Saturday, 08 August 2015 09:20

“…ዜብራውን ለምን ሠሩት?”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ከተማችን ውስጥ አንዳንድ ስፍራዎች አሉ …አለ አይደል…በአጠገባቸው ስታልፉ የእህል በረንዳ ጥራጥሬ ሁሉ ትከሻችሁ የተራገፈ የሚያስመስሉ ቦታዎች፡፡ በቃ… ምን አለፋችሁ…ካልጠፋ ‘ትውስታ’ ምንም በሌለበት ስፍራ ያያችሁት ሆረር ፊልም ሁሉ አእምሯችሁ ውስጥ በትልቅ ስክሪን በ‘ስሪ ዲ’  (ቂ…ቂ…ቂ…) መርመስመስ ይጀምራል፡፡
እናላችሁ… የሆኑ በአሥራዎቹ መጨረሻ አካባቢ ዕድሜ ያሉ ወጣቶች ከእንደዚሀ አይነት ስፍራዎች በአንዱ ማዶ እያለፉ ነበር፡፡ ከመሀል አንደኛቸው መንገዱን ሊሻገር ‘ዜብራው’ ውስጥ ይገባል፡፡ ይሄኔ አንዱ ጓደኛው… “አንተ ተመለስ! በእሱ በኩል ማለፍ አይቻልም…” ሲለው ደንገጥ ብሎ ወደኋላ ይመለሳል። ትንፋሹን ሰብሰብ አድርጎ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ታዲያ ዜብራውን ለምን ሠሩት?” አሪፍ አይደለች፡፡ በጦቢያችንም ሆነ በየትኛውም አገር ‘ዜብራ’ መስመሩ የሚያስተላልፈው መልእክት… “እግረኛ ሆይ፣ መሻገር የምትችለው በዚህ በኩል ብቻ ነው…” አይነት መልእክት ያለው ነው፡፡ ታዲያላችሁ…ልንሻገርበት የምንከለከል ከሆነ መጀመሪያውኑ ለምን ነጭ ቀለሙን ያባክኑታል!
እናላችሁ…ዘንድሮ  “ታዲያ ዜብራውን ለምን ሠሩት?” የሚያሰኙ መአት ነገሮች ናቸው፡፡
አንዳንድ ህንጻዎች ነገሬ ብላችሁልኛል! ‘ኤስካሌተር’ (አንዱ መዝገበ ቃላት ‘ተንቀሳቃሽ ደረጃ’ ይለዋል፣) አሠርተዋል፡፡ ግን አገልግሎት አይሰጡም፡፡ አንዳንድ ቦታ እንደውም በሆነ ነገር ዘግተውታል፡፡ “‘ኤስካሌተር’ ለጌጥ ብቻ የሚሠራባቸው አገራት ዝርዝር…”  አይነት የወጣ ጊዜ እንክት አድርገን ነው ‘ቶፕ ቴን’ ውስጥ የምንገባው፡፡ እና ይህን የመሰለ ቴክኖሎጂ አስገጥመው አገልግሎት አለመስጠት… አለ አይደል…ነገርዬው “ታዲያ ዜብራውን ለምን ሠሩት?” የሚያሰኝ ነው፡፡
የሆነ ምግብ ቤት ትገባላችሁ፡፡ ሜኑ ላይ ሠላሳ ምናምን ምግብ ተዘርዝሯል፡፡
“እሺ አንድ ስፓጌቲ…”
“ስፓጌቲ ዛሬ የለም…”
“እሺ፣ አሳ ጉላሽ ይሁንልኝ…”
“አሳ ጉላሽም የለም…”
ምን አለፋችሁ…ሜኑውን እያነበባችሁ ስትመርጡ ሁሉንም “እሱ ዛሬ የለም…” ይሏችኋል፡፡ የማይጠፉ ነገሮች ቢኖሩ እነኛው የፈረደባቸው የበግ ጥብስና በየአይነቱ ናቸው፡፡ እና ሠላሳ አይነት ምግብ “እሱ ዛሬ የለም…” በሚባልበት… ሠላሳ ምናምን አይነት ምግብ ሜኑ ላይ መደርደር ምን ማለት ነው! አለን ከሚሉት የምግብ አይነት መርጠንም “እሱ ዛሬ የለም…” የምንባል ከሆነ… አለ አይደል…ነገርዬው  “ታዲያ ዜብራውን ለምን ሠሩት?” ያሰኛል፡፡
የምግብ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ከዚህ በፊት አውርተናት ሊሆን ይችላል፡፡ ለአንድ ምግብ ከጠቅላይ ግምጃ ቤት ይወሰድ የነበረው የሦስት ወር ደሞዝ የሚጠየቅባቸው ቤቶች አሉ አይደል…እናላችሁ እሱዬው ‘ገርሉካውን’ ይዞ ይገባል፡፡ ሜኑ ይቀርብለታል፡፡ ዝርዝሩን ሲያነብ ይቆይና “በቃ እነዚህ ብቻ ናቸው፤ ሌላ የለም?” ይላል፡፡ ሜኑው እኮ ሁለት ገጽ ተኩል ጥቅጥቅ ያለ ነው!
አሳላፊውም በሆዱ “ድንቄም ተሸለለ!” ይልና “ይኸው ነው…” ይላል፡፡ ከዛላችሁማ… “አንድ በያይነቱ” ይልና ወደ እሷ ዞሮ “አንዱን በልተን ካነሰ ብንጨምር አይሻልም?” ይላታል፡፡
ይቀጥልናም “የሚጠጣ ምን አለ?” ይላል፡፡
“ለስላሳ፣ ቢራ ውስኪ፣ ዋይን…” እየተባለ ይዘረዝርለታል፡፡ ወደ እንትናዬው ዘወር ይልና “ውሀ ይሻለናል፣ አይደል!” ይልና ለአስተናጋጁ ምን ቢለው ጥሩ ነው…
“በጆግ ውሀ አምጣልን…”
እናላችሁ…በአንድ በየአይነቱና በጆግ ውሀ እሷዬዋን ‘ሊያሰምጡ’ የሚሞክሩ እንትናዎች የምር…የሆነ ‘የክብር’ ምናምን ያስፈልጋቸዋል፡፡ አሀ…በዘንድሮ ኑሮ እንዲህ ካልሆነ እንዴት ይሰነበታል!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የጆግ ውሀ ነገር ካነሳን አይቀር …“ይሄ ነገር ውሀ አይቋጥርም…” “ያ ነገር ውሀ አያነሳም…” ምናምን የሚባል ነገር የሆነ የማይመች ነገር ያለው አይመስልም! አሀ… ልክ ነዋ…ፈረንጆቹ ‘ኢት ዳዝንት ሆልድ ወተር’ ምናምን ብለው ከውሀ ጋር ሲያያዙት…አለ አይደል….የሆነ ነገር ሊኖራቸው ይችላል፡፡ እኛ…“ከውሀ ጋር ለምን አያያዛችሁት?” ብንባል ምን ልንል ነው! ለነገሩ… ‘‘ዳይሬክቶሬት፣’ ‘ሴክተር፣’ ‘ትራንስፎርሜሽን’ ምናምን አይነት የፈረንጅ አፍ ነገሮች ‘የአገር ልጅ አፍ’ ባልጠፋበት ተቆጣጥረውን የለ!
እናማ…እኛ ውሀ ሲቋጥሩ የምናውቀው በክረምት ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ’ መንገዶች ናቸው፡፡ (‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች’ ከሚለው በውሰት የተወሰደ፡፡)
ደግሞላችሁ…የሆነ ዝግጅት ይዘገጃል፡፡ ዝግጅቱ “…ልክ ሰባት ሰዓት ላይ ይጀመራል…” ምናምን የሚባል ነገር ይጻፍበታል፡፡ እንደውም ከመጥሪያው ስር “…ሰዓት ይከበር…” ምናምን የሚባል ሁሉ ይጨመርበታል፡፡
የተጋበዘው ሰውም በተባለው ሰዓት የዝግጅት ስፍራውን ‘ጢም’ ያደርገዋል፡፡ እናላችሁ…ሰባት ሰዓት የተባለው ዝግጅት ስምንት ሰዓት ተኩል ‘ይጀመራል’፡፡ ሰዓት እንደማያከብሩ እያወቁ  ማን “…ሰዓት ይከበር…” ምናምን ብላችሁ ጻፉ አላቸው!
“ታዲያ ዜብራውን ለምን ሠሩት?” የሚያሰኘው ይሄኔ ነው፡፡
ደግሞላችሁ… የሆነ መሥሪያ ቤት ለሆነ ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ያወጣል፡፡ ለሁለት ክፍት ቦታ ሁለት ሺህ ምናምን ሰው ያመለክታል፡፡ ፈተናም ይሰጣል፡፡ ከዚያላችሁ ተፈታኞች ጥቂት ሳምንታት ሲመላላሱ ከከረሙ በኋላ “ለ…ክፍት የሥራ ቦታ የወጣው ማስታወቂያ ተሰርዟል”  ምናምን የሚባል ማስታወቂያ ይለጠፋል፡፡
እኔ የምለው… የእነኛ ሁሉ አመልካቾች ልፋትስ! ልክ ነዋ…እንዲህ ኑሮ በራሱ ‘በወረቀት ላይ ያልሰፈረ’ ቅጣት እየሆነ ባለበት ጊዜ… አለ አይደል… በሥራ አጥ አቅም ለትራንስፖርቱ፣ ለፎቶኮፒው ለምናምኑ ‘የፈሰሰው’ ገንዘብስ! ይህን ሁሉ ሰው አጉላልተው የሚሰርዙት ከሆነ መጀመሪያውኑ በሚገባ ሳያስቡበት ማን ማስታወቂያ አውጡ አላቸው!
“ታዲያ ዜብራውን ለምን ሠሩት?” የሚያሰኘው ይሄኔ ነው፡፡
እሱዬው እንደ ‘ድሮው ዘመን’ ሳይለፋ ሳይደክም፣ የሰፈር ልጅ ብጣሽ ወረቀት አስይዞ ሳይልክ፣ “ታላቅ ወንድሟ አገጬን እንዳያበረው!” ብሎ ሳይሰጋ ካፌ ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ የሆነች እንትናዬ ያገኛል፡ ከዛማ… አለ አይደል… ‘ፈረንካውን ከየት እንደሚያመጣው እግዜር ይወቀው’… ያንበሸብሻታል። (“ፈረንካውን ከየት እንደሚያመጣው እግዜር ይወቀው!” የምንባል ሰዎች እየበዛን ነው፡፡)
እናላችሁ…አንድ ሦስት ቀን…ቅድመ ማጣሪያ ምናምን አይነት ዝግጅት ካካሄደ በኋላ ከዛ ሁሉ ግብዣ በኋላ እንደ መብቱ የሚቆጥረውን ‘የእነሆ በረከት’ ጥያቄ ያቀርባል፡፡ ከራሱም፣ ከሚያውቃቸውም ሰዎች ተሞክሮ እንደሚያውቀው በዚህ አይነት ጥያቄ “አይመቸኝም…” የሚል መልስ መስማት እንደ ሰበር ዜና “ጉድ!” የሚያሰኝ ነው፡፡
እሷዬዋም… “አልነገርኩህም እንዴ ሰው አለኝ እኮ…” ትለዋለች፡፡ እሱዬውም በሆዱ “ሁ ኬርስ! ሰው የሌለው ማንን አይታለች!” ምናምን ይልና “ታዲያ ምን ችግር አለው!” ይላታል፡፡ እሷ ግን… “አይ እኔ እኮ በንጹህ እህትነት ነው የቀረብኩህ!” ምናምን ስትለው… ምን አለፋችሁ… የሆነ ‘እንቁልልጭ ተብለው ዕጢያቸው ዱብ ያለ ምስኪኖች ሊብሬሽን ፍሮንት’ አይነት ነገር ሊያቋቋም ምንም አይቀረው፡፡
እኔ የምለው…እሷዬዋ እንዲህ አይነት መልስ ለመስጠት ማን የዜብራ መስመሮቹን አስምሪ አላት፡፡ ፊልም ገብታ እጁ እንደ ሚግ ተዋጊ ሲምዘገዘግ ማን ዝም በይ አላት (የጥያቄ ‘አሜንድመንት’  አለን…ምን አይነት ወንድም ነው እንደዛ እጁን እንደደነበረ በቅሎ በየቦታው የሚያሯርጠው!) …ቂ…ቂ…ቂ…
እናማ “ታዲያ ዜብራውን ለምን ሠሩት?” የሚያሰኘው ይሄኔ ነው፡፡
በደማቅ ቀለም ተሰምረው ለመሻገር የማይፈቀድባቸው ‘ዜብራ’ መስመሮች በሙሉ ይጥፉልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 2489 times