Saturday, 04 February 2012 12:01

የእስራኤሉ አምባሳደር ስለ ኢትዮጵያ ይናገራሉ

Written by  መልካሙ ተክሌ (melkamutekele@gmail.com)
Rate this item
(0 votes)

ኦዴድ ቤን - ሃየም በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ሆነው የመጡት በራሳቸው ፍላጐት ነው፡፡ አምባሳደሩ በሦስት ዓመታት ቆይታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የኢንቨስትመንት ችግሮች ስለ አንዱ የታዘቡትን ተናግረዋል፡፡የሦስት ልጆች አባት የሆኑት አምባሳደር አንደኛዋ ልጃቸው አንዲት ኢትዮጵያዊት ህፃን በጉዲፈቻ ማሳደግ ስለመፈለጓ እንዲሁም ስለ ቤተእስራኤላውያን የእስራኤል ኑሮ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ይዞታ ስለሆነው ዴርሱልጣን ገዳም፣ በጥምቀት ዋዜማ ጐንደር ላይ ላገኛቸው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መልካሙ ተክሌ ነግረውታል፡፡

ጐንደር እንዲመጡ ማን ጋበዘዎት? ወይስ በግልዎ መጡ?

በግሌ መምጣት ብፈልግም በዚህ ዝግጅት እንድገኝ የጋበዘኝ ግን የጐንደር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ነው፡፡ የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ ጌትነት አማረ የግብዣ ወረቀት ላኩልኝ፡፡ ከጐንደር ጋር የረዥም ጊዜ ግንኙነት አለን፡፡ እስራኤላውያን እዚህ መምጣት እንዳለባቸው አምናለሁ፡፡ ከክብር እንግዶቹ እኔ ብቸኛው “ፈረንጅ” ነኝ፡፡ ሌሎች ጥቂት እስራኤላውያን አይቻለሁ፡፡

ጐንደር ከእስራኤሏ ሪሻን ጽዮን ከተማ ጋር “የእህት ከተማ” ስምምነት አላት …

ሊሆን ይችላል፤ አላውቅም፡፡ ይኼ ማዘጋጃ ቤቶች በግል የሚያደርጉት ነው፡፡ በእስራኤል ልዩ የማዘጋጃ ቤቶች ድርጅት አለን፡፡ በቅርቡ ባህርዳር እና የእስራኤል ትልቅ ወደብ ከተማዋ አሸዶድ ተመሳሳይ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ እኛም ማሪታይም ኦፊሰሮችን በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ማሠልጠን ጀምረናል፡፡ ጣና ላይ ባህል ዘለቅ መርከቦች ባይኖሩም ማሪታይም ኦፊሰሮች ለማሰልጠን ጥሩ ቦታ ነው ባህርዳር፡፡

ኢትዮጵያን ተዘዋውረው አይተዋል?

ዓለምአቀፍ የትብብር ስምምነት በተለይ በግብርና ስላለን ብዙ ቦታዎች አይቻለሁ፡፡ እጅግ በጣም ያስደመመኝ ላሊበላ ነው፡፡ ላሊበላ መጀመሪያ እ.ኤ.አ በሴፕቴምበር 2008 በሄድኩበት ጊዜ ስምንተኛው የዓለም አስደናቂ ቅርስ መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ ብዙ ሰዎች ስለሱ አያውቁም፡፡ አሁን ብዙ እስራኤላውያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ላሊበላን በመጐብኘታቸው በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ መጀመሪያ የሚጐበኙት ላሊበላን ነው፡፡

ላሊበላ በአምሳለ ኢየሩሳሌም ነው የተሰራችው፡፡ ለእኔ በአይን የሚታየው የኢየሩሳሌም  አምሳያ ብቻ ሳይሆን ስለ ኢየሩሳሌም ያለው እሳቤ ቦታ ያለው ነው፡፡ እንደዚያማ ባይሆን ኢየሩሳሌም በሁላችንም ልብ ውስጥ አለች፡፡

ጐንደር በርካታ ቤተእስራኤላውያን መኖራቸው የተለየ ፍላጐት አያሳድርባችሁም?

ልነገርህ የምፈልገው ቤተእስራኤላውያን በሙሉ ቀድሞውኑ ከኢትዮጵያ ወጥተዋል፡፡ እስራኤልም ሄደዋል፡፡ ዛሬ በእስራኤል 120ሺህ ትውልደ ኢትዮጵያ እስራኤላውያን አሉን፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንድ ሦስተኛ ያህሉ ልጆች በእስራኤል የተወለዱ ናቸው፡፡ ወደ እስራኤል መጓዙ የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1970 እና 1971 አካባቢ ነው፡፡ ረጅም ሂደት ነው፡፡ አሁን ምንም ቤተእስራኤላውያን አልቀሩም፡፡

ቤተእስራኤላውያን ነን የሚሉ አሁንም አሉ በተለይ በዚህ በሰሜን ጐንደር?

ፈላሻሙራ ናቸው፤ ክብር ነክ ነው ቃሉ፡፡ ከውጪ የመጡ እንደምንለው ማለት ነው፡፡ ወደ ክርስትና የተቀየሩ ሕዝቦች ናቸው፤ ከአንድ መቶ ሃምሳ ዓመት በፊት ከእስራኤል እንደመጡ ይናገራሉ፡፡ ከነዚሁ ውስጥ የትኞቹ ከቤተአይሁድ መሆናቸውን እየወሰንን ነው፡፡ ይሁዳውያን ከሆኑ ክርስትያን ቢሆኑም ወደ እስራኤል የመሄድ መብት አላቸው፡፡

ስለነሱ ግን ብዙ ዜና ይሰማል?

ብዙ ዜና አይሰማም፡፡ የተለየ ዜና የለውም፡፡ እንደ እስራኤላውያን ኑሮ ይኼ የተለመደ ነው እንጂ ብዙ ዜና አይወጣውም፡፡ አንዳንዴ የሚገጥሙ ችግሮች ሲኖሩ በሰልፍ ይገልፁታል፡፡ የእስራኤልን ዜና ትከታተል ከሆነ የዘወትር ዜና ውስጥ ይኼ የለም፡፡

የኬኔሴት (ሸንጐ) ምክትል ሊቃነመናብርት መካከል አንዱ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ነው…

ልክ ነው፡፡ ከሰባት ምክትል ሊቃነመናብርት አንዱ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ እሳቸው ፖለቲከኛ ስለሆኑ ሁሌ ዜና ላይ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ለመመረጥ በቅድሚያ ፓርቲው ያጭሀል ከዚያ ሕዝቡ በድምፁ ያፀድቅልሀል፤ መታወቅ አለብህ፡፡ ለመታወቅ ደግሞ ዜና ላይ መኖር አለብህ፡፡ ዜና ላይ ካለህ ሁሉም ያውቅሃል፡፡ ማንነትህን ካወቁ ይመርጡሃል፡፡

በእስራኤል የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የዘረኝነት ተጠቂ ነን የሚል ቅሬታ አላቸው ይባላል…

የምነግርህ እስራዔል በስደተኞች የተገነባች ሀገር መሆኗን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ከመላ ዓለም የተሰበሰቡ ሕዝቦች መኖሪያ ነች፡፡ ከሞሮኮ፣ ከሩማኒያ፣ ከፖላንድ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከሩስያ፣ ከሌሎችም ቦታዎች መጥተዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ መጀመሪያ ሲመጡ ተመሳሳይ ችግር አለ ብለው ያማርራሉ፤ እስራኤላውያኑን፡፡ የኢትዮጵያውያንም እንደዚያው ነው፡፡ አዲስ ሲመጣ የአካባቢው ሕይወትን መለማመድ እስኪቻል ድረስ ማማረር በየትኛውም ዓለም የተለመደ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በ1980ዎቹና በ1990ዎቹ የመጡ ናቸው፡፡ የተለየ ሥርአተ ትምህርትና ኑሮ ነው ያለው፡፡ በእስራኤል የሚነገረው ቋንቋ እብራይስጥ ነው፡፡ እብራይስጥ መናገር ካልቻልክ ከሕዝቡ ጋር መግባባት አትችልም፡፡ ከኢትዮጵያ ስትሄድ ቋንቋው አዲስ ነው፡፡ ለአዋቂዎቹ ከባድ ነው፤ ሕፃናቱ ግን በቀላሉ መማር ይችላሉ፡፡ በእስራኤል ትምህርት ቤቶች በእብራይስጥ ይማራሉ፤ ኑሮውንም ይለምዳሉ፡፡ ውትድርናም ይሰለጥናሉ፡፡ በሌሎች መስሪያ ቤቶችም አሉ፡፡

ከነዚህ አንዷ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረባዬ የሆነችው በላይነሽ ናት፡፡ ሌሎችም በደቡብ አፍሪካና ሌሎች ኤምባሲዎቻችን የሚሰሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ስለዚህ ሕብረተሰቡ እየተለወጠ ነው፡፡ ፓይለቶች፣ የሠራዊት አዛዦች አሉ፡፡ እኔ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራዬን ስሰራ አንዳንዶች “ፈረንጅ” ሲሉኝ ምቾት አይሰማኝም፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ ከማስተማር ጋር ይያያዛል፡፡ አለመታደል ሆኖ ጠባብ አዕምሮ ያላቸው ዘረኞችም አሉ፡፡ ይህ በማንኛውም ዓለም አለ፤ በተለይ የተወሰኑ የሃይማኖት ቡድኖች፡፡ ሀበሻ ነኝ፤ መልኬ የተለየ ስለሆነ ግን መቀጣት የለብኝም፡፡ ሁላችንም ሕግ አውጪዎችን ጨምሮ እንዲህ አይነት ዘረኝነትን እንቃወማለን፡፡

በሁሉም ቦታ ቢከሰትም በእስራኤል ግን መሆን አልነበረበትም፡፡ ልጆቼ ግልጽ እንዲሆኑ አስተምሬአለሁ፡፡ የልጆች እናት የሆነችው አንደኛዋ ልጄ ኢትዮጵያዊት ህፃን በጉዲፈቻ ለማሳደግ እንድረዳት ትፈልጋለች፡፡ ይኼንን ለማድረግ እንደ አምባሳደርነት ሳይሆን እንደ አባትነት እያሰብኩበት ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ጋር ስላላችሁ ትብብሮች ይንገሩኝ…

ከኢትዮጵያ ጋር ብዙ የአቅም ግንባታ ስምምነቶች አሉን፡፡ አብዛኛው ስምምነት በግብርና በተለይም በመስኖ ልማት ነው፡፡ በአበባ እርሻም ስምምነት አለን፡፡ ልዩ ዝርያዎችን እናስገባለን፡፡ ከእርሻዎቹ አንዳንዶቹን ጐብኝቻለሁ፡፡ ገበሬዎች ፍራፍሬ ማምረታቸው በጣም ወሳኝ በመሆኑ በዚህ ዘርፍም እየሰራን ነው፡፡ የምግብ እጥረት በሚኖርበት ጊዜ ሊሸጡትና በምግብነት ሊጠቀሙበትም ይችላሉ፡፡

የባህል ትብብሮች ላይስ?

የዛሬ ሦስት ዓመት ትልቅ አውደርዕይ አካሂደናል፡፡ ከእስራኤል የባህል ቡድን መጥቶ ነበር፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ እዚህ ዝግጅት እንዲያቀርቡ አድርጌ ነበር ያኔ፡፡ የዛሬ ወር ደግሞ ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ወደ እስራኤል ልኬአለሁ፤ በጃዝ ቡድኖች የታገዙ፡፡ የተለያዩ ከያንያንም አሉበት፡፡ የባህል ልውውጡ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ፊልሞችም እናመጣለን፡፡

የእስራኤላውያን ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ምን ይመስላል?

ብዙ ኢንቨስትመንት በተለይ በአበባ ዘርፍ አለ፡፡ እስራኤላውያን ልምድና እውቀታቸውን እንዲሁም ሙዋዕለ ንዋይ ወደዚህ አምጥተዋል፡፡ አሁን የተለየ የኢንቨስትመንት አማራጭ በኢትዮጵያ እንዲኖር እሻለሁ፡፡ ኮንስትራክሽን፣ ቴሌኮሙኒኬሽን ሌላም የአቅም ግንባታ ዘርፍ ሊሆን ይችላል፡፡

እስራኤላውያን ባለሀብቶች ከኤምባሲው ጋር ሳይሆን ከመንግስት ጋር አብረው መሥራት አለባቸው፡፡ የኔ ሥራ እነዚህን ባለሀብቶችና ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ ነው፡፡ እያደረግን ያለነው በቂ አይደለም፡፡ ችግር ግን አለ፡፡ የእስራኤላውያን ብቻ ሳይሆን የሌሎች ሀገራት ባለሀብቶች ኢትዮጵያ መጥተው ሀብታቸውን ሥራ ላይ እንዳያውሉ ችግር አለ፡፡ ጨረታን አስመልክቶ እንቅፋቶች አሉ፡፡

ዛሬ እንኳን ከአንዲት ባለሀብት ጋር በስልክ ብዙ አውርተናል፡፡ በእርሻና በዶሮ እርባታ መሠማራት ትፈልጋለች፡፡ ኩባንያዋ ግን የማይታመኑ ማነቆዎች እዚህ ገጥመውታል፡፡ በሥጋ ምርት በዓለም የታወቀ አሜሪካዊ ኩባንያ አምስት ቢሊየን ዶላር ይዞ ከእስራኤል ኢንተርፕሪነሮች ጋር ኢትዮጵያ ላይ መሥራት ይፈልጋሉ፡፡ በኢትዮጵያ ላለፉት አምስት ዓመታት የሠሩትን መቀጠል ይፈልጋሉ፤ ኬንያዊ ባለሀብትን ጨምረው፡፡ በየቀኑ ግን አዲስ እንቅፋት ያጋጥማል፡፡

እንቅፋቱ ያለው የት ነው?

በአስተዳደሩ ታህታይ መዋቅር፡፡ በክልል ላይ ያለች አንዲት ሴት ሰነዱ ከኢትዮጵያ ኢንቨስተር አኳያ መከለስ አለበት ብላናለች፡፡ ይኼ እኮ ትልቁ የዓለም ዶሮ አርቢ ነው፡፡

ኩባንያው የራሱ ድርጅታዊ አሠራርና ምስጢር ሊኖረው ይችላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሳገኝ ስለነዚህ ጉዳዮች አወራቸዋለሁ፡፡ በበታች መዋቅር ያሉ የቀበሌ፣ የወረዳና ሌሎች ባለሥልጣናት ምን ማቅረብ እንዳለባቸው መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ ሊያደርጉ የሚችሉትን እያንዳንዱን ነገር ከሀ እስከ T መዘርዘር አለባቸው፡፡ ካሁን በፊት የነበሩ ባለሀብቶች ያልጠየቁትን አዲሶቹ ሲጠይቋቸው ማሟላት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እንጂ እኔ ወይም ባለሀብቶቹ አይደለንም የምንሠራው፡፡

የኩባንያው ሊቀመንበር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ሲወያዩ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጋብዘዋቸዋል፡፡ ውጤታማ ከሆነ ይኼ ለኢትዮትያ የተለየ ኢንቨስትመንት ይሆናል፡፡ ባለሀብቶች ሀብታቸውን በዚህ ኢንቨስት እንዲያደርጉ መበረታታት አለባቸው፡፡

በእስራኤል የሚገኘው ዴርሱልጣን ላይ ስላሉ ችግሮችና ውዝግቦች ምን ይላሉ?

በሚገባ አውቃለሁ፡፡ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰዎች ጋር ስለጉዳዩ አውርቻለሁ፡፡ ከፓትርያርኩ አቡነ ጳውሎስም ጋር ተነጋግረናል፡፡ ሁሉም እንደሚረዳው የእስራኤል መንግስት መፍትሔ ይሻል፡፡ ጥገናውን በራሳችን ወጪ ልናደርግ ወስነናል፡፡ ሆኖም በግብጽና በኢትዮጵያ አብያተክርስትያናት መካከል አለመግባባት አለ፡፡ በዚህ ጣልቃ አንገባም፡፡ ልናስገድዳቸውም አንችልም፡፡ የሰሞኑ ሁኔታ ምን እንደሆነ ባላውቅም በተሻለ አብሮ መሥራት ግን ይቻላል፡፡

እስቲ ስለ ራስዎ ይንገሩኝ…

ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት ከሦስት ዓመት ተኩል በፊት ነው፡፡ በኢትዮጵያ አምባሳደር መሆን እንደምፈልግ የተናገርኩት እኔው ነኝ፡፡ ጠየኩ፤ ከዚያ ተሾምኩ፡፡

የሁለቱ ሕዝቦች ግንኙት ሦስት ሺህ አመታት አስቆጥሯል፡፡ ኢትዮጵያውያንና እስራኤላውያን ምን ያህል እንደሚዋደዱም አውቃለሁ፡፡ ይህንን ለእስራኤላውያን ጓደኞቼና ዘመዶቼ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እነግራቸዋለሁ፡፡ በኢትዮጵያ አምባሳደር መሆኔንም በጣም ወድጄዋለሁ፡፡ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ወገኖችንም አይቻለሁ፡፡ ገበሬዎችም አነጋግሬአለሁ፡፡

ከታች ገጠር ካለው እላይ እስካለው ድረስ ሕዝቡ ምን ያህል እስራኤልን እንደሚወድ አረጋግጫለሁ፡፡ ማንኛውም ዲፕሎማት ሊያገለግል በሚሄድበት ቦታ እንዲህ እንዲገጥመው እመኛለሁ፡፡ ለኔ እጅግ በጣም ጥሩ ልምድ ነው፡፡ አምባሳደርነቴ ሲያበቃም የወደፊት ሕይወቴ ከኢትዮጵያ ጋር ይያያዛል ብዬ አምናለሁ፡፡

የጥምቀትን በዓል ከኢትዮጵያ ውጭ አይተዋል?

የለም በኢትዮጵያ ብቻ ነው የታደምኩት፡፡

ትውልደ ኢትዮጵያዊ እስራኤላውያን በኢትዮጵያ ኢንቨስት አድርገዋል?

እንዲያደርጉ ምኞቴ ነው፡፡ እነሱ እዚህ ቢመጡ ድልድይ ሆኑ ማለት ነው፡፡ የመዩ ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹ ግን ውጤታማ አልሆኑም፡፡ የአበባ እርሻው የሰመረለት አንድ ባለሀብት አለ፡፡ ሌሎችም እንዲመጡ እፈልጋለሁ፡

 

 

Read 3751 times Last modified on Saturday, 04 February 2012 12:04