንግስተሮች መሆናቸውን ስለተረዱ እግሬ አውጪኝ ብለው ተፈተለኩ፡፡ መኪናቸውን የያዘው ዘለቀ ነበር፡፡ በከፍተኛ ፍጥነት እየነዳ ወደፊት ከነፈና የሆነ ቦታ ሲደርስ ቤንዚን ማደያ ስላየ ወደዚያ ታጠፈ፡፡ ጋንግስተሮቹም ታጠፉ፡፡ እንዳልለቀቋቸው ሲያውቁ ከመኪናዋ ወርደው ወደ ማደያው ኪችን ዘለው ገቡ፡፡ ምክንያቱም ኪችን የሚሰሩት ብዙ ጊዜ የተለያየ ቀለም ያላቸው ዜጎች ስለሆኑ አንለይም በማለት ነው፡፡ ትረፊ ያላት ነፍስ ሆኖ ጋንግስተሮቹም ከዚያ በላይ አላሳደዷቸውም፡፡ በኋላ ፖሊሶች ተጠርተው ከዚያ ጉድ አወጧቸው፡፡ ዘለቀ የዚያን ዕለት ሁኔታ ሲናገር፤ በረሃው ላይ አስቁመውን ቢሆን ኖሮ መጥፎ ይሆን ነበር ብሏል፡፡
የዘረኝነት በደል በዚህ ብቻ አላቆመም፡፡ በሚኖሩባት ቺካጎ ከተማም አልቀረላቸውም፡፡ ከሚሰሩበት ክበብ ጀርባ ሀብታም ዘረኛ ነጮች ቤት ገዝተው ገቡ፡፡ ከዚያ ሊያባርሯቸው ስለፈለጉ፣ “የክለቡ ድምፅ ይጮሃል፣ ረበሸን፣ ፀጥታ አጥተናል፣” … እያሉ ብዙ ጊዜ ሊያስወጧቸው ሞከሩ። “ጉዳዩ የድምፅ ብክለት ሳይሆን ዘረኝነት ነው” በማለት ለማዘጋጀት ቤት አመለከቱ፡፡ ማዘጋጃ ቤቱ በህጉ መሰረት “በመኖሪያ አካባቢ ድምፅ ማስጮህ አትችሉም አላቸው፡፡
ስደተኞች “አሜሪካን ድሪም” የሚባል ነገር አላቸው፡፡ ሁሉም ሰው በስደት አሜሪካ ሲገባ፣ እንዲህ አድርጌ፣ እንዲህ ሰርቼ፣ እንዲህ ሆኜ … የሚለው ህልም አለው፡፡ የባንዱ አባላትም ሕልም ነበራቸው፡፡ እናም ትልልቆቹ የጥቁሮች መብት ተከራካሪዎች እነ ጄሲ ጃክሰን ወዳሉበት ሄደው፣ “ሙዚቃ መጫወትና ታዋቂ መሆን የአሜሪካ ህልማችን ነው፡፡ እነዚህ ዘረኞች ህልማችንን እውን እንዳናደርግ ቤታችንን ሊያዘጉብን ነው” ብለው ነገሩ፡፡
የከተማዋ ገዥ የዴሞክራት ፓርቲ አባል ናቸው፡፡ እነ ጄሲ ጃክሰን ለምን የፑሽ (PUSH) ኮሚቴ ሆናችሁ አታገለግሉም? አሏቸው፡፡ ለምን? ሲሉ ጠየቁ፡፡ እናንተ ተማሪ ናችሁ፡፡ ለምን በዚህ አጋጣሚ ስለ አሜሪካ ፖለቲካ፣ ስለ ዴሞክራሲ አትማሩም? አሏቸውና የምርጫ አቀነባባሪ ሆነው አረፉት፡፡ በዚህ ሁኔታ ወደ ፖለቲካ ገቡና የአሜሪካ ፖለቲካ እንዴት እንደሚሰራ ጠንቅቀው አወቁ፡፡
አርቲስት ዘለቀ ገሠሠ፤ በአሜሪካ ከሚጫወተው ሙዚቃና በግሉ ከሚሰራው ቢዝነስ በተጨማሪ በበጎ አድራጎት ተግባርም የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ አገልግሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቺካጎ ውስጥ ብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የያዘ ኢትዮጵያን ኮሙኒቲ አሶሴሽን አለ፡፡ ይህን ድርጅት ዶ/ር እርቁ ይመር ሲያቋቁሙ፣ ዘለቀና ዶ/ር አብርሃም ደሞዝ ከመስራቾቹ አንዱ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቺካጎ ሲደርሱ ስለ አገሩ ስለማያውቁ ብዙ ይቸገራሉ፣ ግራ ይገባቸዋል፡፡ ስለዚህ ማኅበሩ አገር ያሳውቃል፣ መታወቂያ ካርድ፣ መንጃ ፈቃድ እንዴት እንደሚወጣ፣ የት መ/ቤት ማመልከት እንዳለባቸው … ይረዳቸዋል፡፡
አርቲስቱ ከኢትዮጵያ ከወጣ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አገሩን የረገጠው ከ17 ዓመት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ በአድዋ 100ኛ ዓመት ክብረ በዓል ወቅት ነው፡፡ ያኔ ኢትዮጵያን ተዟዙሮ ጎበኛት፡፡ በወቅቱ እንዳሁኑ ትምህርት በየገጠር ከተማውና መንደሮች አልተዳረሰም ነበር፡፡ በደረሰበት ሁሉ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናትና ወጣቶች ጊዜያቸውን በአልባሌ ሁኔታ እንደሚያሳልፉ ተመለከተ፡፡
ወደሚኖርበት አሜሪካ ሲመለስ፣ ያየውን ነገር ሁሉ ለዚጊ ማርሌ ነገረው፡፡ ኢትዮጵያን  እንዴት እንርዳ? በየዘፈኖቻችን ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እንላለን፡፡ ኢትዮጵያን ለመርዳት ምን እናድርግ? በማለት አማከረው፡፡ ዚጊም ጥናት አድርግ አለው።
ዘለቀ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ትምህርት ያልተዳረሰባቸው አካባቢዎች የት የት ናቸው በማለት የአፍሪካ ህብረት (ያኔ የአፍሪካ አንድት ድርጅት) ዩኒሴፍና ዩኔስኮን አነጋገረ፡፡ ድርጅቶቹም ትክክለኛውን መረጃ ሰጡት፡፡ አብዛኞቹ ገጠር ናቸው - ሩቅ ገጠር፡፡ መረጃውን ይዞ ተመለሰና ዘለቀ ገሠሠ፣ ዚጊ ማርሌና አዲስ ገሠሠ ሆነው ዋን ላቭ አፍሪካ (One Love Africa) የተሰኘ ድርጅት በ1992 ዓ.ም በኢትዮጵያ አቋቋሙ፡፡ የቦርድ ኮሚቴ አባላትም መሠረቱ፡፡
ከቦርድ አባላት አንዱ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩን የመረጠው እንዲመሯቸው ነው፡፡ በነጆ - ወለጋ የተወለዱት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ እንደተመረቁ (በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመን) ወደ አገራቸው ተመልሰው “ፊደል ሰራዊት” መስርተው “የተማሩ ያስተምሩ” እያሉ በኩምቢ ቮክስዋገን እየዞሩ ይቀሰቅሱ እንደነበር ዘለቀ ያውቃል፡፡ ነገሮችን መንገድ ያስያዙላቸው በሂውስተን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ኤፍሬም መሆናቸውን ዘለቀ ይናገራል፡፡ አሜሪካ እያለ ከሙዚቃና ከግል ቢዝነሱ በተጨማሪ ዋን ላቭ አፍሪካን በኃላፊነት እየመራ ቆይቷል፡፡
በፈረንጆች ሚሊኒየም (ከዛሬ 15 ዓመት በፊት) በደቡብ ክልል በሲዳማ ዞንና በቦረና ዞን 10 ት/ቤቶች ከፈቱ። ት/ቤቶቹን የሚከፍቱት ከመንግሥት ጋር ተነጋግረውና ተፈራርመው ነው፡፡ ት/ቤቱ ከማኅበረሰቡ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ማህበረሰቡ ለት/ቤቱ መስሪያ መሬት ይሰጣል፣ እንጨት፣ ድንጋይ፣ ለክዳን ሳራ፣ … ያቀርባል። ከማኅበረሰቡ ውስጥ የተማሩና ሥራ የሌላቸው ተመርጠውና ሰልጥነው በመምህርነት ይቀጠራሉ፡፡ ዋን ላቭ አፍሪካ ለ4 ዓመት በሴቭ ዘ ችልድረን ዩኤስኤ በኩል አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ እነዘለቀ ገንዘቡን ከአሜሪካ ለጋሽ ድርጅቶች ለምነው ለሴቭ ዘ ችልድረን ዩኤስኤ ይሰጣሉ፡፡ ወጪ የሚያደርገውና ሂሳቡን የሚቆጣጠረው ዩኤስኤይድ ነው፡፡
ት/ቤቱቹ በየአካባቢያቸው ከፍተኛ ለውጥ አምጥተዋል። ዘለቀ፣ ከ4 ዓመት በኋላ በ2004 (እኤአ) ት/ቤቶቹ ያሉበትን ሁኔታ ለማየት ድጋፍ ያደረጉላቸውን ድርጅቶች ይዞ መጥቶ ነበር፡፡ እጅግ የሚገርም ነገር ነው ያዩት፡፡ በሲዳማ ዞን ከይርጋዓለም ከተማ 70 ኪ.ሜ ገባ ብሎ ያሉት የማደኖ ማኅበረሰቦች፣ ያደረጉትን ማመን ነው ያቃታቸው፡፡ “ልጆቻችን 4ኛ ክፍል ከጨረሱ በኋላ ለመቀጠል 2 ሰዓት የእግር ጉዞ ሊያደርጉ ነው፡፡ በተለይ ሴቶቹ ዕድሜያቸው ከፍ ስላለ ከቤተሰብ ርቆ መሄድ ችግር አለው፡፡ ስለዚህ እኛ ሁለት መማሪያ ክፍል ሰራን፡፡ እናንተ ደግሞ ቀሪውን አስፈላጊ ነገር አሟሉልንና እስከ 6ኛ እዚሁ ይማሩ” በማለት ጠየቁ፡፡ የፈለጉት ነገር ተሟላላቸው፡፡
በቀጣይ የታቀደው ፕሮግራም ሸዋ ውስጥ ነው። ፕሮፖዛል አዘጋጅቶ ለለጋሽ ድርጅቶች አቅርቦ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ፣ ከአዲስ አበባ ዙሪያ ወጣ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች በቦሌ ወረዳ፣ በውንጪ፣ በፍቼ፣ በአቃቂ … ሌሎች 10 ት/ቤቶች ሰርተዋል፡፡ እነዚህን ት/ቤቶች ሲጎበኙ ማኅበረሰቡ ክፍሎች እየሰራ የጎደለውን አሟሉልን እያለ ይጠይቃቸዋል፡፡ እነሱም ያሟላሉ፡፡ ሌሎች 10 ት/ቤቶች የተሰሩት ደግሞ ጎንደር ውስጥ በደንቢያ ወረዳ ነው፡፡ በአጠቃላይ 30 ት/ቤቶች ተሰርተው በመንግሥት ሲስተም ውሰጥ እንዲገቡ ተደርገዋል፡፡
ዋን ላቭ አፍሪካ ያደረገው ት/ቤት መገንባት ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች ተግባራትም አሉ፡፡ አርቲስቱ ሸዋ ውስጥ ያሉ ት/ቤቶችን ሲጎበኝ አንድ ነገር ተገነዘበ፡፡ ት/ቤቶቹ የተሰሩበት አካባቢ ውሃ የለም፡፡ ሴት ተማሪዎች ወደ ት/ቤት የሚመጡት ዘግይተው ከመሆኑም በላይ ደክመው ስለሚደርሱ የትምህርት አቀባበላቸው ደካማ መሆኑን ዳይሬክተሮቹ ነገሩት፡፡ ፕሮፖዛል አዘጋጅቶ የገንዘብ ድጋፍ ለሚያደርጉለት ለጋሾች አቀረበ፡፡ ለጋሾች ም ፊት አልነሱትም። ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ከ10ሩ ት/ቤቶች 7ቱ የውሃ ጉድጓድና ፓምፕ አላቸው፡፡
ት/ቤቶቹ ያሉበትን ሁኔታ ፊልም ቀርፆ ተመለሰ፡፡ ከዚያም ትልቅ ዝግጅት አድርጎ ቺካጎ በሚገኘው ክለባቸው ያንን ፊልም አሳየ፡፡ ፊልሙን የተመለከተ አንድ ድርጅት “እኔ ለት/ቤቶቹ ኮምፒዩተር እችላለሁ” ማለቱን ዘለቀ ገልጿል፡፡ የኮምፒዩተሩ ጥያቄ መነሻ አለው፡፡ ሲዳማ ውስጥ ያሉትን ት/ቤቶች ሲጎበኝ፣ አንዲት ትንሽ ልጅ “ኮምፒዩተር እፈልጋሁ” አለችው፡፡ ያነሳውን ፊልም ለፈረንጆቹ ሲያሳይ ልባቸው በጣም ተነካ፡፡
ስለዚህ “ዋን ላፕቶፕ ፎር ኢች ቻይልድ” በሚለው ፕሮግራም መሰረት፣ ከ6 ዓመት በፊት ዋጋቸው ሩብ ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ 1,000 ላፕ ቶፖች ገዝተው ለ16 ት/ቤቶች አከፋፈሉ፡፡ 30ዎቹ ት/ቤቶች በየዓመቱ 15,000 ተማሪዎች ያስተናግዳሉ፡፡ መጀመሪያ ትምህርት የጀመሩት በአሁኑ ወቅት ኮሌጅ መድረሳቸውን ዘለቀ ተናግሯል፡፡ አርቲስት ዘለቀ ከግራሚ ሽልማቱና ከወርቅ ሬከርዱ በላይ ትልቅ እርካታ የሚሰጠው፣ ወገኖቹ ከድንቁርና ጭለማ ወጥተው የእውቀት ብርሃን እንዲያዩ ማድረጉ ነው፡፡ ከ7 ወይም 8 ዓመት በፊት በወንጪ አካባቢ የተሰራውን ት/ቤት ሲጎበኙ ያየው ነገር ከምንም በላይ እጅግ የላቀ እርካታ እንዲሰማው አድርጎታል። ለካንስ ወጣቶቹ አባቶቻቸውንና አረጋዊያን አያቶቻቸውን ፊደል ለይተው እንዲያውቁና ገጣጥመው እንዲያነብቡ አስተምረዋቸዋል፡፡
አንድ የ80 ዓመት አዛውንት ተነስተው “በጠቅላላው እንኳን ሰው እግዜርም ረስቶናል ያልነውን ቦታ እናንተ ት/ቤት ከሰራችሁ በኋላ ልጆቻችን ተማሩ፤ እኔ ሽማግሌው እንኳ ማንበብ ቻልኩ” በማለት ከፍ - ዝቅ፣ ራቅ - ቀረብ እያደረጉ፣ በደከመ ዓይናቸው በግድ ሲያነብቡ፣ እሱና አብረውት የነበሩት የደስታ ሲቃ ከውስጣቸው ፈንቅሎ ማልቀሳቸውን መቼም እንደማይዘነጋው ተናግሯል፡፡
አርቲስቱ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ የተለያዩ ቢዝነሶች ጀምሯል፡፡ አጀማመሩ ታዲያ በችኮላ አይደለም። ቀስ እያለ በማጥናት ነው፡፡ በአያት አካባቢ እየተሠራ ያለው ባለ 2 ፎቅ መኖሪያ ቤት በ18 ወሮች እንደሚጠናቀቅ ተገምቷል፡፡ የአያቱ ሲጠናቀቅ ቦሌ አካባቢ የእንግዳ ማረፊያ ለመሥራት ዲዛይኑ አልቋል፡፡ በሽርክና የተገዙ ቢሆንም የሚከራዩ የግንባታ ማሽነሪዎች አሉት፡፡
ዘለቀ፣ ከቺካጐ ሲለቅ ክለቡን አዲስ አበባ ልወስደው ነው ያለው ከአንጀቱ ባይሆንም አሁን ግን አዲስ አበባ ከአምስትና ከሰባት ሺህ በላይ እንግዶች እያስተናገደች ስለሆነ ሰፊ መዝናኛ እንደሚያስፈልጋት አምኗል፡፡ ለመዝናኛው ግንባታ ሰፊ ቦታና ትልቅ ካፒታል የሚጠይቅ ስለሆነ ከመንግሥትና ከፋይናንሰሮች ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ገልጿል፡፡
አርቲስት ዘለቀ አሜሪካ የሚኖሩ ሦስት ልጆች አሉት። ትልቁ ልጅ ትምህርቱን ጨርሶ ሆሊዉድ ውስጥ ፊልም እየሠራ ነው፡፡ በቅርቡ ልጅ ወልዶ አባቱን አያት አድርጓል። ሴቷ ልጅ በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በሂዩማን ራይት ሎው ማስተርሷን እየተማረች ሲሆን በዚህ ዓመት (2015) ትመረቃለች። የመጨረሻው ልጅ በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፍሎሪዳ እየተማረ ሲሆን ከዓመት በኋላ ይመረቃል፡፡ ሎቢስት (ሕግ ሲወጣ የመንግሥትና የቢዝነስ ሰዎችን የሚያግባባ፣ የሚያቀራርብ) እሆናለሁ እያለ ስለሆነ ፖለቲከኛ የመሆን ፍላጐት ያለው ይመስላል ብሏል አባቱ - አርቲስት ዘለቀ ገሠሠ፡፡

Read 11175 times