Saturday, 01 August 2015 14:59

የኢትዮጵያ ክለቦች በምስራቅ አፍሪካ ተፎካካሪ መሆን አልቻሉም

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በታንዛኒያ ከተማ ዳሬሰላም 13  ክለቦችን በማሳተፍ ሲካሄድ የቆየው 48ኛው የምስራቅ አፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንሺፕ (ካጋሜ ካፕ) ትናንት በግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ቀጥሏል፡፡
ከግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎቹ በፊት በተደረጉት 26 ጨዋታዎች 74 ጎሎች ተቆጥረዋል፡፡ በአንድ ጨዋታ በአማካይ 2.54 ጎሎች ማለት ነው፡፡
የኡጋንዳው ክለብ ካምፓላ ሲቲ የሱዳኑን አልሃሊ ሸንዲ 3ለ0 በማሸነፍ እንዲሁም ሌላው የኡጋንዳ ክለብ አዛም የታንዛኒያውን ያንግ አፍሪካንስ በመለያ ምት 5ለ3 አሸንፎ ለግማሽ ፍፃሜ ደርሰዋል፡፡ ሁለቱም ክለቦች በምድብ 3 ከአዳማ ከነማ ጋር የተደለደሉ ነበሩ፡፡ በግማሽ ፍፃሜ እርስበራስ ተገናኝተዋል፡፡ ሌሎቹ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚዎች የሱዳኑ አል ካርቱም እና የኬንያው ጎሮማሃያ ናቸው፡፡ አልካርቱም በሩብ ፍፃሜ የሩዋንዳውን ኤፒአር 4ለ0 ሲረታ ጎሮማሃያ ደግሞ የደቡብ ሱዳኑን አል ማላይካ 2ለ1 በማሸነፍ ለግማሽ ፍፃሜው ደርሰዋል፡፡ ትናንት ሁሉም የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ተደርገዋል፡፡
ኢትዮጵያን በመወከል የተሳተፈው  አዳማ ከነማ በምድብ 3 ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች ተሸንፎ በጊዜ የተሰናበተው ምንም ነጥብ ሳያስመዘግብ በሰባት የግብ እዳ ነው፡፡  በምድብ 3 የመጀመርያ ጨዋታውን ከደቡብ ሱዳኑ ክለብ ማላይካ ጋር ባደረገበት ወቅት በ30ኛው ደቂቃ ታከለ አለማየሁ ባስቆጠረው ግብ  አዳማ ከነማ መምራት ቢችልም በመጨረሻ 2ለ1 ነበር የተሸነፈው፡፡  በሁለተኛው ጨዋታ ተገናኝቶ የነበረው ከኡጋንዳው ተወካይ ኬሲሲ ጋር ነበር፡፡  በ79ኛው ደቂቃ ያቆብ ፍስሃ በፈፀመው ፋውል ፍፁም ቅጣት ከተሰጠበት በኋላ የኬሲሲ አምበል  ጎሉን በማስቆጠሩ 1ለ0 ተሸንፏል፡፡ በምድብ 3 የመጨረሻ ጨዋታውን ከታንዛኒያ ክለብ አዛም ጋር አድርጎ 4ለ0 ከተሸነፈ በኋላ ከውድድሩ መሰናበቱ ይታወቃል፡፡ በሴካፋ የክለቦች ሻምፒዮና ካጋሜ ካፕ ታሪክ የኢትዮጵያ ክለቦች ውጤታማነት ቢያንስ ከአምስት የዞኑ አባል አገራት ከኬንያ፤ ኡጋንዳ፤ ታንዛኒያ፤ ሩዋንዳና ብሩንዲ ያነሰ ነው፡፡ በክለቦች ሻምፒዮናው ኢትዮጵያን የወከለ ክለብ ያስመዘገበው ትልቁ ውጤት ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2010 እኤአ ላይ ለዋንጫ ጨዋታ የደረሰበት ብቻ ነው፡፡ በምስራቅ አፍሪካ የክለቦች ሻምፒዮና ላይ እጅግ ውጤታማው ክለብ የታንዛኒያው ሲምባ ሲሆን ባገኛቸው ስድስት ዋንጫዎች ነው፡፡ የኬንያው ኤፍሲ ሊዮፓርድስ፤ የታንዛኒያው ያንግ አፍሪካንስ፤ የኬንያዎቹ ጎሮማሃያ እና ታስከር ኤፊሲ እኩል ለ5 ጊዜያት ዋንጫዎችን በመውሰድ በከፍተኛ ውጤት ሁለተኛ ደረጃን ተጋርተዋል፡፡ የሩዋንዳው ኤፒአርና የሱዳኑ አልሜሪክ እያንዳንዳቸው ሁለት ዋንጫዎችን ሲቀዳጁ፤ የኡጋንዳው ኬሲሲ፤ የሩዋንዳው አትራኮን፤ የኡጋንዳው ፖሊስ ኤፍሲ፤ የሩዋንዳው ራዮን ስፖርትስ፤ እንዲሁም የብሩንዲው ቪታሎ ኦ ቢያንስ አንድ ጊዜ የዋንጫው ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በአገር ደረጃ ደግሞ የኬንያ ክለቦች 15 ጊዜ ሻምፒዮን በመሆን ሲመሩ፤የታንዛኒያ ክለቦች በ11 የዋንጫ ድሎች ይከተሏቸዋል፡፡ የኡጋንዳ ክለቦች 5 ጊዜ፤ የሩዋንዳ ክለቦች 4 ጊዜ ፤ የሱዳን ክለቦች 3 ጊዜ እንዲሁም አንድ የብሩንዲ ክለብ የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
በዓለም አቀፉ የእግርኳስ ፌደሬሽኖች ታሪክ እና አሃዛዊ መረጃ አሰባሳቢ ማህበር (IFFHS) መሰረት ባለፉት 10 ዓመታት ምርጥ የምስራቅ አፍሪካ ክለቦች የደረጃ ዝርዝር እስከ 10ኛ እንድም ኢትዮጵያዊ ክለብ የለበትም፡፡ በደረጃ ሰንጠረዡ በዝተው የሚገኙት የኡጋንዳ፤ የኬንያ፤ የታንዛኒያና የብሩንዲ ክለቦች ናቸው፡፡ በአይኤፍኤችኤችኤስ መለኪያ መሰረት ባለፉት 10 ዓመታት ባስመዘገበው ውጤት አንደኛ ደረጃ የተሰጠው የታንዛኒያው ክለብ ሲምባ ነው፡፡ በመቀጠል ደረጃውን አከታትለው እስከ 4ኛ ደረጃ የያዙት የኡጋንዳ ክለቦች ኤስሲ ሲቪላ፤ካምፓላ ሲቲ ኬሲሲ እና ኤክስፕረስ ናቸው፡፡ የኬንያው ታስከር፤ የኡጋንዳው ዪአርኤ፤ የታንዛኒያዎቹ ያንግ አፍሪካንስና ሚትብዋ ሹገር፤ የኬንያው ማታሬ ዩናይትድ፤ የብሩንዲው ኡሊንዚ ስታርስ እና ሶኒ ሹገር እስከ 10 ያለውን ደረጃ ወስደዋል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ ክለቦች በአንፃሩ በህጉራዊ የክለብ ውድድሮች ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌደሬሽን ካፕ ብዙም ውጤታማ አይደሉም፡፡ የሱዳን ክለቦች አልሁላል፤ ኤልሜሪክ በቅርብ አመታት በሻምፒዮንስ ሊግ ያስመዘገቡት ስኬት ብቻ ለየት አድርጎ አውጥቷቸዋል፡፡የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በሚያወጣው የየአምስት ዓመቱ የአህጉራዊ ክለቦች የውጤት ደረጃ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ላይም የሱዳን ክለቦች በ33 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ክለቦች በ4 ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ በኮንፌደሬሽን ካፕ አሁንም የሱዳን ክለቦች በ31 ነጥብ አምስተኛ ሲሆኑ፤ የኢትዮጵያ በ7 ነጥብ 17ኛ ናቸው፡፡

Read 3280 times