Saturday, 08 August 2015 08:04

አፍሪካን ከራሷ አምባገነኖች የሚያላቅቃት ትሻለች!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(9 votes)

አሜሪካና ቻይና “ቀዝቃዛውን ጦርነት” እንዳይጀምሩት እሰጋለሁ
ቻይና በባራክ ኦባማ የአፍሪካ ጉብኝት “ቀንታለች” ልበል!?

   የዛሬ የፖለቲካ ወጋችን ያነጣጠረው በእናት አህጉር አፍሪካ ላይ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን የመሰረተ ልማት ግንባታችን ቀኝ እጅ ስለሆነችው ስለ ኮሙኒስቷ ቻይና ጥቂት እንድናወራ ወደድኩኝ፡፡ (ግራ ዘመም መሆኗ አልጠፋኝም!) በነገራችን ላይ በኦባማ የአፍሪካ ጉብኝት ቻይና ቅናት ቢጤ እንዳደረባት የፖለቲካ ተንታኞች ጠርጥረዋል፡፡ (ለምን በተራዋ ፕሬዚዳንቷን አትልካቸውም?!) በአንድ በኩል ደሞ -----
አይፈረድባትም፡፡ (ማን ባቀናው ማን ይፏልልበታል?) ሃቁን ለመናገር እኮ -------- ቻይና ከአፍሪካ ጋር የመሰረተችውን ግንኙነት እዚህ ለማድረስ ብዙ መስዋዕትነት ከፍላበታለች። በመጠነኛ ወለድ ብድር እየሰጠች ----- በአገራት ፖለቲካዊ ጉዳይ እጇን ሳታስገባ ------ የአፍሪካን መሰረተ ልማት በመገንባት ላይ የምትገኝ የክፉ ጊዜ አጋራችን ናት፡፡ (ለኢህአዴግም 1ለ5 ስትራቴጂን አሰልጠናዋለች ልበል?!) ቻይና በኦባማ ጉብኝት ቅናት ሲወዘውዛት መሰንበቷን የሚጠቁሙ የህትመት ማስረጃዎችም ተገኝተዋል። (በፅሁፍ አልቀራት በካርቱን!) እናላችሁ----ኦባማ ኬንያንና ኢትዮጵያን ሲጎበኙ  የቻይና መንግስት ልሳኖች እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሚዲያዎች ጉብኝቱን ክፉኛ ሲያጣጥሉት እንደነበር ለመረዳት ችለናል፡፡
ግሎባል ታይምስ የተሰኘው በእንግሊዝኛ የሚታተም የቻይና ዕለታዊ ጋዜጣ ባወጣው ሃተታ፤ “አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር የኢኮኖሚ ትብብሯን ለማደስ የተነሳሳችው ቻይና በአህጉሪቱ ያላት ተፅዕኖ እየሰፋና እየፈረጠመ መምጣቱ በፈጠረባት ስጋት ነው” ብሏል፡፡ አሜሪካ በአፍሪካ ውስጥ ገናና ኃይል እንደነበራት ያስታወሰው ጋዜጣው፤ያንን ሚናዋን በቻይና መነጠቋ #ነርቯን ነክቷታል” ሲል ጽፏል፡፡ ግሎባል ታይምስ፤አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር የጀመረቻቸውን የልማት ትብብሮች በጭፍን እስከማጣጣል ሁሉ ደርሷል፡፡ ኦባማ በቅርቡ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የሚገኙ የንግድ ሥራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት ይፋ ያደረጉትን የ1 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ #ትርጉም ያለው ለውጥ አያመጣም” ሲል በደፈናው አጣጥሎታል፡፡ ለ50 ሚሊዮን አፍሪካውያን የኤሌትሪክ ሃይል የማዳረስ ግብ ሰንቆ የተነሳውንም የ7 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ጋዜጣው አናንቆታል - ምንም ዕድገት አላሳየም በሚል፡፡ (ቻይና፤አሜሪካን በአፍሪካ አልያት የምትል ትመስላለች!?)  ከዚህም የሚብሰው ደግሞ ጋዜጣው ያወጣው ;ዘረኛ ካርቱን” ነው - እንደ ዋሽንግተን ፖስት ዘገባ። “Homecoming; በሚል ርዕስ ሥር በኦባማ ወደ ኬንያ መምጣት ለመሳለቅ የተሰራው ካርቱን፤ኦባማ የአፍሪካ የጎሳ ልብስ ለብሰውና በእጃቸው ጦር ይዘው፣በአፍሪካ ዱር ውስጥ የሜዳ አህዮችን ሲቃኙ የሚያሳይ ነው። ይሄ ካርቱን ኦባማንም ሆነ ኬንያውንን የሚያበሳጭ እንደሚሆን ዋሽንግተን ፖስት ጠቁሟል፡፡ የቻይናው ግሎባል ታይምስ፣ የአፍሪካ መልክአምድርን የወከለበት ምስል የተሰለቸና ቂላቂል ነው ሲል የነቀፈው ዋሺንግተን ፖስት፤በዚሁ ጊዜ የኬንያ ጋዜጦች የኦባማን መምጣት አስመልክቶ ያወጧቸው ካርቱኖች ሺ ጊዜ ያስንቁታል ብሏል። (ከዚህ በላይ “ቀዝቃዛው ጦርነት” ከየት ይምጣ?)በነገራችን ላይ ኦባማም እኮ ዝም አላሉም፡፡ ቻይና በአፍሪካ የምታደርገውን እንቅስቃሴ ስም ሳይጠቅሱ ተችተዋል፡፡ (ያውም ራሷ ገንብታ በሰጠችው የአፍሪካ ህብረት ህንፃ ውስጥ ነው!) “መሰረተ ልማት መገንባትና የተፈጥሮ ሃብትን ማሟጠጥ የኢኮኖሚ አጋርነት አይባልም” ያሉት ኦባማ፤የኛ ግን ላለፉት በርካታ በአስርት ዓመታት በመገንባት ላይ የሚገኝ የልማት አጋርነት ነው ብለዋል፡፡ (የቃላት ውርወራው አይሏል!)አሁን በቀጥታ ወደ እናት አህጉር አፍሪካ እንዝለቅ። ይኼውላችሁ … በዛሬ ወጋችን ኦባማ በአፍሪካ ህብረት የማንዴላ አዳራሽ (የቀኃሥ አዳራሽ አለመኖሩ ያበግናል?!) ባደረጉት ንግግር፤ ሥልጣን ላይ ችክ አትበሉ ያሏቸውን የአፍሪካ መንግሥታት ነው የምንቃኘው፡፡  እኔ የምለው ግን … ሥልጣን ርስቴ ብለው የተቀመጡ ፈላጭ ቆራጭ የአፍሪካ አምባገነን መሪዎችን #በቃችሁ!!# ለማለት ኦባማ ከአሜሪካ እስኪመጡ መጠበቅ ነበረብን? (በአፍሪካ ህብረት አፈርኩኝ!) ለነገሩ የህብረቱ የወቅቱ ሊቀመንበር እኮ---ዚምባቡዌን ከ34 ዓመታት በላይ እንደ ግል ንብረታቸው እየገዙዋት ያሉት ሙጋቤ ናቸው፡፡ ኦባማ በህብረቱ አዳራሽ ንግግራቸው፤“የአፍሪካ መሪዎች በቂ ገንዘብ እያላቸውም እንኳን ከስልጣን አንወርድም ብለው የሚፈጠሙበት ምክንያት ጨርሶ አይገባኝም” ያሉት ነገር ትክክል ነው። “ሥልጣን ወይም ሞት” ብለው የሙጥኝ ያሉት የአፍሪካ መሪዎች በሙሉ ዲታ  መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ አንድ ድረ-ገጽ፤8ቱ የአፍሪካ እጅግ ባለጸጋ ፕሬዚዳንቶች  በሚል ባወጣው ዝርዝር ውስጥ ለአጭር ጊዜ በስልጣን ላይ የቆዩት የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሄሬ ኬንያታ ብቻ ናቸው። የ500 ሚ. ዶላር ባለሀብቱ ኬንያታ፤ ሥልጣን ላይ የወጡት ገና በ2013 ዓ.ም ነው፡፡በሃብት የአፍሪካን ፕሬዚዳንቶች የሚመሩት የአንጎላው መሪ ጆሴ ኢዱራዶ ዶስ ሳንቶስ ሲሆኑ ያላቸውን የገንዘብ መጠን ስትሰሙ አዙሯችሁ ልትወድቁ ትችላላችሁ፡፡ ሰውየው በመሪነት 20 ቢ.ዶላር አካብተዋል። ሁለተኛው ቢሊዬነር የሞሮኮው ንጉስ መሐመድ VI ደግሞ 2.1 ቢ. ዶላር ሲኖራቸው ለ15 ዓመት በስልጣን ላይ ኖረዋል፡፡ የካሜሩን ፕሬዚዳንት ፓውል ቢያ፣ 31 ዓመት በስልጣን ላይ ተፈናጠው፣ 200 ሚ. ዶላር አካብተዋል፡፡ (ከስልጣን የሚወርዱበት ጊዜ አይታወቅም!)
ከ34 ዓመት በላይ በስልጣን ኮርቻ ላይ ተቀምጠው በዕድሜያቸው መጥለቂያ ላይ ስልጣናቸውን ለሚስታቸው ያውርሱ ለልጃቸው ግራ የተጋቡት የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ደግሞ

የ10ሚ. ዶላር ባለፀጋ ናቸው፡፡ የቻዱ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ አይትኖ፣ የ25 ዓመት የስልጣን

ዘመንና የ50ሚ. ዶላር ሀብት ያላቸው ቀጭን ጌታ ናቸው፡፡ የኢኳቶሪያል ጊኒው ቴዎዶሮ ኦብያንግ

ንጉማ ምባሶጎ፣ የ600 ሚ. ዶላር ባለጸጋ ሲሆኑ ለ34 ዓመት አገራቸውን አንቀጥቅጠው ገዝተዋል፡፡
እውነቱን ልንገራችሁ አይደል … ዕድሉን የሚሰጠው አጥቶ እንጂ የአፍሪካ ህዝብ ከቅኝ ገዢዎችና

ከራሱ አምባገነኖች እንዲመርጥ ሪፍረንደም ቢካሄድ…በእርግጠኝነት የቀድሞ ቅኝ ገዢዎቹን

እንደሚመርጥ በ1ሚሊዮን ብር አሲዛለሁ፡፡ (ስፖንሰር ከተገኘ ነው ታዲያ!)
እስቲ አሁን ደግሞ አሁን ደግሞ 10ሩን በሙስና ክፉኛ የተጠቁ የአፍሪካ አገራትን ዝርዝር እንቃኝ!!

(ባለፀጎች መሪዎች ባሉባቸው አገራት ሙስናው የከፋ፣ህዝቡ ደግሞ ድሃ እንደሚሆን ጠርጥሩ!)

እናላችሁ ----- በሙስና ቶፕ 10 ውስጥ በቀዳሚነት የምትመጣው በአሸባሪዎች የምትንገላታው

ጎረቤት አገር ሶማሊያ ናት፡፡ 2ኛ ሱዳን፣ 3ኛ ቡሩንዲ (የስልጣን ዘመን በማራዘም በኦባማ

የተነቀፉት ፕሬዚዳንት የሚማሯት አገር) 4ኛ - ቻድ (መሪዋ የ50 ሚ. ዶላር ባለቤት!) 5ኛ

ዚምባቡዌ (የ10 ሚ.ዶላር ባለሃብት መሪ ያላት) 6ኛ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ 7ኛ የኮንጎ ዲሞክራቲክ

ሪፐብሊክ፣ 8ኛ - ሊቢያ፣ 9ኛ - አንጎላ፣ 10ኛ ጊኒ--- ናቸው፡፡
አያችሁልኝ ----- በአፍሪካ እንዴት የመሪዎች ባለጸጋነት፣ከረዥም የሥልጣን ዘመን፣ ከሙስናና

ከከፋ የአገራት ድህነት ጋር በቀጥተኛ እንደሚገናኝ!! (This is Africa!) እናላችሁ---አሁን አፍሪካ

ከራሷ አምባገነኖች የሚያላቅቃት ነጻ አውጭ ትፈልጋለች! (ተከፍሏቸው ነጻ የሚያወጡ ቢኖሩማ

ግልግል ነበር!)

Read 3696 times