Print this page
Saturday, 08 August 2015 09:33

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(16 votes)

 ላንቺ
(በ.ሥ)
እንዳገው ጃንጥላ፤ ሰማይ ተሽከርክሮ
እንደ ጎፋ ፈረስ፤ መሬቱ ደንብሮ
ሁሉ ሲያዳልጠኝ
ሁሉ ሲያዳክመኝ
ቀሚስሽን ይዤ፤ መትረፌ ገረመኝ፡፡

ኤልሻዳይ ምኞት
(በ.ሥ)
እንደ ድሮ ቀሚስ፤ መሬት እየጠረግሁ
ኮቴሽን ምድር ላይ፤ ተግቸ እየፈለግሁ
እንደ ጉም
ሳዘግም
እንደ ሰርዶ ስሳብ
ባካል ብታመልጭኝ፤ ደረስኩብሽ ባሳብ
መች ሊያግደኝ በሩ፤ መች ሊገታኝ መስኮት
በዝግ በርሽ ገባሁ፤ ልክ እንደ መለኮት
ላንዲት መስቲካ ሻጭ ህጻን
(በ.ሥ)
በደብተርሽ ምትክ
ትንሽ ሱቅ ታቅፈሽ
ካልፎሂያጅ እግር ስር፤ እንደ ድንቢጥ ከንፈሽ
ጋሼ ግዙኝ ስትይ፤ ኣንጋጠሽ ወደ ላይ
ለጉድ ተጎልቸ፤ ምታረጊውን ሳይ
ራሴስ ይታመም፤ ምላሴን ምን ነካው
ግራዋ ይመስል፤ መረረኝ ማስቲካው፡፡
ኣፈር ጠጠር ለብሶ፤ በዶዘር ተድጦ
መስኩ ከነጎርፉ
ሰማይ ከነዶፉ
ለጌቶች ተሽጦ
ኣተር ነው እያሉ፤ ኣፈር ዘግኖ መፍጨት
ገነት ነው እያሉ፤ መስክ ላይ መፈንጨት
ጠበል ነው እያሉ፤ ተጎርፉ መራጨት
ይህንን ማን ሰጦሽ
ገና በልጅነት፤ ልጅነት ኣምልጦሽ፡፡
በምቢልታ በዋሽንት፤ በከበሮ ታጥሮ
በክራር ተማግሮ
በቆመ ከተማ
እምባሽ ቅኝት የለው፤ ለሰው ኣይሰማ፡
ጠዋት የፎከረ፤ ቀትር ላይ ሲረታ
ዛሬ ዝሎ ሲወድቅ፤ ትናንት የበረታ
ኑሮን ያህል ሸክም፤ ያላንቀልባ ሲያዝል፡፡
ምን ጸጋ ለብሶ ነው፤ ትከሻሽ የማይዝል፡፡

Read 4849 times
Administrator

Latest from Administrator