Saturday, 08 August 2015 08:05

እያቃጠለ ከሚያጠግበኝ እስኪቀዘቅዝ ይራበኝ

Written by 
Rate this item
(14 votes)

ለዓመታት የአዕምሮ ሆስፒታል የቆየ አንድ ሰው ነበረ፡፡ ተሽሎት ከሆስፒታሉ ይውጣ ከተባለ በኋላ
ዶክተሩ እስቲ ለማንኛውም ቃለ - መጠይቅ ላድርግለት ብሎ ያስጠራውና፤
“እስቲ አንድ ነገር ንገረኝ፡፡ አሁን ከዚህ ሆስፒታል ብትወጣ ኑሮህን እንዴት አድርገህ ለመምራት ታስባለህ?” አለው፡፡ ሰውዬውም፤ “መቼም ተመልሼ ህይወት መጀመሬ በጣም ድንቅ ነገር ነው፡፡
ኑሮዬን ለመምራት የመጀመሪያ እርምጃዬ ዱሮ የሠራኋቸውን ስህተቶች አለመድገም ነው። የኒኩሊየር
ፊዚክስ ባለሙያ ነበርኩ፡፡ የኒኩሊየር መሣሪያ ጥናትና ምርምር ነበር አዕምሮዬ እንዲነካ ያደረገው፡፡
ከዚህ ብወጣ ወደ ንፁሁ ንድፈ - ሀሳብ ላይ ብቻ አተኩራለሁ፡፡ ያ ብዙ የማያስጨንቀኝ ስለሆነ
ሰላም አገኛለሁ”
የአዕምሮ ሐኪሙ፡-
“ድንቅ ነው!” አለ በመደሰት፡፡
“አለበለዚያ ደግሞ” አለና ቀጠለ ሰውዬው፤ “ላስተምርም እችላለሁ። የሳይንቲስት ትውልድ የማፍራት ኃላፊነት ያለብን ይመስለኛል፡፡ በዚያ ረገድ ላግዝ እችላለሁ፡፡” “በጣም ትልቅ ሀሳብ ነው” አለ የአዕምሮ ሀኪሙ፡፡ “ሌላው አማራጬ ደግሞ መፃፍ ነው፡፡ ህዝባችን የሳይንስ መፅሀፍ ዕጥረት አለበት፡፡ ወይም ደግሞ
በዚህ መልካም ተቋም ውስጥ ስላገኘሁት ልምድ ልፅፍም እችላለሁ፡፡” “ያማ በጣም የጠለቀ፣ ግሩም አማራጭ ነው” አለ ሀኪሙ፡፡ “በመጨረሻም” አለ የአዕምሮ ህመምተኛው፤
“በመጨረሻም፤ እነዚህ ሁሉ አማራጮች እምቢ ካሉኝ፣ በቃ የቡና ጀበና መሆኔን እቀጥላለሁ!” አለ፡፡
ሐኪሙ ጭንቅላቱን ይዞ፤
“በል እዚሁ ቁጭ በል!” አለው፡፡
*       *      *
ደህና ሄደን ከመቆልመም ይሰውረን፡፡ የጀመርነውን በአግባቡ ለመጨረስ ጥናቱንም ፅናቱንም ይስጠን! በሙስና ከመመንደግ፣ ቁልቁል ከማደግ ዲበ - ኩሉ ይጠብቀን! ከሸፍጠኛ ዳኛ፣ ከአባይ መስካሪ ያድነን! የመጪውን ዓመት ትምህርታችንን ይግለጥልን! ያለፈውን ዓመት ስህተታችንን እንዳንደግም ልብና ልቡና ይስጠን፡፡ ከውጪ ሸረኛ፣ ከውስጥ ቂመኛ ይጠብቀን፡፡ ሀገራችን “ደንጊያና ቅል ተላግቶ፣ ዜጋና ሹም ተሟግቶ አይሆንም” የማንልባት ሀገር መሆን ይኖርባታል፡፡ ሹም ሲበድል ዝም ብለን የማናይበት፣ ዜጋ መብቱን ሳያውቅ ሲቀር ምክንና ውጤቱን በወግ በወጉ የምናስረዳበት ሁኔታ እንዲኖር መጣር ይኖርብናል፡፡ “እናቱ ወንዝ የወረደችበትም እናቱ የሞተችበትም እኩል የሚያለቅሱበት” ሀገር መሆን የለባትም፡፡ ከቶውንም ሃይማኖታዊ አስተምህሮት ከፖለቲካዊ ጥቅም ፍለጋ ተለይተው የሚታዩበት ሀገር ታስፈልገናለች፡፡ ከሁሉም በላይ ዛሬ ሐሳዊ - ዲሞክራሲን (Pseudo - democracy) መዋጋት ግዴታ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ በአስመሳይነት በአደባባይ መደስኮርና ዕውነተኛው ዲሞክራሲ ለየቅል ናቸው! መንግሥት የአምስት ዓመቱን ዕቅድ አፈፃፀም ድክመትን በወጉ ገምግሞ ዓይነተኛ መፍትሄ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ የእከክልኝ ልከክልህን ዜማ ቅኝቱን በመሰረታዊ መልኩ መለወጥ ይኖርበታል፡፡
በተለይም ደግሞ በሂደቱ ውስጥ ዓይን እንደሚቆረቁር አሸዋ ሲያስቸግር የነበረውን ሙስና በቅጡ
መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ዛሬም የፍትህን፣ የሰብዓዊ መብቶችን፣  የትምህርት ሂደትን ጉዳይ በአፍዓዊ መልኩ ሳይሆን በልባዊ መልኩ መመርመር መሰረታዊ ነገር ነው፡፡ ይህ ካልሆነ “እያቃጠለ ከሚያጠግበኝ፣ እስኪቀዘቅዝ ይራበኝ” የሚለውን መጥቀስ ግድ ይሆናል፡፡ ከዚህም ይሰውረን!

Read 5089 times