Saturday, 04 February 2012 12:04

“በአብዮት የሚመራ ዲሞክራሲ፣ አብዮታዊ እርምጃ ከመውሰድ አይመለስም” እያሉ ማማት ምን ይሠራል?

Written by  ናርዶስ ጂ
Rate this item
(1 Vote)

ባለፈው ሳምንት፣ ከአቶ በረከት “የሁለት ምርጫዎች ወግ” መጽሐፍ ምረቃ ጀርባ “ሌላ ወግ መሰለቃችንን አውግቻችሁ ነበር፡፡ በተለይ፣ አቶ በረከት ለወዳጆቻቸው ምስጋና ሲያቀርቡ፣ የሸራተኑ ላሊበላ አዳራሽ በጭብጨባ መናጡን ተናግሬ ነው በቀጠሮ የተለያየነው፡፡ እንደተባለው በኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ (ወቅታዊ ሁኔታም ማለት ይቻላል) ኢትዮጵያዊያን በአንድ አዳራሽ ተገናኝተን የምናደርገው ጭብጨባ፣ አንድምታው ብዙ ነው፡፡ አንዳንዱ ጭብጨባ በኩራት ወጥሮ ያስተኛናል፤ አንዳንዱ ጭብጨባ በስጋት ቀብትቶ ያነቃናል፡፡ አንዳንዱ ጭብጨባ ከአንጀት ይንጣል፤ አንዳንዱ ጭብጨባ ከአንገት ይወልቃል፡፡ “ጭብጨባ” በኢትዮጵያዊኛ ወግ ልማድ ሲመነዘር አንድም “ስም ነው፣ አንድም “ወርቅ” ነው፡፡ በብዙ አዳራሽ በሚስተጋቡ ጭብጨባዎች ላይ የበሰለ የህይወት ልምድ ያካበቱ ኢትዮጵያውያን (“ብዙ” ማለት ምን ያህል ነው ብሎ ወጌን ያቆረፈደ ከሽብርተኛ ለይቼ አላየውም) እንደሚያስተነትኑት፣ “የሀበሻ ጭብጨባ” ቅኔ ነው፡፡ የጭብጨባውን ወርቅ ያወቀ በርግጥም የምር ሊያስጨበጭብ ይችላል” ብለናል፡፡

ለዚህ ነው፣ አቶ በረከት አቶ መለስን እና ብአዴንን በየተራ ሲያስመሰግኑ፣ የተለያየ የጭብጨባ መጠን የገጠማቸው፡፡ የብአዴኑ ሞቅ ይል እንደነበር አልደበቅኋችሁም፤ የብአዴኑ መድመቁን አስመልክተው፣ ይቀላለዱ የነበሩት ዘፋኞች ጭብጨባውን ማስተንተን ይዘዋል፡፡ እኔም፣ ፊቴን ወደ አዳራሹ አድርጐ እንደ ነጭ ለባሽ የጆሮዬን አንቴና ከአርቲስቶቹ ወግ ላይ ተከልኩ፡፡ የአማራ ልሂቃን፣ “ወሬ ሲበዛ እናቴ ባሪያ ናት ያሰኛል” እንደሚሉት፣ አርቲስቶቹ ሞቅታና ወሬ ሲደራ ሼህ መሐመድ አላሙዲንን ማማት ጀምረዋል፤ አይገርምም ጐበዝ! “ኢህአዴግና ሼህ መሐመድ ኮከባቸው አንድ ነው” እየተባለ ሲወራ አላምንም ነበር፤ እውነቴን ነው የምላችሁ… አሁን ግን አረጋግጥኩ፤ ሁለቱም ምንም ቢያደርጉ ከመታማት አይድኑም፤ እጃቸው አመድ አፋሽ ነው…

ታዲያ አሁን ማን ይሙት ሼሁ የወዳጃቸውን መጽሐፍ ሲያስመርቁ ቅልጥ ያለ ድግስ አዘጋጅተው ባበሉና ባጠጡ መታማት ነበረባቸው? እኔማ ጉድ ሊያሰማኝ አይደል ሸራተን የወሰደኝ! (ለነገሩ ምን ጉድ ሊያሰማኝ ብቻ ጉድ ሊያበላኝና ሊያጠጣኝ እንጂ በሕይወት ዘመኔ አይቼው የማላውቀውን፣ ቁርጥ እኮ ነው ያስቆረጥኩት…) ለካ የጭብጨባው ቅኔ፣ እሳቸው (ሼሁ) ነበሩ… ለነገሩ በገዛ እጃቸው ነው የታሙት፤ ሀበሻ “ቁርጥ” በውስኪ ካወራረደ መፈላሰፍ፣ ቅኔ መቀኘት እንደሚያበዛ እያወቁ እንዲህ አይነት ድግስ ማን ደግሱ አላቸው? አቶ በረከትም፣ መጽሐፋቸውን እንዲያሳትሙ እንጂ እንዲደግሱ ቀጭን ትዕዛዝ አላስተላለፉም…

ለማንኛውም ግን ታዳሚው የቀረበለትን እያሻመደ ወጉን ተያይዞታል፤ እኔም ትዝብቴን ቀጥያለሁ …ካጠገቤ ያሉት አርቲስቶቹ የጭብጨባውን ቅኔ፣ ወርቁን ማስተንተን ሲጀምሩ ሞቅታው የለቀቀኝ መሰለኝ… “ምን ነካችሁ? ሼሁ በእናታቸው እኮ ትግሬ ናቸው የአድዋ አካባቢ ተወላጅ” ሲል “በለው! ከየት ነው ቆርጠህ የምትቀጥለው!” የሚል ምላሽ ተከተለ፡፡ ካ! ካ! ካ! ሞቅ ያለ ሳቃቸው በሙሉ አዳራሹ ያስተጋባ መሰለኝ… “እውነትህን ነው …እንደዚህ ተብሎ ተወርቷል…? የወሎ ተወላጅ መሆናቸውን ነው የማውቀው” አንዱ ሳቁን ጋብ አድርጐ መረር አድርጐ ጠየቀ፡፡

አንዱ በሳቅ ታጅቦ፣ “ኧረ ወዳጄ…አጐቴ እንደነገረኝ ዘመዳችን ናቸው… ወልድያ አይደል እንዴ ተወልደው ያደጉት” በማለት ሲናገር፣ ሌላው “ወደየት ጠጋ ጠጋ” አለ፡፡ ሁሉም በሳቅ ተንከተከቱ…እኔስ ብሆን ነገር የሚገባኝ በፍልጥ አይደለ… ለብአዴን ምስጋና ጊዜ ጭብጨባው ሞቅ ያለው ለካ፣ የሼሁን አማራነት ለማጽናት ኑሯል ውይውይ ውይ አይ እኛ ጮማ ያስቆረጠንን ባለፀጋ ማማት ነበረብን ጮማ ያስቆረጠን እኮ አማራ ወይም ትግሬ መሆናቸው አይደለም፤ ባለፀጋነታቸው እንጂ! ለነገሩ የጐሣ ተኮር ፖለቲካ ትርፉ ይኸው አይደል ልል አልኩና “ውሻ በበላበት ይጮሃል” እንዲሉ፣ ጮማቸውን ቆርጬ፣ በእጃቸው በልቼ፣ ሲያሟቸው እየሰማሁ ዝም ማለት አልቻልኩም፤ ባይሆን ዘወር ብዬ ሼሁን አያቸው ዘንድ ልቤ ፈቀደ፣ (“ሼሁን በቅርብ እርቀት የማያቸው እኔ ማን ነኝ? ብዬ በትሁትነት እራሴን ጠየቅኩ) በዚህ ጊዜ ግን ሰበር ዜና የሚሆን አጋጣሚ አየሁ፡፡ ጋዜጠኛ ስላልሆንኩ፣ ሰበር ዜናውን ትቼ “ሰበር ወጉን” ላውራችሁ፡፡

አንድ ታዋቂ የሃገራችን ዘፋኝ፣ ከአንድ የክልል ፕሬዝዳንት ጋር ቆሞ ሲያወጋ፣ አንድ ፎቶ አንሺ (ካሜራ ማን) ሲያነሳቸው ተመለከተ፡፡ ወጉን አቋርጦ ወደ ፎቶ አንሺው ገሰገሰ፡፡  ወዲያው እጁን ይዞ፣ “ያነሳኸውን ፎቶግራፍ ሠርዝ” በማለት በሀይል ሙግት ጀመረ፡፡ የዘፋኙ ስሜታዊነት ያበሳጨው ፎቶ አንሺ “የማንሳት ፈቃድ ያለኝ ባለሙያ ነኝ” እያለ ተከራከረ፤ ሞቅ ያለ ጭቅጭቅ ውስጥ ገቡ፡፡ ታዋቂው ወጣት ዘፋኝ ሀይል በተቀላቀለበት ሁኔታ፣ “ሰማህ አናትክን በሽጉጥ ስልህ ታጠፋዋለህ” ሲለው በጆሮዬ በብረቱ ሰማሁ፡፡ ፎቶ አንሺውም መንጭቆት፣ “አትችልም እሺ” እያለ በንዴት ጦፈ፡፡ ዘፋኙ እየተከተለው፣ “ያነሳኸውን ፎቶ ታጠፋዋለህ እሺ!” ካለበለዚያ በሽጉጥ ስልህ ታጠፋዋለህ… ዘፋኝ ስለሆንኩ ፈርቼ የምተውህ መሰለህ” በማለት አምባረቀ…

“ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠበባም” አሉ፡፡ የዘፋኙ ዛቻ አበሳጨኝ፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው አቶ በረከትንና ሼህ መሀመድን ጨምሮ የሀገሪቱ ታላላቅ ባለሥልጣኖች ከተቀመጡበት ከ5 ሜትር ባልበለጠ ርቀት ነው፡፡ እኔ የሰጋሁት በግርግር፣ እወደድ ያሉ የሼሁም ሆነ የባለሥልጣናቱ ጠባቂዎች በጮማ ጥድፊያ ያለሁትን ሰው በጫማ ጥፊ እያሉ እንዳያስወጡኝ ነበር፡፡ የዘፋኙ ጓደኛ (ሌላ ታዋቂ ዘፋኝ) ነገሩን ለማብረድ ይሯሯጣል፡፡ አንድ ሁለት ጋዜጠኞችም ሊያረጓጓቸው እየሞከሩ ነው፡፡ የዘፋኙ ጓደኛ “ጥፋቱ የዘፋኙ እንጂ ካሜራ ማኑ ምንም አላደረገም …እዚህ ቦታ ላይ ተገኝተን ፎቶ አታንሱን ማለት አንችልም” በማለት ጓደኛውን እየተቆጣ ፎቶ አንሺውን ለማጽናናትና ለማስታረቅ ጣረ…

በኋላ ፎቶ አንሺውና ዘፋኙ ታረቁ፤ ከሽማግሌዎቹ ራቅ ብለው ተቃቅፈው የሆድ የሆዳቸውን አወጉ፡፡ አሁን ፎቶ አንሺው ንዴቱ በረድ እያለለት ነው፡፡ ዘፋኙም በይፋ ይቅርታ ጠየቀውና ዘፋኙ፣ ለዚህ ሁሉ ነገር የበቃበትን ምክንያት ሰማን፡፡ በአንድ ወቅት ይህ ታዋቂ ዘፋኝ፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪ ጋር ቆሞ ሲያወራ ያነሱትን ፎቶ፣ በተለያዩ ድረገጾች ላይ እንለቅብሃለን በማለት አስፈራርተው በርከት ያለ ገንዘብ የተቀበሉት ሰዎች (ምን ሰዎች “አሸባሪዎች” እንጂ) ነበሩ፡፡ ለካ ያለ ነገር እንደዛ በሽጉጥ እየማለ አልተወራጨም፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ…የደረሰበትን በደል ስሰማና እራሱን አረጋግቶ በጥሩ ትህትና ይቅርታ ማለቱ ሳይ፣ ስሙን ማንሳትና ማሳጣት አልፈለኩም፡፡ ግን የፈለገ ቢናደዱ ያውም የሃገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ባሉበትና ከዓለማችን ባለፀጐች አንዱ በሆኑት ሰው ድግስ ላይ (በምስክር ፊት) በሽጉጥ ማስፈራራት ተገቢ አይደለም ብዬ ለመምከር ፈለግሁና “እኔ ብሎ መካሪ” ብዬ እነሆ ተውኩት…

ወዳጆቼ! በሉ የሀበሻ ጭብጨባ አያዘናጋን! አሁንም እኔ ያለሁት ሸራተን ላሊበላ አዳራሽ ውስጥ ነው፡፡ የአቶ በረከት መጽሐፍን መሃሉን ገልጬ የቅናት ንባቤን ቀጥያለሁ፤ ብዙ ታዋቂ ሰዎች ደግሞ ዙሪያዬን ከበውኛል፡፡ በርግጥ “ከበውኛል” ማለት ይከብዳል፤ ባይሆን በዙሪያቸው ጠርዝ ላይ እራሴው ሄጄ ቆሜያለሁ ብል ይሻላል እንጂ…

አይ የኔ ነገር…ደግነቱ ሀቁን ፍርጥ ነው የማደርገው፡፡ እናም እላችኋለሁ… ከሁሉም አይቅርብኝ ብዬ፣ ከቢራውም፣ ከወይኑም እያነሳው እጨልጣለሁ፡፡

እርግጥ ነው የሞቅታን ቀይ መስመር ዘልያለሁ፡እኔ ደግሞ በ”ተፈጥሮዬ” ሞቅ ሲለኝ የማንበብ ልማዴ ይነሳል፤ “በሣል አንባቢ ነው” ይሉኛል፡፡ ለዚህ ነው፣ “የሁለት ምርጫዎች ወግ”ን ከሚመረቅበት አዳራሽ ሳልወጣ መሃል ላይ ማንበብ የጀመርኩት፤ “ዶ/ር በየነና ዶ/ር መረራ “የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም” የሚለው የአማርኛ ምሣሌ በአስራ አንደኛው ሰዓት የገባቸው መሆኑን ለማረጋገጥ ህገመንግስታዊ ድንጋጌውን የማክበር ብቻ ሳይሆን የማስከበር ግዴታም እንቀበላለን አሉ” (ገጽ 187) የሚለውን ቀድሜ አነበብኩት፡፡ “ምን ማለት ነው?” ገልብጬ ይሆን እንዴ ያነበብኩት? ብዬ ተወዛገብኩ - ደግሜ ሳነበው ግን ልክ ነው፡፡

ፐ! እንዴት ነው ነገሩ ጐበዝ! ሦስት ዲግሪ ያላቸው ታላላቅ ምሁራን፣ “የአበራሽን ጠባሳ” የሚለውን አንዲት ቅንጣት የአማርኛ ምሣሌያዊ አነጋገር ለመረዳት፣ እንዴት? “አስራ አንደኛው ሰዓት” ድረስ ይቆያሉ? ይሄ ነገር የታይፕ ስህተት ያለው መሰለኝ አልኩ፡፡ ምክንያቱም፣ እንኳን ሶስት ዲግሪ ያለው ቀርቶ እንደኔ አንድ ዲግሪ የተሰጠው እንኳን፣ አንድ የአማርኛን ምሣሌ ለመረዳት አስራ አንድ ደቂቃ የሚበቃው ይመስለኛል…እንዴት የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች እቺ ሁልጊዜ የምንጠቅሳትን “ጠባሳዋን አበራሽ” ማወቅ ይሳናቸዋል?...

እውነቴን ነው የምላችሁ…እኔ ፖለቲካ ስለማይገባኝ እንጂ፣ አቶ በረከት፣ እነ ፕሮፌሰር በየነ አንዲት የአማርኛ ምሣሌ ያውም የአበራሽ ጠባሳ ይጠፋቸዋል ብለው እንዳልተዘባበቱ ገባኝ…እናም እቺ አንድ መስመር የፖለቲካ ጽሑፍ እራሴን አዞረችው፤ ወደ አዳራሹ ጠርዝ አመራሁና ግድግዳ ተደግፌ ቢራዬን እየተጐነጨሁ “ፖለቲካ ሥላልገባኝ” ተክዤ ዝም አልኩ፡፡ ለካ ዝም ብዬ ነው የምጨናነቀው፤ ፖለቲካ የማይገባኝ እኔ ብቻ አልነበርኩም፤ ታላቁ ባለሀብት ሼህ ሙሐመድ አልአሙዲንም፣ “እኔ ፖለቲካ አይገባኝም…” ሲሉ በጆሮዬ በብረቱ ሰማኋቸው፡፡ ተስፋ መቁረጤን ትቼ ተጽናናሁ፡፡

ለካ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አልገባ የሚለው ለእኔ ቢጤው መናጢ ደሀ ብቻ አይደለም፤ ለሼህ አላሙዲንም ጭምር እንጂ! እኔም ባለፀጋው ሼህም አልገባን ካለ ችግሩ የእኛ ሳይሆን የሀገሪቱ ፖለቲካ ይሆናል! “አብዮታዊ ዲሞክራሲ”ን ለማለት ግን አይደለም፡፡ ጐመን በጤና እናቴ! (ችግሩ ጐመንስ የት ይገኛል) “በአብዮት የሚመራ ዲሞክራሲ፣ አብዮታዊ እርምጃ ከመውሰድ አይመለስም” እያሉ ሲያሙ ሰምቻለሁና!

 

 

Read 2592 times Last modified on Saturday, 04 February 2012 12:07