Saturday, 08 August 2015 09:29

“የሴም ወርቅ” በአዲስ አበባ ሲኒማ ቤቶች እየታየ ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በዳንኤል ተገኝ ተደርሶ በአለምፀሐይ በቀለ ዳይሬክት የተደረገውና በዳኒሮጐ ማስታወቂያና ፊልም ፕሮዳክሽን የቀረበው “የሴም ወርቅ” የተሰኘ ፊልም ባለፈው ሰኞ ምሽት በቀይ ምንጣፍ ሥነስርዓት ተመረቀ፡፡
የ1፡45 ደቂቃ ርዝማኔ ያለውን ፊልም ሰርቶ ለማጠናቀቅ 2 ዓመት ያህል የፈጀ ሲሆን 1.5 ሚ. ብር እንደወጣበት አዘጋጆቹ ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ልብ አንጠልጣይ የቤተሰብ የፍቅር ፊልም ላይ አርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም፣ አምለሰት ሙጬ፣ ዳንኤል ተገኝ፣ ሙሉ ሰለሞን፣ ዝናህብዙ ፀጋዬ እና ሌሎች አንጋፋና ወጣት ተዋንያን ተሳትፈውበታል ተብሏል፡፡
በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ አቶ አሚን አብዱል ቃድርን ጨምሮ አርቲስት አበበ ተስፋዬ (ፋዘር) እና ሌሎችም ታዋቂ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን ሚኒስትሩ ፊልሙን ከተመለከቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት፤“በጣም ደረጃውን የጠበቀ የአገራችንን ገፅታ የሚያሳይ ፊልም ነው” ሲሉ ማድነቃቸውን አዘጋጆቹ ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
የፊልሙ 70 ከመቶ ቀረጻ የተካሄደው በባህር ዳር እና ጎንደር ከተሞች ላይ ሲሆን ቀሪው አዲስ አበባ መቀረጹን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በፊልሙ ላይ ከዕውቅ ተዋናዮች ባሻገር የዳሽን ቢራ ሰራተኞችን ጨምሮ ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መሳተፋቸውን የጠቆመው የፊልሙ ደራሲና ፕሮዱዩሰር አርቲስት ዳንኤል ተገኝ፤ዳሽን ቢራ ለፊልሙ ከ1.3 ሚሊዮን ብር በላይ ስፖንሰር ማድረጉን ገልጿል፡፡
ዳሽን ቢራ ፊልሙ ለተመልካች እንዲበቃ ላደረገው ድጋፍ፣ታዋቂ አርቲስቶችና የውጭ ሃገር ዜጎች የተሳተፉበት ማስታወቂያ ሰርተው ለፋብሪካው በስጦታ ማበርከታቸውን አርቲስቱ ተናግሯል፡፡ ባለፈው ሰኞ በፊልሙ ምረቃ ላይ የታደሙ አንዳንድ ተመልካቾች፤ፊልሙ የዳሽን ማስታወቂያ ይመስላል የሚል ትችት የሰነዘሩ ሲሆን በብስጭት ፊልሙ ከመጠናቀቁ በፊት ጥለው የወጡ እንደነበሩም ለማወቅ ተችሏል፡፡ አርቲስት ዳንኤል፤ ስፖንሰር አድራጊውን የዳሽን ቢራ ፋብሪካን በፊልሙ ውስጥ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ለማስተዋወቅ መሞከሩን አልካደም፡፡ ነገር ግን መላ ፊልሙ የዳሽን ቢራ ማስታወቂያን ይመስላል የሚያሰኝ አይደለም ብሏል፡፡   
 #የሴም ወርቅ” በአዲስ አበባ በሚገኙ ሲኒማ ቤቶች በሙሉ በመታየት ላይ መሆኑን የጠቆሙት አዘጋጆቹ፤በባህር ዳር እና በጎንደር ባለፈው ረቡዕ እና ሐሙስ መመረቁን አክለው ገልጸዋል፡፡  

Read 2274 times